በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

ግብረ ሰዶም ስህተት ነው?

ግብረ ሰዶም ስህተት ነው?

 “በልጅነቴ መቋቋም ከነበሩብኝ ከባድ ፈተናዎች አንዱ ተመሳሳይ ፆታ ላላቸው ሰዎች የሚሰማኝ የፍቅር ስሜት ነበር። እንዲሁ የሚያልፍ ነገር መስሎኝ ነበር፤ ሆኖም ይህ ስሜት አሁንም ያስቸግረኛል።”—ዴቪድ፣ 23

 ዴቪድ አምላክን የማስደሰት ፍላጎት ያለው ክርስቲያን ነው። ሆኖም ተመሳሳይ ፆታ ላላቸው ሰዎች የፍቅር ስሜት እያደረበት አምላክን ማስደሰት ይችላል? አምላክ ስለ ግብረ ሰዶም ምን አመለካከት አለው?

 መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 ግብረ ሰዶምን በተመለከተ ሰዎች ያላቸው አመለካከት ከባህል ባህል ሊለያይ እንዲሁም ከጊዜ ወደ ጊዜ ሊለዋወጥ ይችላል። ሆኖም ክርስቲያኖች በብዙሃኑ አመለካከት አይመሩም ወይም ‘በማዕበል የሚነዱ ይመስል በማንኛውም የትምህርት ነፋስ ወዲያና ወዲህ አይንገዋለሉም።’ (ኤፌሶን 4:14) ከዚህ ይልቅ ግብረ ሰዶምን በተመለከተ (ወይም ሌላ ማንኛውንም ምግባር በተመለከተ) ያላቸው አመለካከት የተመሠረተው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙት መሥፈርቶች ላይ ነው።

  •  መጽሐፍ ቅዱስ ግብረ ሰዶምን በተመለከተ ያለው አመለካከት ግልጽ ነው። የአምላክ ቃል እንዲህ ይላል፦

     “ከሴት ጋር እንደምትተኛ ከወንድ ጋር አትተኛ።”—ዘሌዋውያን 18:22

  •  “አምላክ ልቅ ለሆነ የፆታ ምኞት አሳልፎ [ሰጣቸው]፤ ሴቶቻቸውም ተፈጥሯዊ የሆነውን ግንኙነት ከተፈጥሮ ውጭ በሆነ ግንኙነት ለወጡ።”—ሮም 1:26

  •  “አትታለሉ፤ ሴሰኞችም ሆኑ ጣዖት አምላኪዎች ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ግብረ ሰዶማውያን ወይም ሌቦች ወይም ስግብግቦች ወይም ሰካራሞች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ቀማኞች የአምላክን መንግሥት አይወርሱም።”—1 ቆሮንቶስ 6:9, 10

 የአምላክ መሥፈርቶች የግብረ ሰዶም ዝንባሌ ላላቸውም ሆነ ከተቃራኒ ፆታ ጋር የፆታ ግንኙነት የመፈጸም ዝንባሌ ላላቸው ሰዎች ይሠራሉ። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ አምላክን የማያስደስቱ ተግባራት የመፈጸም ዝንባሌ ያደረበት ማንኛውም ሰው ራሱን መቆጣጠር ይጠበቅበታል።—ቆላስይስ 3:5

 ታዲያ ይህ ማለት . . . ?

 ታዲያ ይህ ማለት፣ መጽሐፍ ቅዱስ ግብረ ሰዶማውያንን መጥላት እንዳለብን ይናገራል ማለት ነው?

 አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ግብረ ሰዶማዊ ሆነም አልሆነ ማንኛውንም ሰው መጥላትን አያበረታታም። ከዚህ ይልቅ የሰዎች የአኗኗር ዘይቤ ምንም ሆነ ምን “ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር ጥረት” እንድናደርግ ይነግረናል። (ዕብራውያን 12:14) በመሆኑም በግብረ ሰዶማውያን ላይ የጉልበተኝነት ድርጊት፣ በጥላቻ ተነሳስቶ ዓመጽ መፈጸም ወይም ማንኛውንም በደል ማድረስ ስህተት ነው።

 ታዲያ ክርስቲያኖች ተመሳሳይ ፆታ ባላቸው ሰዎች መካከል የሚፈጸመውን ጋብቻ የሚፈቅዱ ሕጎችን መቃወም አለባቸው ማለት ነው?

 መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ ትዳርን ያዘጋጀው በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል የሚፈጠር ጥምረት እንዲሆን አድርጎ እንደሆነ ይናገራል። (ማቴዎስ 19:4-6) ሆኖም ተመሳሳይ ፆታ ባላቸው ሰዎች መካከል የሚደረግን ጋብቻ በተመለከተ ሰዎች የሚያወጧቸው ሕጎች የሚያያዙት ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ጋር እንጂ ከሥነ ምግባር ጋር አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች ከፖለቲካ ጉዳዮች ገለልተኛ መሆን እንዳለባቸው ይናገራል። (ዮሐንስ 18:36) ስለሆነም ተመሳሳይ ፆታ ባላቸው ሰዎች መካከል የሚፈጸመውን ጋብቻ በተመለከተ መንግሥታት የሚያወጧቸውን ሕጎች አይደግፉም ወይም አይቃወሙም።

 ግን እንዲህ ቢሆንስ . . . ?

 ግን አንድ ሰው ግብረ ሰዶማዊ ቢሆንስ? ይህ ሰው መለወጥ ይችላል?

 ይችላል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ሰዎች መለወጥ ችለዋል! መጽሐፍ ቅዱስ ግብረ ሰዶማውያን የአምላክን መንግሥት እንደማይወርሱ ከተናገረ በኋላ እንዲህ ይላል፦ “አንዳንዶቻችሁም እንደዚህ ነበራችሁ።”—1 ቆሮንቶስ 6:11

 ታዲያ ይህ ማለት ግብረ ሰዶም መፈጸም ያቆሙት ሰዎች ከዚያ በኋላ ወደ ቀድሞ አኗኗራቸው የመመለስ ዝንባሌ ጨርሶ አይኖራቸውም ማለት ነው? አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “በትክክለኛ እውቀት አማካኝነት እየታደሰ የሚሄደውን አዲሱን ስብዕና ልበሱ።” (ቆላስይስ 3:10) ለውጥ ማድረግ ቀጣይ ሂደት ነው።

 ግን የአምላክን መመሪያዎች መከተል የሚፈልግ አንድ ሰው አሁንም ግብረ ሰዶም የመፈጸም ፍላጎት ቢኖረውስ?

 ከሌሎች መጥፎ ዝንባሌዎች ጋር በተያያዘ ማድረግ እንደሚቻለው ሁሉ ይህ ሰው ይህን ፍላጎቱን ለመግደል ወይም ለመፈጸም መምረጥ ይችላል። እንዴት? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “እኔ ግን በመንፈስ መመላለሳችሁን ቀጥሉ እላለሁ፤ እንዲህ ካደረጋችሁ የሥጋን ምኞት ከቶ አትፈጽሙም።”—ገላትያ 5:16

 ጥቅሱ ግለሰቡ ምንም የሥጋ ምኞት አይኖረውም እንደማይል ልብ በል። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስን የማጥናትና የመጸለይ ልማድ በማዳበር እነዚህን ምኞቶች መቋቋም ይቻላል።

 በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው ዴቪድ በተለይ በውስጡ ስለሚያደርገው ትግል ለክርስቲያን ወላጆቹ ከነገራቸው በኋላ የዚህን ሐሳብ እውነተኝነት መረዳት ችሏል። እንዲህ ብሏል፦ “ከትከሻዬ ላይ ከባድ ሸክም ወረደልኝ። ለወላጆቼ ቀደም ብዬ ነግሬያቸው ቢሆን ኖሮ የወጣትነት ሕይወቴን ይበልጥ ደስተኛ ሆኜ ማሳለፍ እችል ነበር።”

 ሕይወታችንን ከይሖዋ መመሪያዎች ጋር በሚስማማ መንገድ ከመራን ይበልጥ ደስተኞች መሆናችን አይቀርም። የይሖዋ መመሪያዎች ‘ትክክልና ልብን ደስ የሚያሰኙ’ እንደሆኑና “እነሱን መጠበቅ ትልቅ ወሮታ” እንዳለው እርግጠኞች ነን።—መዝሙር 19:8, 11