በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

የወጣቶች ጥያቄ

ዛሬ ነገ የማለት ልማዴን ማስተካከል የምችለው እንዴት ነው?

ዛሬ ነገ የማለት ልማዴን ማስተካከል የምችለው እንዴት ነው?

የቤት ውስጥ እንዲሁም የትምህርት ቤት ሥራዎችን ሁልጊዜ ባለቀ ሰዓት መሥራት ሰልችቶሃል? ከሆነ ሥራዎችህን ለነገ እያልክ ማሳደርህን ማቆም አለብህ! ይህ ርