ፍጥረት ወይስ ዝግመተ ለውጥ?

አምላክ ሁሉንም ነገሮች እንደፈጠረ ታምናለህ? ከሆነ ብቻህን አይደለህም፤ ብዙ ወጣቶች እንዲሁም አዋቂዎች ተመሳሳይ አመለካከት አላቸው። በሌላ በኩል ደግሞ ሕይወትም ሆነ ጽንፈ ዓለም የተገኘው የፈጣሪ እጅ ሳይኖርበት በዝግመተ ለውጥ እንደሆነ የሚያምኑም አሉ።

ይህን ታውቅ ነበር? ብዙውን ጊዜ እንደሚታየው ሁለቱም ዓይነት አመለካከት ያላቸው ሰዎች በምን እንደሚያምኑ ከመናገር ባለፈ እንደዚያ ያመኑት ለምን እንደሆነ በእርግጠኝነት አያውቁም።

  • አንዳንድ ሰዎች ሕይወት በፍጥረት እንደተገኘ የሚያምኑት በቤተ ክርስቲያን እንደዚያ ተብለው ስለተማሩ ብቻ ነው።

  • ብዙ ሰዎች በዝግመተ ለውጥ የሚያምኑት በትምህርት ቤት እንደዚያ ተብለው ስለተማሩ ብቻ ነው።

እነዚህ ተከታታይ ርዕሶች፣ ሁሉ ነገር የመጣው በፍጥረት እንደሆነ ያለህን እምነት ማጠናከርና የምታምንበትን ነገር ለሌሎች ማስረዳት እንድትችል ይጠቅሙሃል። በመጀመሪያ ግን የሚከተለውን መሠረታዊ ጥያቄ ራስህን ጠይቅ፦

 አምላክ መኖሩን እንዳምን ያደረገኝ ምንድን ነው?

ይህን ጥያቄ መመለስህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ፣ አእምሮህን ይኸውም ‘የማሰብ ችሎታህን’ እንድትጠቀም ያበረታታል። (ሮም 12:1) በመሆኑም አምላክ መኖሩን የምታምነው በሚከተሉት ነገሮች ላይ የተነሳ መሆን የለበትም፦

  • ስሜት (እንዲሁ ከሰው የሚበልጥ አንድ አካል እንዳለ ይሰማኛል)

  • የሌሎች ተጽዕኖ (የምኖረው ሃይማኖተኛ በሆነ ማኅበረሰብ ውስጥ ነው)

  • ጫና (ወላጆቼ በአምላክ ማመን እንዳለብኝ ነግረውኛል፤ እንዲህ ባላደርግ ግን . . .)

ከዚህ ይልቅ አምላክ መኖሩን አንተ ራስህ ልታረጋግጥና ስለምታምንበት ነገር በቂ ምክንያት ሊኖርህ ይገባል።

አምላክ መኖሩን እንድታምን ያደረገህ ምንድን ነው? “አምላክ መኖሩን እንዳምን ያደረገኝ ምንድን ነው?” የሚለው የመልመጃ ሣጥን ስለምታምንበት ነገር እርግጠኛ እንድትሆን ይረዳሃል። በተጨማሪም ሌሎች ወጣቶች ለዚህ ጥያቄ የሰጡትን መልስ ማንበብህ ሊጠቅምህ ይችላል።

“ክፍል ውስጥ አስተማሪው ሰውነታችን ስለሚሠራበት መንገድ ሲያስረዳን አምላክ መኖሩን ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ሆንኩ። በጣም ትንሽ የሚመስሉትን ጨምሮ በሰውነታችን ውስጥ እያንዳንዱን ሥራ የሚያከናውኑ የአካላችን ክፍሎች አሉ፤ ብዙውን ጊዜ እነዚህ ሥራዎች የሚከናወኑት እኛ ሳናስተውለው ነው። የሰው አካል በእርግጥም አስደናቂ ነው!”—ቴሬዛ

“ሰማይ ጠቀስ ሕንፃ፣ ግዙፍ መርከብ ወይም መኪና ስመለከት ‘ይህን የሠራው ማን ነው?’ ብዬ ራሴን እጠይቃለሁ። ለምሳሌ መኪናን የሠሩት ማሰብ የሚችሉ የሰው ልጆች ናቸው፤ መኪናው መንቀሳቀስ እንዲችል በውስጡ ያሉት ትናንሽ ነገሮች በሙሉ በትክክል መሥራት መቻል አለባቸው። አንድ መኪና ንድፍ አውጪ ካስፈለገው እኛ የሰው ልጆች የተሠራንበት መንገድም ያው ነው።”—ሪቻርድ

“ብሩህ አእምሮ ያላቸው ሰዎች እንኳ ለብዙ መቶ ዓመታት ምርምር በማድረግ ስለ ጽንፈ ዓለም ማወቅ የቻሉት ነገር በጣም አነስተኛ ነው፤ ከዚህ አንጻር፣ ጽንፈ ዓለም የመጣው የማሰብ ችሎታ ያለው አካል ሳይፈጥረው ነው ብሎ ማሰብ ጨርሶ ምክንያታዊ አይደለም!”—ካረን

