በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

ጓደኛ የሌለኝ ለምንድን ነው?

ጓደኛ የሌለኝ ለምንድን ነው?

ቅርብ ጊዜ በተደረገ አንድ ግብዣ ላይ ጓደኞችህ የተነሷቸውን ፎቶዎች ኢንተርኔት ላይ እየተመለከትህ ነው። ሁሉም ጓደኞችህ ግብዣው ላይ የተገኙ ከመሆኑም ሌላ ደስ የሚል ጊዜ አሳልፈዋል። ፎቶዎቹን ስትመለከት ቅር አለህ። አንተ ግብዣው ላይ አልነበርህም።

‘ለምንድን ነው ግብዣው ላይ ያልተጠራሁት?’ ብለህ ታስባለህ።

ቁጭ ብለህ ይህን እያሰብህ ስትብሰለሰል ማዘን ትጀምራለህ። ሁሉም ሰው እንደተወህ ይሰማሃል! ከሰዎች ጋር ያለህ ጓደኝነት ልክ ነፋስ እንደበተነው ገለባ ብትንትኑ እንደወጣ ታስብ ይሆናል። በዚህ ጊዜ በብቸኝነት ስሜት ስለምትዋጥ ‘ጓደኛ የሌለኝ ለምንድን ነው?’ ብለህ ታስባለህ።

 ብቸኝነት—ጥያቄዎች

 እውነት ወይም ሐሰት

 1.   ብዙ ጓደኞች ካሉህ መቼም ቢሆን ብቸኝነት አይሰማህም።

 2.   የማኅበራዊ ድረ ገጽ ተጠቃሚ ከሆንህ በፍጹም ብቸኝነት አይሰማህም።

 3.   ብዙ የጽሑፍ መልእክቶችን በሞባይል የምትለዋወጥ ከሆነ በፍጹም ብቸኝነት አይሰማህም።

 4.   ለሌሎች ጥሩ ነገር የምታደርግ ከሆነ በፍጹም ብቸኝነት አይሰማህም።

 የአራቱም ዓረፍተ ነገሮች መልስ ሐሰት የሚል ነው።

 ለምን?

 ብቸኝነት—እውነታው ምንድን ነው?

 •   ብዙ ጓደኞች ቢኖሩህም እንኳ ብቸኝነት ሊሰማህ ይችላል።

   “እኔ ጓደኞቼን እወዳቸዋለሁ፤ አንዳንድ ጊዜ ግን እኔ ለእነሱ የሚሰማኝን ያህል እንደማይወዱኝ ይሰማኛል። ጓደኞችህ እንደማይወዱህ ወይም ቦታ እንደማይሰጡህ የሚሰማህ ከሆነ በብዙ ጓደኞች ብትከበብም እንኳ በብቸኝነት ስሜት መዋጥህ አይቀርም።”አን

 •   የማኅበራዊ ድረ ገጽ ተጠቃሚ ብትሆንም እንኳ ብቸኝነት ሊሰማህ ይችላል።

   “አንዳንድ ሰዎች ከጓደኞቻቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት አሻንጉሊቶችን መሰብሰብ የሚወዱ ሰዎች ከሚያደርጉት ነገር ጋር ይመሳሰላል። እነዚህ ሰዎች ብዙ አሻንጉሊቶች ቢኖሯቸውም አሻንጉሊቶቻቸው፣ እንደሚወደዱ እንዲሰማቸው ሊያደርጉ እንደማይችሉ የታወቀ ነው። ኢንተርኔት ላይ ከምታገኛቸው ጓደኞችህ ጋር ያለህ ግንኙነት የጠበቀ ካልሆነ ሕይወት ከሌላቸው ከእነዚህ አሻንጉሊቶች የተሻለ ነገር ሊያደርጉልህ አይችሉም።”ኢሌይን

 •   ከሌሎች ጋር የጽሑፍ መልእክት በመለዋወጥ ብዙ ጊዜ ብታሳልፍም እንኳ ብቸኝነት ሊሰማህ ይችላል።

   “አንዳንድ ጊዜ ብቸኝነት ይሰማህና መልእክት ተልኮልህ እንደሆነ ለማየት አሥር ጊዜ ስልክህን ትመለከታለህ። ማንም መልእክት እንዳልላከልህ ስትመለከት የበለጠ ብቸኝነት ይሰማሃል!”ሴሪና

 •   ለሌሎች ጥሩ ነገር ብታደርግም እንኳ ብቸኝነት ሊሰማህ ይችላል።

   “ለጓደኞቼ ብዙ ነገር አደርጋለሁ፤ እነሱ ግን ለእኔ እንደዚያ እንደማያደርጉ ይሰማኛል። ለእነሱ መልካም በማድረጌ ባልቆጭም አንዴም እንኳ በምላሹ ደግነት እንዳላሳዩኝ ሳስብ ትንሽ ይከፋኛል።”ሪቻርድ

 ዋናው ነጥብ፦ ዞሮ ዞሬ ብቸኝነት ከአመለካከታችን ጋር የተያያዘ ነው። ጃኔት የተባለች ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “ብቸኝነት ከውስጥህ የሚመጣ ነገር እንጂ ከውጭ ባሉ ነገሮች ላይ የተመካ አይደለም።

 ጓደኛ እንደሌለህና ብቸኛ እንደሆንህ የሚሰማህ ከሆነ ምን ልታደርግ ትችላለህ?

 መቋቋም የሚቻለው እንዴት ነው?

በራስ የመተማመን ስሜት ይኑርህ።

 “አንድ ሰው ብቸኝነት የሚሰማው በራሱ ስለማይተማመን ሊሆን ይችላል። የሰዎችን ፍቅር ለማግኘት የማትበቃ ሰው እንደሆንህ የምታስብ ከሆነ ከሌሎች ጋር ጓደኝነት መመሥረት ከባድ ይሆንብሃል።”ጃኔት

 መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ።” (ገላትያ 5:14) ከሌሎች ጋር ጥሩ ጓደኝነት ለመመሥረት በተወሰነ መጠንም ቢሆን ለራሳችን ጥሩ አመለካከት ሊኖረን ይገባል፤ እርግጥ ነው፣ ከልክ በላይ ራሳችንን የምንወድድ እንሆናለን ማለት አይደለም።—ገላትያ 6:3, 4

ስለ ራስህ ችግር ብቻ እያሰብህ አትተክዝ።

 “ብቸኝነት፣ ስትቆምበት ይዞህ እየሰመጠ እንደሚሄድ አሸዋ ነው። ስለ ብቸኝነትህ ብቻ እያሰብህ የምትቆዝም ከሆነ ከዚያ ለመውጣት አስቸጋሪ እየሆነብህ ይሄዳል። ሁልጊዜ ስለ ራስህ ችግር ብቻ የምታስብ ከሆነ ሌሎችም ወደ አንተ መቅረብ አይፈልጉም፤ ይህ ደግሞ ይበልጥ ብቸኝነት እንዲሰማህ ያደርጋል።”ኤሪን

 መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ፍቅር . . . የራሱን ፍላጎት አያስቀድምም።” (1 ቆሮንቶስ 13:4, 5) እውነቱን ለመናገር ሁልጊዜ የሚያሳስበን የራሳችን ችግር ብቻ ከሆነ ለሌሎች አዛኝ መሆናችንን እየተውን እንሄዳለን፤ እንዲህ ዓይነት ሰዎች ከሆንን ደግሞ ሰዎች ከእኛ እየራቁ መሄዳቸው አይቀርም። (2 ቆሮንቶስ 12:15) ለማንኛውም ሐቁ ይህ ነው፦ የአንተ ደስታ ወይም ስኬታማ መሆን የተመካው ሌሎች በሚያደርጉልህ ነገር ላይ ከሆነ ያሰብከው ባለመሳካቱ ማዘንህ እንደማይቀር እወቅ! “ስልክ ሊደውልልኝ የሚፈልግ ሰው የለም” ወይም “ማንም ግብዣው ላይ ሊጠራኝ አይፈልግም” እያልክ የምታስብ ከሆነ ደስታህ በሌሎች ላይ የተመካ እንዲሆን እያደረግህ ነው። ታዲያ እንዲህ ስታደርግ ሌሎች ከመጠን በላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድሩብህ መፍቀድህ አይደለም?

