በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው

ዮሐንስ 3:16—“ዓለምን እንዲሁ ወዶአልና”

ዮሐንስ 3:16—“ዓለምን እንዲሁ ወዶአልና”

 “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።”—ዮሐንስ 3:16 አዲስ ዓለም ትርጉም

 “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።”—ዮሐንስ 3:16 አዲሱ መደበኛ ትርጉም

የዮሐንስ 3:16 ትርጉም

 አምላክ ይወደናል፤ እንዲሁም የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ ይፈልጋል። ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ምድር የላከው በዚህ ምክንያት ነው። ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ ብዙ ነገሮችን አከናውኗል። አንደኛ፣ ስለ አባቱና ስለ አምላኩ ተከታዮቹን አስተምሯል። (1 ጴጥሮስ 1:3) ሁለተኛ፣ ለሰው ልጆች ሲል ሕይወቱን ሰጥቷል። የዘላለም ሕይወት ለማግኘት በኢየሱስ ላይ እምነት ሊኖረን ይገባል።

 “አንድያ ልጁን ሰጥቷል” የሚለው አገላለጽ አምላክ ለሰዎች ምን ያህል ጥልቅ ፍቅር እንዳለው ያሳያል። a ኢየሱስ ልዩ የሆነ የአምላክ ልጅ ነው። ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው? አምላክ በቀጥታ የፈጠረው ኢየሱስን ብቻ ነው። (ቆላስይስ 1:17) ኢየሱስ “የፍጥረት ሁሉ በኩር ነው።” (ቆላስይስ 1:15) መላእክትን ጨምሮ ሌሎች ፍጥረታት በሙሉ የተፈጠሩት በኢየሱስ በኩል ወይም በእሱ አማካኝነት ነው። ያም ሆኖ ይሖዋ b አምላክ በጣም የሚወደው ልጁ ወደ ምድር መጥቶ ‘እንዲያገለግልና በብዙ ሰዎች ምትክ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ እንዲሰጥ’ ፈቅዷል። (ማቴዎስ 20:28) ኢየሱስ የመጀመሪያው ሰው አዳም ካወረሰን ኃጢአትና ሞት እኛን ነፃ ለማውጣት ሲል ተሠቃይቷል እንዲሁም ሕይወቱን አሳልፎ ሰጥቷል።—ሮም 5:8, 12

የዮሐንስ 3:16 አውድ

 ኢየሱስ በዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኘውን ሐሳብ የተናገረው ኒቆዲሞስ ከተባለ የአይሁድ የሃይማኖት መሪ ጋር በተነጋገረበት ወቅት ነበር። (ዮሐንስ 3:1, 2) ባደረጉት ውይይት ላይ ኢየሱስ ስለ አምላክ መንግሥት c እና ‘ዳግመኛ ስለ መወለድ’ አብራርቷል። (ዮሐንስ 3:3) በተጨማሪም ስለ አሟሟቱ ተናግሯል። “የሰው ልጅ . . . ሊሰቀል ይገባዋል፤ ይኸውም በእሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 3:14, 15) ቀጥሎም፣ አምላክ የሰው ልጆች የዘላለም ሕይወት የሚያገኙበት አጋጣሚ እንዲከፈት ያደረገው ለእነሱ ባለው ጥልቅ ፍቅር የተነሳ እንደሆነ ጎላ አድርጎ ገልጿል። በመጨረሻም ሕይወት ማግኘት ከፈለግን እምነት ማሳየትና አምላክን የሚያስደስቱ ሥራዎች መሥራት እንዳለብን በመናገር ሐሳቡን ደምድሟል።—ዮሐንስ 3:17-21

a “አንድያ” ተብሎ የተተረጎመው ሞኖየኒስ የሚለው የግሪክኛ ቃል “አንድና አንድ ብቻ፣ . . . በዓይነት ወይም በመደብ አምሳያ የሌለው፣ (በዓይነቱ) ልዩ የሆነ” የሚል ትርጉም አለው።—ኤ ግሪክ-ኢንግሊሽ ሌክሲከን ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት ኤንድ ኧርሊ ክሪስቲያን ሊትሬቸር፣ ገጽ 658

b ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው።—መዝሙር 83:18

በኢየሱስ ማመን በእሱ እንደሚያምኑ ከመናገር ወይም እሱ ላደረገልን ነገር እውቅና ከመስጠት ያለፈ ነገርን ይጠይቃል። እሱን በመታዘዝና የእሱን ፈለግ በመከተል በአምላክ ልጅ ላይ ያለንን እምነት ማሳየት ይጠበቅብናል። (ማቴዎስ 7:24-27፤ 1 ጴጥሮስ 2:21) መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “በወልድ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ ወልድን የማይታዘዝ ግን . . . ሕይወትን አያይም።”—ዮሐንስ 3:36

c የአምላክ መንግሥት (“መንግሥተ ሰማያት” ተብሎም ይጠራል) በሰማይ ያለ መስተዳድር ነው። (ማቴዎስ 10:7፤ ራእይ 11:15) አምላክ ክርስቶስን የዚህ መንግሥት ንጉሥ አድርጎ ሾሞታል። የአምላክ መንግሥት አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ እንዲፈጸም ያደርጋል። (ዳንኤል 2:44፤ ማቴዎስ 6:10) ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።