በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

የወጣቶች ጥያቄ

በሚዲያ ላይ የሚታዩ እኩዮቼን መምሰል የሌለብኝ ለምንድን ነው?—ክፍል 2፦ ለወንዶች

በሚዲያ ላይ የሚታዩ እኩዮቼን መምሰል የሌለብኝ ለምንድን ነው?—ክፍል 2፦ ለወንዶች

በሚዲያ ላይ የሚታዩት እኩዮችህ ምን ዓይነት ባሕርይ አላቸው?

 ከታች ያሉትን ባሕርያት ተመልከት፤ ከዚያም ቀጥሎ ለቀረቡት ጥያቄዎች መልስ ስጥ።

ረድፍ 1

ረድፍ 2

ዓመፀኛ

ሰው አክባሪ

ራስ ወዳድ

ታማኝ

ጉልበተኛ

ርኅሩኅ

ሰነፍ

ታታሪ

ግድየለሽ

ኃላፊነት የሚሰማው

ተንኮለኛ

ሐቀኛ

 1. በሚዲያ (ለምሳሌ በፊልም፣ በቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ወይም በማስታወቂያዎች) ላይ የሚታዩት ወጣት ወንዶች ከላይ ከተጠቀሱት መካከል ይበልጥ የሚታወቁት በየትኞቹ ባሕርያት ነው?

 2. አንተስ ከላይ ከተጠቀሱት ባሕርያት መካከል የትኞቹ እንዲኖሩህ ትፈልጋለህ?

ለመጀመሪያው ጥያቄ መልስ የሰጠኸው ከረድፍ 1 በመምረጥ ሊሆን ይችላል፤ ለሁለተኛው ጥያቄ ደግሞ በረድፍ 2 ሥር ካሉት መካከል እንደምትመርጥ የታወቀ ነው። ከሆነ፣ በጣም ጥሩ። ምክንያቱም ይህ፣ በሚዲያ ላይ ከሚታዩት ወጣት ወንዶች የተለየህ እንደሆንክ ወይም ከእነሱ የተለየህ መሆን እንደምትፈልግ ያሳያል። እንዴት?

 • ብዙውን ጊዜ በሚዲያ ላይ የሚታዩት ወንዶች ዓመፀኛ ናቸው። ዋይ ቦይስ ዶንት ቶክ—ኤንድ ዋይ ኢት ማተርስ የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው በቴሌቪዥን ፕሮግራሞችና በፊልሞች እንዲሁም በስፖርቱ ዓለም ታዋቂ የሆኑ ወንዶች ብዙውን ጊዜ ‘ሰውነታቸው የፈረጠመና ግልፍተኛ ናቸው።’ “ይህም አንድ ወንድ አሪፍ የሚባለው ጉልበተኛና ዓመፀኛ ሲሆን እንደሆነ የሚጠቁም መልእክት ያስተላልፋል።”

  እስቲ አስበው፦ ጉልበተኛ መስለህ መታየትህ ጥሩ ጓደኛ፣ ጥሩ የሥራ ባልደረባ ወይም ጥሩ ባል እንድትሆን ይረዳሃል? ሰዎች ሲያበሳጩህ ይበልጥ ጥንካሬ የሚጠይቀው የቱ ነው? በንዴት እርምጃ መውሰድ ወይስ ቁጣህን መቆጣጠር? ብስለት እንዳለህ የሚያሳየውስ የትኛው ነው?

  መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ታጋሽ ሰው ከጦረኛ፣ ስሜቱን የሚገዛም ከተማን በጕልበቱ ከሚይዝ ይበልጣል።”ምሳሌ 16:32

 • ብዙውን ጊዜ በሚዲያ ላይ የሚቀርቡት ወንዶች የወሲብ ሱስ የተጠናወታቸው ናቸው። የ17 ዓመቱ ክሪስ “በፊልሞች ወይም በቲቪ ላይ ወንዶች የሴት ጓደኛን እንደ ልብስ ሲቀያይሩ ትመለከታላችሁ” ብሏል። የ18 ዓመቱ ጌሪ ደግሞ “በሚዲያ ላይ አሪፍ ተብለው የሚቀርቡት ወንዶች የወሲብ ሱስ የተጠናወታቸው ናቸው” በማለት ሁኔታው ከዚህ የከፋ መሆኑን ገልጿል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ፊልሞች የአንድ ወጣት ዋነኛ የሕይወት ግብ ፓርቲ፣ መጠጥ እና ወሲብ እንደሆነ አድርገው ያቀርባሉ።

  እስቲ አስበው፦ በሚዲያ ላይ የሚቀርቡትን ወንዶች ዓይነት ስም ማትረፍ ትፈልጋለህ? ደግሞስ ብስለት ያለው አንድ ወንድ ሴቶችን የሚመለከተው የወሲብ ስሜትን ለማርካት እንደተፈጠሩ አድርጎ ነው? ወይስ በአክብሮት ይይዛቸዋል?

  መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ከእናንተ እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ዕቃ እንዴት በቅድስናና በክብር መያዝ እንዳለበት እንዲያውቅ ነው፤ ይህም . . . ለፍትወተ ሥጋ በመጎምጀት አይሁን።”1 ተሰሎንቄ 4:4, 5

 • ብዙውን ጊዜ በሚዲያ ላይ የሚታዩት ወንዶች ኃላፊነት የሚሰማቸው አይደሉም። በጣም ተወዳጅ በሆኑ ፊልሞች እና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ላይ፣ ወጣት ወንዶች ብዙውን ጊዜ ሰነፍ እና ችሎታ የሌላቸው ተደርገው ይቀርባሉ። ምናልባትም አንዳንድ ሰዎች ወጣት ወንዶች ላይ ብዙም እምነት የማይጥሉት ለዚህ ሊሆን ይችላል። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ጌሪ እንዲህ ብሏል፦ “አሥራ ስድስት ዓመት ሲሆነኝ ሥራ ለማግኘት ተቸገርኩ፤ ምክንያቱም በአካባቢዬ ያሉት የንግድ ቤቶች መቅጠር የሚፈልጉት ሴቶችን ብቻ ነበር። እነዚህ ሰዎች፣ ሁሉም ወጣት ወንዶች ኃላፊነት የማይሰማቸው እና እምነት የማይጣልባቸው እንደሆኑ አድርገው ያስቡ ነበር!”

  እስቲ አስበው፦ ሁሉም ወጣት ወንዶች ኃላፊነት የማይሰማቸው እና እምነት የማይጣልባቸው እንደሆኑ ተደርገው መፈረጃቸው ተገቢ ነው? አንተ እንዲህ ዓይነት ሰው እንዳልሆንክ ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?

  መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ማንም ሰው ወጣትነትህን እንዲንቅ አትፍቀድ። ከዚህ ይልቅ ታማኞች ለሆኑት በንግግር፣ በምግባር፣ በፍቅር፣ በእምነትና በንጽሕና አርዓያ ሁን።”1 ጢሞቴዎስ 4:12

ልታውቀው የሚገባ ነገር

 •   በሚዲያ ላይ የሚታየው ነገር ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድርብህ ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ተወዳጅ መሆን ከፈለግህ የዘመኑን ፋሽን መከተል እንዳለብህ እንዲሰማህ ሊያደርግ ይችላል። የ17 ዓመቱ ኮሊን እንዲህ ብሏል፦ “ወንዶች እንዴት መልበስ እንዳለባቸው እንዲሁም ወንዶቹ እንዲህ በመልበሳቸው ሴቶቹን እንዴት እንዳማለሏቸው የሚያሳዩ ማስታወቂያዎች ይቀርባሉ። አንድ ሰው እነዚህን ማስታወቂያዎች ሲመለከት እሱም እነዚያን ልብሶች መግዛት ያምረዋል። እኔም እንደዚህ ያደረግኩባቸው ወቅቶች አሉ!”

  እስቲ አስበው፦ አለባበስህ እውነተኛውን ማንነትህን ይገልጻል? ወይስ የሌሎች ተከታይ መሆንህን ያሳያል? የዘመኑን ፋሽን ለመከተል ስትል ገንዘብህን የምትበትን ከሆነ በዋነኝነት የሚጠቀመው ማን ነው?

  መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “የዚህን ሥርዓት የአኗኗር ዘይቤ መኮረጅ አቁሙ።”ሮም 12:2

 • በሚዲያ ላይ የሚታዩ እኩዮችህን መምሰልህ በሴቶች ዘንድ ተወዳጅ እንዳትሆን ሊያደርግ ይችላል። እስቲ አንዳንድ ሴቶች ምን እንዳሉ ተመልከት፦

  • “ያልሆነውን ሆኖ በመታየት ሌሎችን ለማስደመም ከሚሞክር ወንድ ይልቅ በራሱ ማንነት የሚኮራ ወንድ ደስ ይለኛል። ሌሎችን ለማስደመም ከልክ በላይ የሚጥር ወንድ ሞኝ መስሎ መታየቱ አይቀርም!”—አና

  • “ማስታወቂያዎች፣ ወንዶች አንድ ዓይነት የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ካልገዙ ወይም ፋሽን ካልተከተሉ ሴቶችን ማማለል እንደማይችሉ አድርገው ያቀርባሉ። ሆኖም ሴቶች እያደጉ ሲሄዱ በአንድ ወንድ እንዲማረኩ የሚያደርጓቸው እነዚህ ነገሮች አይደሉም። ከዚህ ይልቅ የልጁን ባሕርይና ሰዎችን የሚይዝበትን መንገድ ይመለከታሉ። ለምሳሌ፣ ሴቶች ሐቀኛ እና ታማኝ የሆኑ ወንዶች ደስ ይሏቸዋል።”—ዳንዬል

