በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

ጥሩ ውጤት ማምጣት የምችለው እንዴት ነው?

ጥሩ ውጤት ማምጣት የምችለው እንዴት ነው?

ምን ማድረግ ትችላለህ?

አዎንታዊ አመለካከት ይኑርህ! ማሻሻያ ማድረግ እንደማትችል ማሰብህ በትምህርትህ ጥሩ ውጤት እንዳታመጣ እንቅፋት ስለሚሆንብህ እንዲህ ያለውን አመለካከት አስወግድ። ‘ችሎታ የለኝም’ የሚል አፍራሽ አመለካከት ሲመጣብህ አዎንታዊ ነገሮችን ለማሰብ ሞክር። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ሰዎች በጳውሎስ የመናገር ችሎታ ላይ ትችት (መሠረት የሌለው ሊሆን ይችላል) በሰነዘሩበት ወቅት ሐዋርያው እንዲህ የሚል ምላሽ ሰጥቷል፦ “የተዋጣልኝ ተናጋሪ ባልሆን እንኳ እውቀት የሚጎድለኝ ግን አይደለሁም።” (2 ቆሮንቶስ 10:10፤ 11:6) ጳውሎስ ያሉበትን ድክመቶች ተገንዝቦ ነበር። ይሁንና ጠንካራ ጎኖችም እንዳሉት ያውቅ ነበር። አንተስ? ምን ጠንካራ ጎኖች አሉህ? ጠንካራ ጎኖች እንደሌሉህ ከተሰማህ ስለ አንተ ለሚያስብ አንድ ትልቅ ሰው ስለዚህ ጉዳይ ለምን ጥያቄ አታቀርብለትም? እንዲህ ያለው ወዳጅ ጠንካራ ጎኖችህን ለይተህ እንድታውቅና በደንብ እንድትጠቀምባቸው ሊረዳህ ይችላል።

ጥሩ የጥናት ልማድ አዳብር። በትምህርት ቤት ውጤታማ ለመሆን አቋራጭ መንገድ የለውም። በዚያም ሆነ በዚህ ማጥናት ይኖርብሃል። እርግጥ ነው፣ ማጥናት የሚለው ሐሳብ ገና ሲነሳ ጭንቅ ይልህ ይሆናል። ይሁን እንጂ ጥናት ጠቃሚ ነገር ነው። እንዲያውም የተወሰነ ጥረት ካደረግህ ጥናት አስደሳች ሊሆንልህ ይችላል። እርግጥ ነው፣ ጥሩ የጥናት ልማድ ለማዳበር ጊዜህን በፕሮግራም መጠቀም ያስፈልግሃል። ተማሪ እስከሆንክ ድረስ ቅድሚያ ልትሰጠው የሚገባው ነገር ጥናት እንደሆነ አስታውስ። እውነት ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ “ለመሣቅም ጊዜ አለው . . . ለጭፈራም ጊዜ አለው” ይላል። (መክብብ 3:1, 4፤ 11:9) ብዙ ወጣቶች እንደሚያደርጉት አንተም ለመዝናኛ ጊዜ መመደብ ትፈልግ ይሆናል። ይሁንና “ነፋስን የሚጠባበቅ አይዘራም፤ ደመናትንም የሚያይ አያጭድም” የሚለውን በመክብብ 11:4 ላይ የሚገኘውን ማሳሰቢያ ልብ ማለት ይገባሃል። ከዚህ የምታገኘው ትምህርት ምንድን ነው? ዛሬ ነገ የማለት ልማድ አይኑርህ። አለዚያ አስፈላጊ ነገሮችን ሳታከናውን ትቀራለህ። ጥናት ከጨዋታ ሊቀድም ይገባል። በዚህ ረገድ ሐሳብ አይግባህ፤ ለሁለቱም ጊዜ ማግኘት ትችላለህ!

ክብደት ማንሳት አካላዊ ጥንካሬህን እንደሚያሻሽለው ሁሉ ጥሩ የጥናት ልማድ ማዳበርም የትምህርት ውጤትህን ያሻሽለዋል