በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

በጉርምስና ዕድሜ የሚከሰቱ ለውጦችን ማስተናገድ የምችለው እንዴት ነው?

በጉርምስና ዕድሜ የሚከሰቱ ለውጦችን ማስተናገድ የምችለው እንዴት ነው?

 “ጉርምስና ለሴቶች የሚያስደስት ነገር አይደለም። ከባድ፣ ዝብርቅርቅ ያለና ግራ የሚያጋባ ወቅት ነው፤ ምንም ደስ የሚል ነገር የለውም!”—ኦክሳና

 “ለትንሽ ጊዜ ደስተኛ እሆንና ወዲያው ደግሞ ይከፋኛል። ሌሎች ወንዶች እንዲህ ተሰምቷቸው እንደሆነ አላውቅም፤ እኔን ግን አጋጥሞኛል።”—ብራያን

 የጉርምስና ዕድሜ አንዴ ወደ ላይ አውጥቶ ወዲያው ወደ ታች በሚያወርድ ሮለርኮስተር የተባለ መጫወቻ ላይ ተሳፍሮ ከመሄድ ጋር ሊመሳሰል ይችላል፤ ለምን? ምክንያቱም ይህ ዕድሜ አስደሳችም አስፈሪም ሊሆን ስለሚችል ነው! ታዲያ ይህን ዕድሜ በተሳካ መንገድ ማለፍ የምትችለው እንዴት ነው?

 ጉርምስና ምንድን ነው?

 በአጭር አነጋገር፣ ጉርምስና በጥቂት ጊዜ ውስጥ አካላዊና ስሜታዊ ለውጥ አድርገህ ሙሉ ሰው ወደ መሆን የምትሸጋገርበት የዕድሜ ክልል ነው። በዚህ የዕድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ ወጣቶች ሰውነት ላይ ፈጣን የሆነ አካላዊና ሆርሞናዊ ለውጥ ይካሄዳል፤ ይህም ሰውነታቸው ለመራባትና ልጅ ለመውለድ ዝግጁ እንዲሆን ያስችለዋል።

 ይህ ሲባል ግን በዚህ ዕድሜ ወላጅ ለመሆን ዝግጁ ነህ ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ጉርምስና የልጅነት ዕድሜን እንዳለፍክ የሚያሳይ ምልክት ነው፤ ይህ ደግሞ በአንድ በኩል ደስታ በሌላ በኩል ደግሞ ሐዘን እንዲሰማህ ሊያደርግ ይችላል።

 ጥያቄ፦ ጤናማ የሆኑ ልጆች መጎርመስ የሚጀምሩበት ዕድሜ የትኛው ይመስልሃል?

 • 8

 • 9

 • 10

 • 11

 • 12

 • 13

 • 14

 • 15

 • 16

 መልስ፦ የተዘረዘሩት ዕድሜዎች በሙሉ ጤናማ ልጆች መጎርመስ ሊጀምሩ በሚችሉበት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚካተቱ ናቸው።

 በመሆኑም ወደ አሥራዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ብትጠጋም የጉርምስና ምልክቶችን ገና ማየት ላትጀምር ትችላለህ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከአሥር ዓመት በታች ሆነህም የጉርምስና ምልክቶች ሊታዩብህ ይችላሉ። ይህ ጉዳይ ከልክ በላይ ሊያስጨንቅህ አይገባም። ጉርምስና የሚጀምርበት ዕድሜ የተለያየ ከመሆኑም ሌላ ይህ ወቅት በአብዛኛው ከአንተ ቁጥጥር ውጭ ነው።

የጉርምስና ዕድሜ ሮለርኮስተር ላይ ተሳፍሮ እንደመሄድ ነው፤ አስደሳችም አስፈሪም ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም ይህን ዕድሜ በተሳካ ሁኔታ ማለፍ ትችላለህ