  • “ብዙውን ጊዜ ‘በጣም ያምራል’ የሚባለው ወንድ ትዕቢተኛ ነው፤ እኔ ደግሞ ከእንዲህ ዓይነቱ ሰው አጠገብ ድርሽ ማለት እንኳ አልፈልግም። አንድ ወንድ በዓለም ላይ አለ የተባለ ቆንጆ ቢሆንም እንኳ ባሕሪው እንደ መልኩ ካልሆነ አስቀያሚ መሆኑ አይቀርም።”—ዳያና

  እስቲ አስበው፦ መጽሐፍ ቅዱስ ሳሙኤል ስለተባለ አንድ ወጣት ሲናገር “በአካልና በሞገስ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት እያደገ ሄደ” ይላል። (1 ሳሙኤል 2:26) አንተስ እንዲህ እንዲባልልህ ከፈለግህ የትኞቹን ባሕርያት ለማዳበር ጥረት ማድረግ አለብህ?

  መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ወንድ ሁኑ።”1 ቆሮንቶስ 16:13

ምን ማድረግ ትችላለህ?

 •   ያየኸውን ነገር ሁሉ አትከተል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘውን የሚከተለውን ሐሳብ ልብ በል፦ “በዓለም ያለው ነገር ሁሉ ይኸውም የሥጋ ምኞት፣ የዓይን አምሮትና ኑሮዬ ይታይልኝ የሚል መንፈስ ከዓለም እንጂ ከአብ የሚመነጭ አይደለም።”1 ዮሐንስ 2:16

  ሚዲያው ሰዎች ያሏቸውን እነዚህን ዝንባሌዎች ይጠቀማል፤ እንዲሁም እነዚህ ዝንባሌዎች ጥሩ ነገሮች እንደሆኑ አድርጎ ያቀርባል። ስለዚህ የምታየውን ነገር ሁሉ በጭፍን አትመን። በሚዲያ ላይ የሚቀርቡት ነገሮች ብዙውን ጊዜ የንግድ ሰዎች ትርፍ ለማግኘት የሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች ናቸው።

 • የራስህን ምርጫ አድርግ። በሚዲያ ላይ የሚታዩትን ሰዎች ከመምሰል ይልቅ “ከፈጣሪው አምሳል ጋር በሚስማማ ሁኔታ በትክክለኛ እውቀት አማካኝነት እየታደሰ የሚሄደውን አዲሱን ስብዕና” እንድንለብስ መጽሐፍ ቅዱስ ይመክረናል።ቆላስይስ 3:10

  ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በተግባር ላይ ማዋል እንዲቀልህ በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ የተጠቀሱትን አንተ እንዲኖሩህ የምትፈልጋቸውን ባሕርያት መለስ ብለህ ለማሰብ ሞክር። ታዲያ እነዚህን ባሕርያት ለማዳበር ወይም ባሕርያቱን በተሻለ መንገድ ለማንጸባረቅ ለምን ጥረት አታደርግም?

 • ጥሩ አርዓያ ሊሆኑህ የሚችሉ ሰዎችን ፈልግ። መጽሐፍ ቅዱስ “ከጠቢብ ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል” ይላል። (ምሳሌ 13:20) ጠቢብ የሆኑ የምታውቃቸው ወንዶች አሉ? አንዳንድ የቤተሰብህ አባላት ለምሳሌ አባትህ ወይም አጎትህ ትዝ ይሉህ ይሆናል። አሊያም ደግሞ ብስለት ያላቸው የወንድ ጓደኞችህ እና ሌሎች የምታውቃቸው ሰዎችም በዚህ ረገድ ጥሩ አርዓያ ሊሆኑህ ይችላሉ። የይሖዋ ምሥክሮች በጉባኤያቸው ውስጥ ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉ በርካታ ወንዶችን ማግኘት ይችላሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይም ለወጣቶች ጥሩ አርዓያ ሊሆኑ የሚችሉ እንደ ቲቶ ያሉ ወንዶች ተጠቅሰዋል።ቲቶ 2:6-8

  እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ታሪካቸው ስለተጠቀሱ ጥሩ ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉ ወንዶች ለማወቅ በእምነታቸው ምሰሏቸው የተባለውን መጽሐፍ አንብብ፤ በመጽሐፉ ላይ ከተጠቀሱት ወንዶች መካከል አቤል፣ ኖኅ፣ አብራም፣ ሳሙኤል፣ ኤልያስ፣ ዮናስና ጴጥሮስ ይገኙበታል።