በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

ፍጥረት ወይስ ዝግመተ ለውጥ?—ክፍል 3፦ ፈጣሪ እንዳለ የማምነው ለምንድን ነው?

ፍጥረት ወይስ ዝግመተ ለውጥ?—ክፍል 3፦ ፈጣሪ እንዳለ የማምነው ለምንድን ነው?

“ፈጣሪ እንዳለ የምታምን ከሆነ ሰዎች ሞኝ አድርገው ሊመለከቱህ ይችላሉ፤ ይህ ዓይነት እምነት ሊኖርህ የቻለው ወላጆችህ የነገሩህን ወይም ሃይማኖትህ ያስተማረህን በጭፍን ስለምትቀበል እንደሆነ ይሰማቸዋል።”—ጃኔት

 አንተስ እንደ ጃኔት ተሰምቶህ ያውቃል? ምናልባትም ‘ፈጣሪ እንዳለ ማመኔ ትክክል ነው?’ በማለት አስበህ ይሆናል። በዚያ ላይ ደግሞ ማንም ሰው ቢሆን ሞኝ ተደርጎ እንዲቆጠር አይፈልግም። ታዲያ ፈጣሪ መኖሩን እርግጠኛ እንድትሆን ምን ሊረዳህ ይችላል?

 በምታምንበት ነገር ላይ ሊሰነዘር የሚችል ተቃውሞ

 1. ፈጣሪ እንዳለ የምታምን ከሆነ ሰዎች ሳይንስን እንደማትቀበል ይሰማቸዋል።

 “አስተማሪያችን፣ ‘ፈጣሪ እንዳለ የሚያምኑት፣ ዓለማችን እንዴት እንደመጣ ለመመርመር የሚሰንፉ ሰዎች ናቸው’ በማለት ተናገረች።”—ማሪያ

 ልታውቀው የሚገባ ነገር፦ እንዲህ ዓይነት አመለካከት ያላቸው ሰዎች ከግምት ውስጥ ያላስገቧቸው አንዳንድ እውነታዎች አሉ። እንደ አይዛክ ኒውተን እና ጋሊሊዮ ያሉ ታዋቂ የሳይንስ ባለሙያዎች ፈጣሪ መኖሩን ያምኑ ነበር። ይሁንና ፈጣሪ እንዳለ ማመናቸው ለሳይንስ ፍቅር እንዳይኖራቸው አላገዳቸውም። በዛሬው ጊዜም ፈጣሪ መኖሩን ማመን ከሳይንስ ጋር እንደማይጋጭ የሚያምኑ የሳይንስ ባለሙያዎች አሉ።

 እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ ፈጣሪ መኖሩን የሚያምኑ አንዳንድ የሕክምና እና የሳይንስ ባለሙያዎች የተናገሩትን ለማንበብ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍትን ክፈት፤ ከዚያም በፍለጋ ሣጥኑ ላይ “ስለምታምንበት ነገር ምን ትላለች” ወይም “ስለሚያምንበት ነገር ምን ይላል” ወይም “ስለሚያምኑበት ነገር ምን ይላሉ” የሚሉትን ሐረጎች (ትዕምርተ ጥቅሶቹን ጨምረህ) ጻፍ። እነዚህ ሰዎች በፈጣሪ እንዲያምኑ የረዳቸው ምን እንደሆነ የተናገሩትን ሐሳብ ልብ በል።

 ዋናው ነጥብ፦ ፈጣሪ እንዳለ ስላመንክ ብቻ ፀረ ሳይንስ ነህ ማለት አይደለም። እንዲያውም ስለ ተፈጥሮ ይበልጥ ስትማር ሁሉንም ነገር የፈጠረው አምላክ እንደሆነ ያለህ እምነት ይጠናከራል።—ሮም 1:20

2. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፍጥረት በሚናገረው ሐሳብ የምታምን ከሆነ ሰዎች አክራሪ ሃይማኖተኛ እንደሆንክ ይሰማቸዋል።

 “ብዙ ሰዎች፣ ፈጣሪ አለ ብሎ ማመን ቀልድ እንደሆነ ይሰማቸዋል። እነዚህ ሰዎች ‘በዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ የሚገኘው ሐሳብ ተረት ነው’ ብለው ያስባሉ።”—ጃዝሚን

 ልታውቀው የሚገባ ነገር፦ ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፍጥረት የሚናገረውን ሐሳብ የሚረዱበት መንገድ የተሳሳተ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በፍጥረት እናምናለን የሚሉ አንዳንድ ሰዎች (ክሪኤሽኒስቶች) ምድር ከተፈጠረች ብዙ ጊዜ እንዳልሆናት እንዲሁም ሕይወት ያላቸው ነገሮች የተፈጠሩት እያንዳንዳቸው የ24 ሰዓት ርዝመት ባላቸው ስድስት ቀናት ውስጥ እንደሆነ ይናገራሉ። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ ሁለቱንም ሐሳቦች አይደግፍም።

 •   ዘፍጥረት 1:1 “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ” በማለት ይናገራል። ይህ ሐሳብ፣ ምድር የተፈጠረችው በቢሊዮኖች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት እንደሆነ ከሚገልጸው ሳይንሳዊ ሐሳብ ጋር አይጋጭም።

 •   በዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ የተጠቀሰው “ቀን” የሚለው ቃል ረዘም ያለ ጊዜን ሊያመለክት ይችላል። እንዲያውም በዘፍጥረት 2:4 (የ1954 ትርጉም) ላይ “ቀን” የሚለው ቃል ስድስቱን የፍጥረት ቀናት በሙሉ ለማመልከት ተሠርቶበታል።

 ዋናው ነጥብ፦ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፍጥረት የሚናገረው ሐሳብ በሳይንስ ከተረጋገጡ እውነታዎች ጋር ይስማማል።

 ስለምታምንበት ነገር አስብ

 ፈጣሪ እንዳለ የምናምነው በጭፍን አይደለም። እንዲያውም እንዲህ ዓይነት እምነት ማመዛዘንን ይጠይቃል። እስቲ የሚከተለውን ሐሳብ ልብ በል፦

 በየቀኑ የምትመለከታቸው ነገሮች በሙሉ አንድ ንድፍ ካለ ያንን ንድፍ ያወጣ አካል እንደሚኖር ይጠቁማሉ። አንድን የፎቶ ካሜራ፣ አውሮፕላን ወይም ቤት ስትመለከት እነዚህን ነገሮች የሠራ ሰው እንዳለ ማሰብህ አይቀርም። ታዲያ ዓይናችንን፣ በሰማይ ላይ የምትበረውን ወፍ ወይም ምድርን የሠራ አካል የለም ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነው?

 ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ መሐንዲሶች በፍጥረታት ላይ የሚታዩትን ንድፎች በመመልከት በፈጠራ ሥራዎቻቸው ላይ አንዳንድ ማስተካከያዎችን ያደርጋሉ፤ ደግሞም ለፈጠራ ሥራዎቻቸው ተገቢው እውቅና እንዲሰጣቸው ይፈልጋሉ። ታዲያ ሰዎች ላከናወኑት የፈጠራ ሥራ እውቅና እየሰጠን ከሁሉ የተሻሉ ንድፎች ባለቤት ለሆነው አካል እውቅና አንሰጥም ብንል ተገቢ ይሆናል?

የአውሮፕላንን ንድፍ ያወጣ አንድ ሰው እንደሚኖር የታወቀ ነው፤ ታዲያ ወፎች፣ ንድፍ አውጪ እንደሌላቸው ማሰብ ምክንያታዊ ነው?

