በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

ፆታዊ ትንኮሳ ቢያጋጥመኝ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?

ፆታዊ ትንኮሳ ቢያጋጥመኝ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?

 ፆታዊ ትንኮሳ ምንድን ነው?

 ፆታዊ ትንኮሳ፣ አንቺ a ሳትፈልጊ የሚደረግ ማንኛውም ዓይነት ከፆታ ጋር የተያያዘ ነገር ነው፤ ይህም ሰውነትሽን መንካትን ሌላው ቀርቶ ከፆታ ግንኙነት ጋር የተያያዘ ሐሳብ መሰንዘርን ጭምር ያካትታል። ይሁንና አንዳንድ ጊዜ በቀልድ፣ በማሽኮርመም እና በፆታዊ ትንኮሳ መካከል ያለውን ልዩነት ማወቅ ሊያስቸግር ይችላል።

 ታዲያ ፆታዊ ትንኮሳ ከማሽኮርመም ወይም ከቀልድ የሚለየው እንዴት ነው? መልሱን ለማግኘት  ፆታዊ ትንኮሳ—ጥያቄዎች የሚለውን መልመጃ ሥሪ!

 የሚያሳዝነው ነገር፣ ፆታዊ ትንኮሳ ትምህርት ከጨረስሽ በኋላም ሊቀጥል ይችላል። ያም ቢሆን ፆታዊ ትንኮሳ ሲያጋጥምሽ ምን ማድረግ እንዳለብሽ ከተገነዘብሽ እንዲሁም በራስ የመተማመን መንፈስ ከአሁኑ ካዳበርሽ ወደፊት በሥራው ዓለም የሚያጋጥምሽን ነገር ለመቋቋም ዝግጁ ትሆኛለሽ። አልፎ ተርፎም አንቺን የሚያስቸግርሽ ሰው በሌሎች ሰዎችም ላይ ትንኮሳ እንዳያደርስ ማድረግ ትችዪ ይሆናል!

 የሚደርስብኝን ፆታዊ ትንኮሳ ለማስቆም ምን ላድርግ?

 ፆታዊ ትንኮሳ የሚባለው ምን እንደሆነ ለይተሽ ካወቅሽ እንዲሁም እንዲህ ላለው ትንኮሳ ምን ምላሽ መስጠት እንዳለብሽ ከተረዳሽ አብዛኛውን ጊዜ ጥቃቱ ማስቆም ትችያለሽ። እስቲ ሦስት ምሳሌዎችን እንውሰድና በእያንዳንዱ ሁኔታ ምን እርምጃ ልትወስጂ እንደምትችዪ እንመልከት።

 ምሳሌ፦

“በሥራ ቦታ፣ በዕድሜ በጣም የሚበልጡኝ አንዳንድ ወንዶች ቆንጆ እንደሆንኩና ‘የዛሬ 30 ዓመት ባገኛት ኖሮ’ ብለው እንደሚቆጩ ይነግሩኛል። እንዲያውም አንዱ ከኋላዬ ተጠግቶ ፀጉሬን አሸተተው!”​—ታቢታ፣ 20

 ታቢታ እንዲህ ብላ ልታስብ ትችላለች፦ ‘ድርጊቱን አይቼ እንዳላየሁ ችላ ብዬ ባልፈው ይተው ይሆናል።’

 እንዲህ ብላ ማሰቧ መፍትሔ ላይሆን የሚችልበት ምክንያት፦ የፆታዊ ትንኮሳ ሰለባዎች ሁኔታውን ችላ ሲሉት ብዙውን ጊዜ ትንኮሳው እንደማያቆም አልፎ ተርፎም እንደሚባባስ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

 እንዲህ ማድረጉ የተሻለ ነው፦ ፆታዊ ትንኮሳ ላደረሰብሽ ሰው፣ ሁለተኛ እንደዚያ ብሎ እንዳይናገርሽ ወይም እንዲህ እንዳያደርግ በተረጋጋ ሆኖም ጠንከር ባለ መንገድ ንገሪው። የ22 ዓመቷ ታሪን እንዲህ ብላለች፦ “አንድ ሰው ተገቢ ባልሆነ መንገድ ከነካኝ፣ ከአሁን በኋላ ጫፌን ንክች እንዳያደርገኝ እነግረዋለሁ። ብዙውን ጊዜ ወንዶቹ እንዲህ ሲባሉ ይበረግጋሉ።” ግለሰቡ ትንኮሳውን አላቆም ቢልም አንቺ ተስፋ ሳትቆርጪ በአቋምሽ ጽኚ። “ጸንታችሁ ቁሙ፣ አትነቃነቁ” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ፣ ላቅ ያለ የሥነ ምግባር አቋም ከመያዝ ጋር በተያያዘም ይሠራል።​—1 ቆሮንቶስ 15:58