 አካላዊ ለውጦች

 ከጉርምስና ጋር ተያይዘው ከሚመጡት ለውጦች መካከል በግልጽ የሚታየው ፈጣን እድገት ማድረግህ ሳይሆን አይቀርም። ችግሩ ግን ሁሉም የሰውነትህ ክፍሎች የሚያድጉት በተመሳሳይ ፍጥነት አለመሆኑ ነው። በመሆኑም በዚህ ወቅት ቅልጥፍጥፍ ማለት ቢያስቸግርህ አትደነቅ። በጊዜ ሂደት እየተስተካከለ እንደሚመጣ እርግጠኛ ሁን።

 ከጉርምስና ጋር ተያይዘው የሚመጡ በርካታ አካላዊ ለውጦች አሉ።

 ወንዶች የሚያጋጥሟቸው ለውጦች፦

 •   የፆታ ብልት ማደግ

 •   ብብት ሥር፣ የፆታ ብልት አካባቢና ፊት ላይ ፀጉር ማብቀል

 •   የድምፅ መጎርነን

 •   ሳይታሰብ የፆታ ስሜት መነሳሳትና ተኝተው ሳሉ ዘር መፍሰስ

 ሴቶች የሚያጋጥሟቸው ለውጦች፦

 •   ጡት ማውጣት

 •   ብብት ሥርና የፆታ ብልት አካባቢ ፀጉር ማብቀል

 •   የወር አበባ ማየት

 ወንዶችም ሆኑ ሴቶች የሚያጋጥሟቸው ለውጦች፦

 •   የሰውነት ጠረን፦ የሚፈጠረው ባክቴሪያ ከላብ ጋር በሚቀላቀልበት ጊዜ ነው።

   ይህን ለማድረግ ሞክር፦ አዘውትሮ በመታጠብና ዲዮደራንት ወይም የሰውነትን ላብ የሚቀንሱ ነገሮችን በመጠቀም የሰውነትን ጠረን መቆጣጠር ይቻላል።

 •   ብጉር፦ የሚፈጠረው በቆዳችን ውስጥ የሚገኙ ቅባት አመንጪ ዕጢዎች በባክቴሪያ በሚደፈኑበት ጊዜ ነው።

   ይህን ለማድረግ ሞክር፦ ብጉርን ማጥፋት ቀላል ባይሆንም ፊትን በተደጋጋሚ መታጠብና የቆዳ ማጽጃዎችን መጠቀም ሊረዳ ይችላል።

 ስሜታዊ ለውጦች

 በጉርምስና ወቅት አካላዊ ለውጥ እንዲፈጠር የሚያደርገው ከፍተኛ የሆነ የሆርሞን ለውጥ በስሜትህም ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። ከባድ የሆነ የስሜት መለዋወጥ ሊያጋጥምህም ይችላል።

 “አንድ ቀን ስታለቅስ ትውልና በቀጣዩ ቀን ግን ደህና ትሆናለህ። አንዴ ትበሳጫለህ፤ ከዚያ ደግሞ ድብርት ስለሚጫጫንህ ከክፍልህ መውጣት እንኳ ያስጠላሃል።”—ኦክሳና

 በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ በርካታ ወጣቶች ከልክ በላይ ስለ ራሳቸው ይጨነቃሉ፤ ሰው ሁሉ እነሱን የሚከታተላቸውና የሚታዘባቸው ይመስላቸዋል። ውጫዊ ገጽታህ በአጭር ጊዜ ውስጥ መለዋወጡ ደግሞ ሁኔታውን ያባብሰዋል!

 “ሰውነቴ እየተለወጠ ሲሄድ ሆን ብዬ መጉበጥና ሰፊ ቲሸርቶችን መልበስ ጀመርኩ። ሰውነቴ እየተለወጠ ያለው ለምን እንደሆነ አውቃለሁ፤ ሆኖም ሁኔታው ደስ የማይልና የሚያሳፍር ነበር። ለውጡን ለመልመድ ተቸግሬ ነበር።”—ጃኒስ