“ስለ ሳይንስ ይበልጥ በተማርኩ ቁጥር ዝግመተ ለውጥ ሊታመን የሚችል አለመሆኑን ይበልጥ እየተረዳሁ መጣሁ። ለምሳሌ ያህል፣ በተፈጥሮ ላይ የሚታዩት ንድፎች በሒሳብ ስሌት ቢቀመጡ ዝንፍ የማይሉ መሆናቸውን አስባለሁ፤ እንዲሁም የሰው ልጆች ከሌሎች ፍጥረታት በተለየ መልኩ ማን እንደሆኑ፣ ከየት እንደመጡና ስለ ወደፊቱ ጊዜ የማወቅ ጉጉት ያላቸው መሆኑ ያስገርመኛል። ዝግመተ ለውጥ እነዚህን ነገሮች ለማብራራት የሰው ልጆችን ከእንስሳት ጋር አያይዞ ይገልጽ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ የሰው ልጆች ልዩ የሆኑበትን ምክንያት ማብራራት አልቻለም። እንደ እኔ እንደ እኔ፣ ይበልጥ ‘እምነት’ የሚጠይቀው በዝግመተ ለውጥ ማመን እንጂ በፈጣሪ ማመን አይደለም።”—አንቶኒ

 የማምንበትን ነገር ማስረዳት የምችልበት መንገድ

አብረውህ የሚማሩ ልጆች ‘እንዴት በማታየው ነገር ታምናለህ?’ ብለው ቢያሾፉብህስ? ዝግመተ ለውጥ በሳይንስ “የተረጋገጠ” ሐቅ እንደሆነ ቢነግሩህስ?

በመጀመሪያ ደረጃ፣ ስለምታምንበት ነገር እርግጠኛ ሁን። መሸማቀቅ ወይም መፍራት የለብህም። (ሮም 1:16) ደግሞም የሚከተሉትን ነጥቦች አትዘንጋ፦

  1. እንዲህ ብለህ የምታምነው አንተ ብቻ አይደለህም፤ ብዙ ሰዎች አምላክ መኖሩን ያምናሉ። ከእነዚህም መካከል በሙያቸው የላቁ የተማሩ ሰዎች ይገኙበታል። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ መኖሩን የሚያምኑ የሳይንስ ሊቃውንት አሉ።

  2. ሰዎች አምላክ መኖሩን እንደማያምኑ የሚናገሩት ስለ እሱ መረዳት ያልቻሉት ነገር ስላለ ይሆናል። እነዚህ ሰዎች ስለሚያምኑበት ነገር ማስረጃ ከማቅረብ ይልቅ እንደሚከተለው ያሉ ጥያቄዎችን ያነሳሉ፦ “አምላክ ካለ፣ መከራ ሲደርስ ዝም ብሎ የሚመለከተው ለምንድን ነው?” በመሆኑም እነዚህ ሰዎች ጉዳዩን የሚመለከቱት ከሳይንሳዊ ማስረጃ አንጻር አይደለም።

  3. የሰው ልጆች “መንፈሳዊ” ፍላጎት አላቸው። (ማቴዎስ 5:3) ሰዎች በአምላክ የማመን ፍላጎት አላቸው። በመሆኑም አንድ ሰው አምላክ እንደሌለ ቢነግርህ ስለደረሰበት መደምደሚያ ማብራሪያ መስጠት ያለበት እሱ እንጂ አንተ አይደለህም።ሮም 1:18-20

  4. አምላክ መኖሩን ማመን ምክንያታዊ ነው። ሕይወት ያለው ነገር በራሱ ሊመጣ እንደማይችል ከሚገልጸው የተረጋገጠ ሐቅ ጋር ይስማማል። ሕይወት ያለው ነገር፣ ሕይወት ከሌለው ነገር እንደመጣ የሚገልጸው ሐሳብ በማስረጃ ሊረጋገጥ አልቻለም።

ታዲያ አንድ ሰው በአምላክ መኖር በማመንህ ላይ ጥያቄ ቢያነሳ ምን ብለህ ልትመልስለት ትችላለህ? አንዳንድ አማራጮችን እስቲ እንመልከት።

አንድ ሰው እንዲህ ቢልህ፦ “አምላክ እንዳለ የሚያምኑት ያልተማሩ ሰዎች ብቻ ናቸው።”

እንዲህ ብለህ ልትመልስለት ትችላለህ፦ “ይህ አመለካከት እውነታውን ያገናዘበ እንደሆነ አይሰማኝም። እንዲያውም በተለያዩ እውቅ ዩኒቨርሲቲዎች በሚሠሩ ከ1,600 በሚበልጡ የሳይንስ ፕሮፌሰሮች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳሳየው አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት በአምላክ መኖር እንደማያምኑ ወይም መኖሩን እንደሚጠራጠሩ አልገለጹም። * እነዚህ ፕሮፌሰሮች አምላክ መኖሩን በማመናቸው ብቻ ያልተማሩ ናቸው ትላለህ?”

አንድ ሰው እንዲህ ቢልህ፦ “አምላክ ካለ፣ መከራ ሲደርስ ዝም ብሎ የሚመለከተው ለምንድን ነው?”

እንዲህ ብለህ ልትመልስለት ትችላለህ፦ “ምናልባት እንዲህ ያልከው አምላክ የሚያደርገውን ነገር ስላልተረዳህ ይኸውም እስካሁን ለምን እርምጃ እንዳልወሰደ ግልጽ ስላልሆነልህ ይሆናል። ትክክል ነኝ? [ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው።] ዛሬ በሰው ልጆች ላይ የሚደርሰው መከራ ይህን ያህል የበዛው ለምን እንደሆነ አጥጋቢ መልስ አግኝቻለሁ። ይሁን እንጂ መልሱን ለመረዳት አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን መመርመር አስፈላጊ ነው። ታዲያ ስለዚህ ጉዳይ ይበልጥ ማወቅ ትፈልጋለህ?”

ቀጣዩ ርዕስ፣ የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ እኛ ስለተገኘንበት መንገድ አጥጋቢ መልስ አይሰጥም የምንለው ለምን እንደሆነ ያብራራል።

^ አን.32 ምንጭ፦ Social Science Research Council, “Religion and Spirituality Among University Scientists,” by Elaine Howard Ecklund , February 5, 2007