 ይሁንና ፆታዊ ትንኮሳ የሚያደርስብሽ ሰው ቢያስፈራራሽ ወይም ቢዝትብሽስ? ሁኔታው እንዲህ ከሆነ እሱን አለመጋፈጡ የተሻለ ይሆናል። በተቻለ ፍጥነት ከእሱ ለመራቅ ሞክሪ፤ ከዚያም የምታምኚው ሰው እርዳታ እንዲያደርግልሽ ጠይቂ።

 ምሳሌ፦

“ስድስተኛ ክፍል ሳለሁ ሁለት ሴቶች ኮሪደር ላይ ያዙኝ። አንደኛዋ ግብረ ሰዶማዊ ስለነበረች አብሬያት እንድወጣ ፈልጋ ነበር። ይህን ማድረግ እንደማልፈልግ ብነግራቸውም በየቀኑ፣ አስተማሪ በማይኖርበት ጊዜ ሁሉ ያስቸግሩኝ ነበር። እንዲያውም አንድ ቀን ከግድግዳው ጋ አጣበቁኝ።”​—ቪክቶሪያ፣ 18

 ቪክቶሪያ እንዲህ ብላ ልታስብ ትችላለች፦ ‘ያጋጠመኝን ነገር ብናገር እንደ ፈሪ እታያለሁ፤ እንዲሁም ማንም ላያምነኝ ይችላል።’

 እንዲህ ብላ ማሰቧ መፍትሔ ላይሆን የሚችልበት ምክንያት፦ የደረሰብሽን ነገር ለሌላ ሰው ካልተናገርሽ፣ ፆታዊ ትንኮሳ ያደረሰብሽ ሰው አንቺን ማስቸገሩን ሊቀጥል አልፎ ተርፎም ሌሎች ላይ ተመሳሳይ ነገር ሊያደርግ ይችላል።​—መክብብ 8:11

 እንዲህ ማድረጉ የተሻለ ነው፦ እርዳታ ጠይቂ። ወላጆችሽና አስተማሪዎችሽ ትንኮሳውን ለማስቆም ሊረዱሽ ይችላሉ። ይሁንና እርዳታ የምትጠይቂያቸው ሰዎች የደረሰብሽን ነገር አክብደው ባይመለከቱትስ? እንዲህ ለማድረግ ሞክሪ፦ ፆታዊ ትንኮሳ ሲደርስብሽ ሁኔታውን በዝርዝር ጻፊው። ይህም ቀኑን፣ ሰዓቱን፣ ቦታውን እንዲሁም ትንኮሳ ያደረሰብሽ ሰው የተናገረውን ነገር ይጨምራል። ከዚያም የጻፍሽውን ነገር ለወላጅሽ ወይም ለአስተማሪሽ ስጪው። ብዙ ሰዎች በቃል ከምትነግሪያቸው ይልቅ በጽሑፍ ለምትሰጪያቸው ነገር ክብደት ይሰጣሉ።

 ምሳሌ፦

“በስፖርት ቡድን ውስጥ ያለ አንድ በጣም የሚያስፈራኝ ልጅ ነበር። ቁመቱ ሁለት ሜትር ገደማ ሲሆን ክብደቱ ደግሞ 135 ኪሎ ግራም ገደማ ይሆናል! እንደ ምንም ብሎ ከእኔ ጋር የፆታ ግንኙነት ለመፈጸም ቆርጦ ነበር። አንድ ዓመት ሙሉ በየቀኑ ያስቸግረኝ ነበር። አንድ ቀን ክፍል ውስጥ ያለነው እኔና እሱ ብቻ ነበርን፤ ከዚያም ወደ እኔ መምጣት ጀመረ። በዚህ ጊዜ ከተቀመጥኩበት ዘልዬ በመነሳት እየሮጥኩ ወጣሁ።”​—ጁሊዬታ፣ 18

 ጁሊዬታ እንዲህ ብላ ልታስብ ትችላለች፦ ‘ወንዶች ሲባሉ እንዲህ ናቸው።’

 እንዲህ ብላ ማሰቧ መፍትሔ ላይሆን የሚችልበት ምክንያት፦ ፆታዊ ትንኮሳ የሚያደርስ ሰው፣ ድርጊቱ ተገቢ እንዳልሆነ የሚነግረው ከሌለ ይህን ማድረጉን አያቆምም።

