እንዲህ ዓይነት ጫና ሲደርስብሽ “ከዚህ ሁሉ የፆታ ግንኙነት እንድፈጽም የሚቀርብልኝን ጥያቄ ብቀበል አይሻልም? ደግሞስ ሁሉም ሰው የፆታ ግንኙነት ይፈጽም የለ?” ብለሽ ታስቢ ይሆናል።

እስቲ ቆም ብለሽ ለማሰብ ሞክሪ!

እውነታው፦ የፆታ ግንኙነት የሚፈጽመው ሁሉም ሰው አይደለም።

እርግጥ ነው፣ በርካታ ወጣቶች የፆታ ግንኙነት እንደሚፈጽሙ የሚገልጽ አኃዛዊ መረጃ ተመልክተሽ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ በዩናይትድ ስቴትስ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው በአገሪቱ ከሚኖሩ 3 ወጣቶች መካከል 2ቱ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ከመጨረሳቸው በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸም ይጀምራሉ። ይሁን እንጂ ይኸው አኃዝ እንደሚያመለክተው ከ3 ወጣቶች 1ዱ የፆታ ግንኙነት አይፈጽምም፤ ይህ ደግሞ ቀላል የሚባል ቁጥር አይደለም።

የፆታ ግንኙነት የሚፈጽሙት ወጣቶችስ? ተመራማሪዎች እንደገለጹት ከእነዚህ ወጣቶች አብዛኞቹ ከታች እንደተዘረዘሩት ያሉ ያልጠበቋቸው ሁኔታዎች ወይም ዱብ ዕዳዎች ያጋጥሟቸዋል።

ጸጸት። ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት የፈጸሙ አብዛኞቹ ወጣቶች በኋላ ላይ በድርጊታቸው እንደተቆጩ ተናግረዋል።

ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸም አንድን ውብ ሥዕል የበር ምንጣፍ እንደ ማድረግ ነው

አለመተማመን። ወጣቶቹ የፆታ ግንኙነት ከፈጸሙ በኋላ ‘ከእኔ ሌላ ከማን ጋር የፆታ ግንኙነት ፈጽማ/ፈጽሞ ይሆን?’ እያሉ ማሰብ ይጀምራሉ።

ግራ መጋባት። ማንም ሴት ብትሆን የወንድ ጓደኛዋ ከጉዳት እንዲጠብቃት እንጂ መጠቀሚያ እንዲያደርጋት አትፈልግም። ብዙዎቹ ወንዶች ደግሞ ከአንዲት ሴት የፈለጉትን ካገኙ በኋላ ያቺ ሴት ያን ያህል አትማርካቸውም።

ሊታሰብበት የሚገባው ነገር፦ ሰውነትሽን እንደ ውድ ነገር ልትመለከቺው ይገባል፤ እንደማይረባ ነገር አታቃልዪው። አምላክ ከዝሙት እንድንርቅ የሰጠውን ትእዛዝ ለመጠበቅ የሚያስችል ጥንካሬ እንዳለሽ በተግባር አሳዪ። ደግሞም የፆታ ግንኙነት መፈጸሙን ስታገቢ ትደርሺበታለሽ። ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸም ከሚያስከትለው ጭንቀትና ጸጸት ነፃ ሆነሽ በፆታ ግንኙነት የሚገኘውን ደስታ ሙሉ በሙሉ ማጣጣም የምትችዪው ካገባሽ በኋላ ነው።—ምሳሌ 7:22, 23፤ 1 ቆሮንቶስ 7:3