 ማስረጃዎቹን ለመመርመር የሚረዱህ መሣሪያዎች

 ተፈጥሮን በሚገባ በመመልከት ፈጣሪ እንዳለ ያለህን እምነት ማጠናከር ትችላለህ።

 እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍትን ክፈት፤ ከዚያም በፍለጋ ሣጥኑ ላይ “ንድፍ አውጪ አለው” የሚለውን ሐረግ (ትዕምርተ ጥቅሶቹን ጨምረህ) ጻፍ። በፍለጋ ውጤቱ ላይ ከሚመጡልህ “ንድፍ አውጪ አለው?” በሚለው ዓምድ ሥር የሚወጡ የንቁ! ርዕሶች መካከል አንተን የሚስቡህን ምረጥ። እነዚህን ርዕሶች ስታነብብ በርዕሱ ላይ የተብራራውን የተፈጥሮ ንድፍ አስደናቂ የሚያደርገው ምን እንደሆነ ለማሰብ ሞክር። በርዕሶቹ ላይ የተብራሩት ሐሳቦች ንድፍ አውጪ እንዳለ ያሳመኑህ እንዴት ነው?

 ይበልጥ ለማወቅ ሞክር፦ ፈጣሪ እንዳለ እርግጠኛ እንድትሆን የሚያደርጉ ማስረጃዎችን ጠለቅ ብለህ መመርመር የምትፈልግ ከሆነ የሚከተሉትን ብሮሹሮች አንብብ።

 •  ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ነው?

  •   ምድር በሕዋ ላይ የምትገኝበት ቦታ ሕይወት ያላቸው ነገሮችን ለማኖር ተስማሚ እንድትሆን አድርጓታል፤ እንዲሁም ለሕይወት የሚያስፈልጉ ነገሮችን በሙሉ በሚገባ ይዛለች።—ከገጽ 4-10 ተመልከት።

  •   በተፈጥሮ ላይ የምናያቸው ነገሮች ንድፍ አላቸው።—ከገጽ 11-17 ተመልከት።

  •   በዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ የሚገኘው ስለ ፍጥረት የሚገልጸው ዘገባ ከሳይንስ ጋር ይስማማል።—ከገጽ 24-28 ተመልከት።

 •  የሕይወት አመጣጥ—መልስ የሚያሻቸው አምስት ጥያቄዎች

  •   ሕይወት ያለው ነገር በአጋጣሚ ሕይወት ከሌላቸው ነገሮች ሊገኝ አይችልም።—ከገጽ 4-7 ተመልከት።

  •   ሕይወት ያላቸው ነገሮች በጣም ውስብስብ ናቸው፤ በመሆኑም በአጋጣሚ በተከናወነ አንድ ሂደት አማካኝነት ተሻሽለው የመጡ ሊሆኑ አይችሉም።—ከገጽ 8-12 ተመልከት።

  •   ዲ ኤን ኤ ያለው መረጃ የመያዝ ችሎታ ከየትኛውም ዘመናዊ የቴክኖሎጂ መሣሪያ ይበልጣል።—ከገጽ 13-21 ተመልከት።

  •   ሕይወት ያላቸው ነገሮች በሙሉ ከአንድ አካል እየተሻሻሉ አልመጡም። ከቅሪተ አካላት የተገኙ ማስረጃዎች እንደሚጠቁሙት ዋና ዋና የእንስሳት ምድቦች የተገኙት በአንድ ጊዜ ነው፤ ቅሪተ አካላቱ እነዚህ የእንስሳት ምድቦች አንዳቸው ከሌላው እየተሻሻሉ እንደመጡ አይጠቁሙም።—ከገጽ 22-29 ተመልከት።

 “አምላክ መኖሩን ያሳመነኝ ትልቁ ነገር በተፈጥሮ ላይ ያስተዋልኩት ነገር ነው፤ በምድር ላይ ያሉት እንስሳትም ሆኑ በጽንፈ ዓለም ውስጥ የሚታየው ሥርዓት ስለዚህ ጉዳይ እርግጠኛ እንድሆን አድርጎኛል።”—ቶማስ