 እንዲህ ማድረጉ የተሻለ ነው፦ ጉዳዩን ቀልደሽ ለማለፍ አትሞክሪ፤ ወይም ደግሞ መልስ የምትሰጪው ፈገግ ብለሽ መሆን የለበትም። ከዚህ ይልቅ የምትሰጪው ምላሽና በፊትሽ ላይ የሚነበበው ነገር ድርጊቱን ፈጽሞ እንደማትቀበዪው በግልጽ የሚያሳይ መሆን አለበት።

 ፆታዊ ትንኮሳ ቢደርስብኝ ምን አደርጋለሁ?

 እውነተኛ ታሪክ 1፦

“ሰዎችን ማስከፋት አልወድም። ስለዚህ ወንዶች ፆታዊ ትንኮሳ ሲያደርሱብኝ እንኳ እንዲያቆሙ የምነግራቸው ጠንከር ብዬ አይደለም፤ እንዲያውም ብዙ ጊዜ ሳናግራቸው ፊቴ ላይ ፈገግታ ይታያል። በመሆኑም እየተሽኮረመምኩ ያለሁ ይመስላቸዋል።”—ታቢታ

  •   በታቢታ ቦታ ብትሆኚ ኖሮ ትንኮሳ ለሚያደርሱብሽ ሰዎች ምን ምላሽ ትሰጪ ነበር? ለምን?

  •   ፆታዊ ትንኮሳ የሚያደርስብሽ ሰው እየተሽኮረመምሽ እንዳለ እንዲሰማው የሚያደርገው ምን ሊሆን ይችላል?

 እውነተኛ ታሪክ 2፦

“በስፖርት ክፍለ ጊዜ ላይ አንዳንድ ወንዶች የብልግና ነገር ይናገሩኝ ጀመር። ለተወሰኑ ሳምንታት፣ የሚሉትን እንዳልሰማሁ ሆኜ ለማለፍ ሞከርኩ፤ ልጆቹ ግን እየባሰባቸው መጣ። ከዚያም አጠገቤ መቀመጥ የጀመሩ ሲሆን ሊያቅፉኝ ይሞክሩ ነበር። ብገፈትራቸውም እንደዚያ ማድረጋቸውን አላቆሙም። በመጨረሻም አንዱ ልጅ፣ ብልግና ነገር የተጻፈበት ወረቀት ሰጠኝ። እኔም ወረቀቱን ለአስተማሪዬ ሰጠሁት። ልጁ ለተወሰነ ጊዜ ትምህርት ቤት እንዳይመጣ ታገደ። ይህን ሳይ፣ ጉዳዩን ገና ከመጀመሪያው ለአስተማሪዬ መናገር እንደነበረብኝ ተገነዘብኩ!”—ሳቢና

  •   ሳቢና ወደ አስተማሪዋ ቀደም ብላ ያልሄደችው ለምን ይመስልሻል? የወሰደችው እርምጃ ትክክል ይመስልሻል? እንዲህ ብለሽ የመለስሽው ለምንድን ነው?

 እውነተኛ ታሪክ 3፦

“ወንድሜ ግሬግ መጸዳጃ ቤት እያለ አንድ ልጅ ወደ እሱ በጣም ተጠግቶ ‘ሳመኝ’ አለው። ግሬግ እምቢ ቢለውም ልጁ ግን ሊገባው አልቻለም። ግሬግ ከልጁ ለመላቀቅ ሲል ገፍትሮት ወጣ።”—ሱዛን

  •   ግሬግ ያጋጠመው ነገር ፆታዊ ትንኮሳ ነው? ለምን?

  •   አንዳንድ ወንዶች፣ ሌላ ወንድ ፆታዊ ትንኮሳ ሲያደርስባቸው ጉዳዩን ከመናገር ወደኋላ የሚሉት ለምንድን ነው?

  •   ግሬግ የወሰደው እርምጃ ትክክል ነው? አንተ ብትሆን ምን ታደርግ ነበር? (አንቺ ብትሆኚ ምን ታደርጊ ነበር?)

a በዚህ ርዕስ ውስጥ ፆታዊ ትንኮሳ ስለሚደርስባቸው ሰዎች ስንናገር በአንስታይ ፆታ የተጠቀምን ቢሆንም የቀረቡት ነጥቦች ለሁለቱም ፆታዎች ይሠራሉ።