በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

ፍጥረት ወይስ ዝግመተ ለውጥ?-ክፍል 2፦ ዝግመተ ለውጥ ትክክል መሆኑን ልትጠራጠር የሚገባው ለምንድን ነው?

ፍጥረት ወይስ ዝግመተ ለውጥ?-ክፍል 2፦ ዝግመተ ለውጥ ትክክል መሆኑን ልትጠራጠር የሚገባው ለምንድን ነው?

አሌክስ ግራ ተጋብቷል። አምላክ እንዳለና ሕይወት የተገኘው በፍጥረት እንደሆነ ያምናል። ዛሬ ግን የባዮሎጂ መምህሩ፣ ዝግመተ ለውጥ አሳማኝ ሳይንሳዊ ማስረጃ ያለው ሐቅ እንደሆነ አስረግጦ ተናገረ። አሌክስ ሞኝ ተደርጎ መታየት አልፈለገም። በመሆኑም እንዲህ ብሎ አሰበ፦ ‘የሳይንስ ሊቃውንት ዝግመተ ለውጥ እውነት እንደሆነ ካረጋገጡ እኔ ማን ሆኜ ነው የማልቀበለው?’

 አንተስ እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞህ ያውቃል? ምናልባት “እግዚአብሔር ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ” የሚለውን ሐሳብ ከልጅነትህ ጀምሮ ታምንበት ይሆናል። (ዘፍጥረት 1:1) ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በፍጥረት ማመን የተሳሳተ እንደሆነ፣ ዝግመተ ለውጥ ደግሞ የተረጋገጠ ሐቅ እንደሆነ አንዳንዶች ሊያሳምኑህ ሞክረው ሊሆን ይችላል። ታዲያ ልታምናቸው ይገባል? ዝግመተ ለውጥ ትክክል መሆኑን ልትጠራጠር የሚገባው ለምንድን ነው?

 ዝግመተ ለውጥ ትክክል መሆኑን እንድትጠራጠር የሚያደርጉ ሁለት ምክንያቶች

 1.   የሳይንስ ሊቃውንት ዝግመተ ለውጥን በተመለከተ እርስ በርሳቸው አይስማሙም። የሳይንስ ሊቃውንት ስለ ዝግመተ ለውጥ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ምርምር ቢያደርጉም ሁሉንም ሊያስማማ የሚችል ማብራሪያ ላይ መድረስ አልቻሉም።

   እስቲ አስበው፦ በጉዳዩ እውቀት አላቸው የሚባሉት የሳይንስ ሊቃውንት እንኳ ዝግመተ ለውጥን በተመለከተ አንድ ዓይነት ስምምነት ላይ መድረስ ካልቻሉ አንተ በዚህ ጽንሰ ሐሳብ ትክክለኛነት ላይ ጥያቄ ብታነሳ ምን ይደንቃል?—መዝሙር 10:4

 2.   የምታምነው ነገር በሕይወትህ ላይ ለውጥ ያመጣል። ዛካሪ የተባለ ወጣት እንዲህ ብሏል፦ “ሕይወት የተገኘው በአጋጣሚ ከሆነ የእኛ ሕይወትም ሆነ በጽንፈ ዓለም ውስጥ ያሉት ነገሮች በሙሉ ምንም ዓላማ የላቸውም ማለት ነው።” ይህ ወጣት የተናገረው ሐሳብ እውነት ነው። ደግሞስ ሕይወት የተገኘው በዝግመተ ለውጥ ከሆነ የመኖራችን ዓላማ ምንድን ነው? (1 ቆሮንቶስ 15:32) በሌላ በኩል ግን ሁሉም ነገር የተገኘው በፍጥረት ከሆነ ስለምንኖርበት ዓላማ እንዲሁም ስለ ወደፊቱ ጊዜ አስመልክቶ ለሚነሱብን ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ማግኘት እንችላለን።—ኤርምያስ 29:11

   እስቲ አስበው፦ ስለ ዝግመተ ለውጥ እና ስለ ፍጥረት እውነቱን ማወቅህ በሕይወትህ ላይ ለውጥ የሚያመጣው እንዴት ነው?—ዕብራውያን 11:1

 ሊታሰብባቸው የሚገቡ ጥያቄዎች

 የአንዳንዶች አመለካከት፦ ‘በጽንፈ ዓለም ውስጥ ያሉ ነገሮች በሙሉ የተገኙት ቢግ ባንግ ተብሎ በሚጠራ አንድ ድንገተኛ ፍንዳታ የተነሳ ነው።’

 •   ይህ ፍንዳታ እንዲካሄድ ያደረገው ማን ነው? ወይም ምንድን ነው?

 •   ይበልጥ ምክንያታዊ የሆነው የትኛው ነው? ሁሉም ነገር የተገኘው ከምንም እንደሆነ ማመን ነው ወይስ ሁሉንም ነገር ያስገኘ አንድ ነገር ወይም አካል እንዳለ አምኖ መቀበል?

 የአንዳንዶች አመለካከት፦ ‘የሰው ልጆች፣ ከእንስሳት በዝግመተ ለውጥ ተሻሽለው የመጡ ናቸው።’

 •   የሰው ልጆች የመጡት ከእንስሳት ለምሳሌ ያህል እንደ ዝንጀሮ ካሉ እንስሳት በዝግመተ ለውጥ ተሻሽለው ከሆነ በሰዎች እና በዝንጀሮዎች የማሰብ ችሎታ መካከል ይህን ያህል ልዩነት ሊኖር የቻለው እንዴት ነው? a

 •   ውስብስብ እንዳልሆኑ ተደርገው የሚቆጠሩ ሕይወት ያላቸው ነገሮች እንኳ እጅግ ሲበዛ ውስብስብ የሆኑት ለምንድን ነው? b

 የአንዳንዶች አመለካከት፦ ‘ዝግመተ ለውጥ እውነት መሆኑ በማስረጃ ተረጋግጧል።’

 •   እንዲህ ብሎ የተናገረው ሰው ራሱ ማስረጃውን መርምሯል?

 •   በትምህርታቸው የላቀ ደረጃ ላይ የደረሱ ሰዎች በሙሉ በዝግመተ ለውጥ እንደሚያምኑ ስለተነገራቸው ብቻ ይህን ትምህርት አምነው የሚቀበሉት ስንቶቹ ናቸው?

a በእርግጥ አንዳንድ ሰዎች፣ ዝንጀሮ መሰል የሆኑ እንስሳት እንደ እኛ ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ የሌላቸው የአንጎላቸው መጠን ከእኛ ስለሚያንስ እንደሆነ ይናገራሉ። ይሁንና ይህ የመከራከሪያ ነጥብ ትክክል አይደለም፤ እንዲህ የምንለው ለምን እንደሆነ ለማወቅ የሕይወት አመጣጥ—መልስ የሚያሻቸው አምስት ጥያቄዎች የተባለውን ብሮሹር ገጽ 28 ተመልከት።

b የሕይወት አመጣጥ—መልስ የሚያሻቸው አምስት ጥያቄዎች የተባለውን ብሮሹር ከገጽ 8-12 ተመልከት።