በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መጽሐፍ ቅዱስን ማን እንደጻፈው በእርግጠኝነት ማወቅ ይቻላል?

መጽሐፍ ቅዱስን ማን እንደጻፈው በእርግጠኝነት ማወቅ ይቻላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 ብዙ ሰዎች ‘መጽሐፍ ቅዱስን ማን እንደጻፈው በእርግጠኝነት ማወቅ አንችልም’ የሚል ትምህርት ተምረዋል። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ በውስጡ ያለው ሐሳብ በማን እንደተጻፈ በግልጽ ይናገራል። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የሚጀምሩት “የነህምያ ቃል፣” “ኢሳይያስ . . . ያየው ራእይ፣” “ወደ ኢዩኤል የመጣው የእግዚአብሔር ቃል” እንደሚሉት ባሉ ሐሳቦች ነው።—ነህምያ 1:1፤ ኢሳይያስ 1:1፤ ኢዩኤል 1:1

 አብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች እውነተኛ አምላክ የሆነውን የይሖዋን ሐሳብ እንደጻፉ እንዲሁም የጻፉት በእሱ ተመርተው እንደሆነ ተናግረዋል። የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን የጻፉ ነቢያት ከ300 ጊዜ በላይ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል” በማለት ተናግረዋል። (አሞጽ 1:3፤ ሚክያስ 2:3፤ ናሆም 1:12) ሌሎች ጸሐፊዎች ደግሞ አምላክ መልእክቱ እንዲደርሳቸው ያደረገው በመላእክት አማካኝነት ነው።—ዘካርያስ 1:7, 9

 መጽሐፍ ቅዱስን የጻፉት 40 የሚያህሉ ሰዎች ሲሆኑ ተጽፎ ያለቀው ከ1,600 ዓመታት በሚበልጥ ጊዜ ውስጥ ነው። አንዳንድ ጸሐፊዎች ከአንድ በላይ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍትን ጽፈዋል። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ 66 መጻሕፍትን የያዘ አነስተኛ ቤተ መጻሕፍት ነው ማለት ይቻላል። በተለምዶ ብሉይ ኪዳን ተብለው የሚጠሩ 39 የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትንና ብዙውን ጊዜ አዲስ ኪዳን ተብለው የሚጠሩ 27 የክርስቲያን ቅዱሳን መጻሕፍትን ይዟል።