 ከሚያጋጥሙህ የስሜት ለውጦች መካከል ትልቁ ለተቃራኒ ፆታ ቀድሞ ከነበረህ ሙሉ በሙሉ የተለየ አመለካከት መያዝ ሳይሆን አይቀርም።

 “ቀደም ሲል ወንዶች ሁሉ የሚያበሳጩ እንደሆኑ ይሰማኝ ነበር፤ ከዚያ ግን ይህ ስሜቴ ጠፋ። አንዳንዶቹ ደስ ይሉኝ ጀመር፤ ማፍቀር አስደሳች ሊሆን እንደሚችል ይሰማኝ ጀመር። እንዲያውም ከእኩዮቼ ጋር ‘እገሌ እገሌን ይወዳታል ወይም ትወደዋለች’ በሚለው ጉዳይ ላይ ብዙ ጊዜ እናወራ ነበር።”—አሌክሲስ

 በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ አንዳንድ ወጣቶች ከእነሱ ጋር ተመሳሳይ ፆታ ላለው ሰው የፍቅር ስሜት ሊያድርባቸው ይችላል። አንተም ተመሳሳይ ነገር ካጋጠመህ ‘ግብረ ሰዶማዊ ነኝ’ ብለህ አትደምድም። አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ያለው ስሜት በጊዜ ሂደት ይጠፋል።

 “ራሴን በተደጋጋሚ ከሌሎች ወንዶች ጋር አወዳድር ስለነበር ወንዶችን መውደድ ጀመርኩ። ከጊዜ በኋላ ግን ሴቶች ይማርኩኝ ጀመር። አሁን ለወንዶች የፍቅር ስሜት የለኝም።”—አለን

 ምን ማድረግ ትችላለህ?

 •    አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝ ሞክር። ደግሞም በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚኖረው አካላዊና ስሜታዊ ለውጥ አስፈላጊ ነገር ነው። መዝሙራዊው ዳዊት ‘በሚያስደምም ሁኔታ ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁ’ በማለት የተናገረው ሐሳብ በራስ የመተማመን ስሜት እንድታዳብር ሊረዳህ ይችላል።—መዝሙር 139:14

 •   ራስህን ከሌሎች ጋር አታወዳድር፣ በውጫዊ ገጽታህ ላይ እንድታተኩር የሚያደርግህን ግፊት ተቋቋም። መጽሐፍ ቅዱስ “ሰው የሚያየው ውጫዊ ገጽታን ነው፤ ይሖዋ ግን የሚያየው ልብን ነው” ይላል።—1 ሳሙኤል 16:7

 •   በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴና እረፍት አድርግ። በቂ እንቅልፍ መተኛት ብስጭትን፣ ውጥረትንና ድብርትን ለመቀነስ ይረዳል።

 •   የሚሰማህን አፍራሽ አስተሳሰብ በሙሉ አታስተናግድ። በእርግጥ ሰው ሁሉ አንተን እየተከታተለህ ነው? ሰዎች ስለ እድገትህ አስተያየት ቢሰጡም እንኳ ለነገሮች ትክክለኛ አመለካከት ይኑርህ። መጽሐፍ ቅዱስ “ሰዎች የሚናገሩትን ነገር ሁሉ ትኩረት ሰጥተህ አትከታተል” ይላል።—መክብብ 7:21

 •   የፆታ ስሜትህን መቆጣጠር ተማር፤ እንዲህ ካላደረግክ ድርጊቱን ወደ መፈጸም ልትሄድ ትችላለህ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ከዝሙት ሽሹ! . . . ዝሙት የሚፈጽም ሁሉ ግን በራሱ አካል ላይ ኃጢአት እየሠራ ነው።”—1 ቆሮንቶስ 6:18

 •   ወላጆችህን ወይም አንድ የምታምነውን አዋቂ አማክር። እርግጥ እንዲህ ማድረግ መጀመሪያ ላይ ሊያሳፍርህ ይችላል። ሆኖም ከፍተኛ እርዳታ ስለምታገኝ እንዲህ በማድረግህ አትቆጭም።—ምሳሌ 17:17

 ዋናው ነጥብ፦ የጉርምስና ዕድሜ የራሱ የሆኑ ተፈታታኝ ነገሮች አሉት። ሆኖም አካላዊ ብቻ ሳይሆን አእምሯዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ እድገት የምታደርግበት አስደሳች አጋጣሚ ይከፍትልሃል።—1 ሳሙኤል 2:26