በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መግደላዊቷ ማርያም ማን ነበረች?

መግደላዊቷ ማርያም ማን ነበረች?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 መግደላዊቷ ማርያም የኢየሱስ ክርስቶስ ታማኝ ተከታይ ነበረች። መግደላዊቷ የሚለው ስም የመጣው በገሊላ ባሕር አቅራቢያ ከሚገኘው የመጌዶል (መጌዶን ሊሆንም ይችላል) ከተማ ሳይሆን አይቀርም። ምናልባትም ማርያም በሆነ ወቅት ላይ ትኖር የነበረው በዚያ ከተማ ሊሆን ይችላል።

 መግደላዊቷ ማርያም ከኢየሱስና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በመጓዝ ቁሳዊ ድጋፍ ይሰጧቸው ከነበሩት በርካታ ሴቶች አንዷ ነበረች። (ሉቃስ 8:1-3) በተጨማሪም ኢየሱስ ሲገደል የዓይን ምሥክር ነበረች፤ እንዲሁም ትንሣኤ ካገኘ በኋላ መጀመሪያ ላይ ከተመለከቱት ሰዎች አንዷ እሷ ነች።—ማርቆስ 15:40፤ ዮሐንስ 20:11-18

 መግደላዊቷ ማርያም ዝሙት አዳሪ ነበረች?

 መጽሐፍ ቅዱስ መግደላዊቷ ማርያም ዝሙት አዳሪ እንደነበረች አይገልጽም። ከዚህ ይልቅ ስለ እሷ የቀድሞ ታሪክ የሚናገረው፣ ኢየሱስ ሰባት አጋንንት እንዳስወጣላት ብቻ ነው።—ሉቃስ 8:2

 ታዲያ ዝሙት አዳሪ እንደነበረች የሚገልጸው ሐሳብ የመጣው ከየት ነው? መግደላዊቷ ማርያም ከሞተች ከበርካታ መቶ ዓመታት በኋላ አንዳንድ ሰዎች የኢየሱስን እግር በእንባዋ በማራስ በፀጉሯ ያበሰችው ስሟ ያልተጠቀሰች ሴት (ይህች ሴት ዝሙት አዳሪ ሳትሆን አትቀርም) መግደላዊቷ ማርያም እንደሆነች መናገር ጀመሩ። ሆኖም እንዲህ ብሎ ለማመን የሚያበቃ ምንም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ የለም።

 መግደላዊቷ ማርያም “ለሐዋርያት ሐዋርያ” ነበረች?

 አልነበረችም። የኢየሱስን ትንሣኤ ለሐዋርያቱ መጀመሪያ ላይ ካበሰሩት ሴቶች አንዷ መግደላዊቷ ማርያም በመሆኗ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን “ቅድስት መግደላዊቷ ማርያም” እንዲሁም “ለሐዋርያት ሐዋርያ” በማለት ትጠራታለች። (ዮሐንስ 20:18) ሆኖም የኢየሱስን ትንሣኤ ለሐዋርያት ማብሰሯ ሐዋርያ አያደርጋትም። መጽሐፍ ቅዱስ አንድም ቦታ ላይ መግደላዊቷ ማርያምን “ሐዋርያ” በማለት አይጠራትም።—ሉቃስ 6:12-16

 መጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ የተጠናቀቀው በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. መገባደጃ ላይ ነው። ሆኖም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለመግደላዊቷ ማርያም ከፍ ያለ ቦታ መስጠት የጀመሩት በስድስተኛው ክፍለ ዘመን ነው። በሁለተኛውና በሦስተኛው ክፍለ ዘመን ላይ የተጻፉ ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ያልሆኑ መጻሕፍት፣ አንዳንዶቹ የኢየሱስ ሐዋርያት በማርያም ይቀኑ እንደነበረ ይገልጻሉ። እንዲህ ያሉት የፈጠራ ታሪኮች ምንም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የላቸውም።

 መግደላዊቷ ማርያም የኢየሱስ ክርስቶስ ሚስት ነበረች?

 በፍጹም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ትዳር እንዳልመሠረተ በግልጽ ያስተምራል። a