በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው

ማርቆስ 1:15—“የአምላክ መንግሥት ቀርቧል”

ማርቆስ 1:15—“የአምላክ መንግሥት ቀርቧል”

 “የተወሰነው ጊዜ ደርሷል፤ የአምላክ መንግሥት ቀርቧል። ንስሐ ግቡ፤ በምሥራቹም እመኑ።”—ማርቆስ 1:15 አዲስ ዓለም ትርጉም

 “ጊዜው ደርሶአል፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለች፤ ንስሓ ግቡ፤ በወንጌልም እመኑ!”—ማርቆስ 1:15 አዲሱ መደበኛ ትርጉም

የማርቆስ 1:15 ትርጉም

 ኢየሱስ ክርስቶስ የአምላክ መንግሥት a “ቀርቧል” ያለው እሱ ማለትም የዚያ መንግሥት የወደፊት ንጉሥ በወቅቱ በስፍራው ስለተገኘ ነው።

 ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት በዚያ ጊዜ መግዛት እንደጀመረ መናገሩ አልነበረም። እንዲያውም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ የአምላክ መንግሥት የሚመጣው ገና ወደፊት እንደሆነ የሚጠቁም ሐሳብ ነግሯቸዋል። (የሐዋርያት ሥራ 1:6, 7) ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ ወደፊት ንጉሥ ሆኖ የሚገዛው ኢየሱስ ስለሚገለጥበት ዓመት አስቀድሞ የተነበየ ሲሆን ኢየሱስም በዚያው ዓመት ላይ ተገልጧል። b በዚህም ምክንያት “የተወሰነው ጊዜ ደርሷል” ብሎ ሊናገር ችሏል፤ “የተወሰነው ጊዜ” የሚለው አገላለጽ ኢየሱስ ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸውን ወንጌል ወይም ምሥራች የመስበክ ሥራውን የሚጀምርበትን ጊዜ ያመለክታል።—ሉቃስ 4:16-21, 43

 ሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት ከሚገልጸው ምሥራች ጥቅም ማግኘት ከፈለጉ ንስሐ መግባት ማለትም ከዚህ በፊት በፈጸሙት ኃጢአት መጸጸትና በአምላክ መሥፈርቶች መሠረት ሕይወታቸውን መምራት ነበረባቸው። ንስሐ የገቡ ሰዎች፣ ስለ መጪው የአምላክ መንግሥት በሚገልጸው ምሥራች ላይ እምነት እንዳላቸው ያሳዩ ነበር።

የማርቆስ 1:15 አውድ

 ኢየሱስ እነዚህን ቃላት የተናገረው በገሊላ አገልግሎቱን ሲጀምር ነው። በማቴዎስ 4:17 ላይ የሚገኘው ተመሳሳይ ዘገባ ኢየሱስ “ከዚያን ጊዜ አንስቶ” ስለ አምላክ መንግሥት መስበክ እንደጀመረ ይናገራል። የኢየሱስ አገልግሎት ዋነኛ ርዕሰ ጉዳይ የአምላክ መንግሥት ነበር። እንዲያውም በአራቱ ወንጌሎች c ውስጥ የአምላክ መንግሥት ከ100 ጊዜ በላይ ተጠቅሷል፤ ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ የሚገኙት ኢየሱስ በተናገራቸው ሐሳቦች ላይ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኢየሱስ ከየትኛውም ርዕሰ ጉዳይ ይበልጥ የተናገረው ስለ አምላክ መንግሥት ነው።

ማርቆስ ምዕራፍ 1 አንብብ፤ እንዲሁም ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የግርጌ ማስታወሻዎቹንና ማጣቀሻዎቹን ተመልከት።

a የአምላክ መንግሥት፣ አምላክ ለምድር ያለውን ዓላማ ለማስፈጸም ሲል በሰማይ ያቋቋመው መስተዳድር ነው። (ዳንኤል 2:44፤ ማቴዎስ 6:10) ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት “የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

b ኢየሱስ አስቀድሞ የተነገረለት መሲሕ ማለትም የአምላክ ልዩ ወኪል በመሆን ከተሰጡት የሥራ ድርሻዎች መካከል አንዱን ለመወጣት ንጉሥ መሆን ነበረበት። ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን የሚጠቁሙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “ስለ መሲሑ የተነገሩት ትንቢቶች ኢየሱስ መሲሕ እንደሆነ ያረጋግጣሉ?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

c ወንጌሎች የሚባሉት በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙት የመጀመሪያዎቹ አራት መጻሕፍት ናቸው፤ እነዚህ መጻሕፍት በተለምዶ አዲስ ኪዳን በመባል የሚታወቁ ሲሆን ስለ ኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት የሚገልጹ ዘገባዎች ናቸው።