ጓደኛ ለማግኘት ካለህ ጉጉት የተነሳ አጉል ከሆኑ ሰዎች ጋር ወዳጅነት እንዳትመሠርት ተጠንቀቅ።

 “ብቸኝነት የሚሰማቸው ሰዎች ሌሎች ትኩረት እንዲሰጧቸው ይፈልጋሉ፤ ሆኖም ትኩረት ለማግኘት ካላቸው ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳ ማንኛውም ሰው ትኩረት ቢሰጣቸው ደስተኞች ሊሆኑ ይችላሉ። ተፈላጊ እንደሆኑ እንዲሰማቸው ከሚያደርግ ማንኛውም ሰው ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት ፈቃደኛ ናቸው። ይሁን እንጂ አንዳንድ ሰዎች ተፈላጊ እንደሆንህ እንዲሰማህ የሚያደርጉት መጠቀሚያ ሊያደርጉህ ፈልገው ይሆናል። ይህ ሁኔታ ሲያጋጥምህ ደግሞ ከበፊቱ የበለጠ ብቸኝነት ይሰማሃል።”ብሪያን

 መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ከጠቢብ ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የተላሎች ባልንጀራ ግን ጕዳት ያገኘዋል።” (ምሳሌ 13:20) አንድ ሰው ሲርበው ያገኘውን ነገር ሁሉ ሊበላ ይችላል። በተመሳሳይም ጓደኛ የሌላቸው ሰዎች ጓደኛ ለማግኘት ካላቸው ፍላጎት የተነሳ ጥሩ ካልሆኑ ሰዎች ጋር ወዳጅነት ሊመሠርቱ ይችላል። የተሻለ ጓደኛ ማግኘት እንደማይችሉ እንዲሁም ከማንኛውም ሰው ጋር ጓደኝነት ቢመሠርቱ ችግር እንደሌለው ስለሚያስቡ መጠቀሚያ ሊያደርጓቸው የሚፈልጉ ሰዎች እጅ ላይ በቀላሉ ይወድቁ ይሆናል።

 ማጠቃለያ፦ መጠኑ ከሰው ወደ ሰው ይለያይ እንጂ ሁላችንም ብቸኝነት የሚሰማን ጊዜ ይኖራል። ብቸኝነት ስሜታችንን ሊጎዳው ቢችልም የብቸኝነት ስሜትም እንደ ሌሎች ስሜቶቻችን ነው። ብዙውን ጊዜ ስሜታችን ስለ አንድ ነገር ባለን አመለካከት ላይ የተመካ ነው፤ አስተሳሰባችንን መቆጣጠር ደግሞ እንችላለን።

 ከሌሎች በምትጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ ሁን። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ጃኔት እንዲህ ብላለች፦ “እስከ መጨረሻው አብሮህ የሚሆን ጥሩ ጓደኛ የሚሆንልህ ሁሉም ሰው አይደለም፤ ይሁን እንጂ ከልብ የሚያስቡልህ ጓደኞችን ማግኘትህ አይቀርም። ይህ ደግሞ በቂ ነው። ብቸኝነት እንዳይሰማህ ይረዳሃል።”

 ተጨማሪ ሐሳብ ማግኘት ትፈልጋለህ? ስለ ጓደኝነት የሚሰማህን ስጋት ማሸነፍ” የሚለውን ርዕስ አንብብ። በተጨማሪም “ብቸኝነትን ማሸነፍ” የሚል ርዕስ ያለውን ፒዲኤፍ አውርድ።