በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

የድንግልና ቃለ መሐላ ልግባ?

የድንግልና ቃለ መሐላ ልግባ?

 የድንግልና ቃለ መሐላ ምንድን ነው?

 የድንግልና ቃለ መሐላ ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት ላለመፈጸም በቃል ወይም በጽሑፍ የሚደረግ ቃል ኪዳን ነው።

 የድንግልና ቃለ መሐላ ሰፊ ተቀባይነት ማግኘት የጀመረው በ1990ዎቹ በዩናይትድ ስቴትስ ያሉ የሳውዘርን ባፕቲስት ኮንቬንሽን አባላት “እውነተኛ ፍቅር ይታገሣል” የሚል እንቅስቃሴ በጀመሩ ጊዜ ነበር፤ የዚህ ፕሮግራም ዓላማ የመጽሐፍ ቅዱስን እሴቶችና የጓደኞችን በጎ ተጽዕኖ ተጠቅሞ ወጣቶች ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት ከመፈጸም እንዲታቀቡ ማበረታታት ነው።

 ብዙም ሳይቆይ ሌላ ተመሳሳይ ፕሮግራም ተጀመረ፤ በዚህ ፕሮግራም ላይ ተካፋይ የሆኑ ወጣቶች ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት ላለመፈጸም ቃል እንደገቡ እንዲታወቅ እንዲሁም የገቡትን ቃል እንዲያስታውሱ ለማድረግ የብር ቀለበት ይሰጣቸው ነበር።

 የድንግልና ቃለ መሐላ መግባት ይጠቅማል?

 መልሱ ጥያቄው በሚቀርብላቸው ሰዎች ላይ የተመካ ነው።

  •   ክርስቲን ኪም እና ሮበርት ሬክተር የተባሉ ተመራማሪዎች እንደገለጹት “በጉርምስና ዕድሜ የድንግልና ቃለ መሐላ የሚገቡ ወጣቶች የፆታ ግንኙነት የሚጀምሩት ዘግይተው እንደሆነ አሊያም በዚያ ዕድሜ የፆታ ግንኙነት የመፈጸም አጋጣሚያቸው ከእኩዮቻቸው ያነሰ እንደሆነ በርካታ ጥናቶች ያሳያሉ።”

  •   ጉትማኸር የተባለው ተቋም ያዘጋጀው ምርምር እንደሚያሳየው “‘የድንግልና ቃለ መሐላ’ የሚገቡ ወጣቶች የፆታ ግንኙነት የመጀመር አጋጣሚያቸው መሐላውን ካልገቡት እኩል ነው።”

 ውጤቶቹ የተለያዩ የሆኑት ለምንድን ነው?

  •   አንዳንድ ጥናቶች ቃል የገቡ ወጣቶችን የሚያወዳድሩት ስለ ፆታ ግንኙነት ከእነሱ የተለየ አመለካከት ካላቸው ቃል ያልገቡ ወጣቶች ጋር ነው።

  •   ሌሎች ጥናቶች ደግሞ ቃል የገቡ ወጣቶችን የሚያወዳድሩት ስለ ፆታ ግንኙነት ከእነሱ ጋር ተመሳሳይ አመለካከት ካላቸው ቃል ያልገቡ ወጣቶች ጋር ነው።

 ሁለተኛው ነጥብ ላይ የተገለጹት ጥናቶች ምን ያሳያሉ? የወጣቶች ጤና ስፔሻሊስት የሆነችው ዶክተር ጃኔት ሮዘንቦም ከአምስት ዓመት በኋላ “መሐላውን በገቡና ባልገቡ ሰዎች መካከል የፆታ ግንኙነት ከመፈጸም ጋር በተያያዘ ምንም ልዩነት አይኖርም” ብላለች።

 የተሻለ አማራጭ

 የድንግልና ቃለ መሐላ ፕሮግራሞች ክቡር ዓላማ አላቸው። ሆኖም ወጣቶች ቃላቸውን እንዲጠብቁ የሚገፋፋቸውን የሥነ ምግባር እሴት መቅረጽ አልቻሉም። ይህን ቃል ከሚገቡ ወጣቶች መካከል አብዛኞቹ “ቃለ መሐላው አልተዋሃዳቸውም” በማለት ዶክተር ሮዘንቦም ተናግራለች። አክላም “አንድ ሰው ከጋብቻ በፊት ከፆታ ግንኙነት መታቀብ ያለበት በሆነ ፕሮግራም ስለተካፈለ ሳይሆን አምኖበትና በራሱ ተነሳስቶ መሆን አለበት” ብላለች።

 መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች በራሳቸው ተነሳስተው እንዲህ ያለ አቋም እንዲይዙ ያበረታታል፤ እንዲህ የሚያደርገው የቃል ወይም የጽሑፍ መሐላ እንዲገቡ በመጠየቅ ሳይሆን “ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት እንዲችሉ የማስተዋል ችሎታቸውን” እንዲያሠለጥኑ በመርዳት ነው። (ዕብራውያን 5:14) ደግሞም አንድ ሰው ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት ከመፈጸም የሚርቅበት ዋነኛ ምክንያት በሽታን ወይም እርግዝናን ፈርቶ ሳይሆን የጋብቻ መሥራች ለሆነው አምላክ አክብሮት ስላለው መሆን አለበት።—ማቴዎስ 5:19፤ 19:4-6

 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን መስፈርቶች ተግባራዊ ማድረግ የሚጠቅመው እኛኑ ነው። (ኢሳይያስ 48:17) በእርግጥም በየትኛውም የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎች “ከዝሙት ሽሹ” የሚለውን ትእዛዝ ለመፈጸም የሚረዳቸውን ቁርጠኝነት ሊያዳብሩ ይችላሉ። (1 ቆሮንቶስ 6:18) ትዳር ከመሠረቱ በኋላ ደግሞ የፆታ ግንኙነት በመፈጸም መደሰት ይችላሉ፤ ያን ጊዜ ደግሞ ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት ከመፈጸም ጋር ተያይዞ የሚመጣው ጭንቀትና ጸጸት አይኖርባቸውም።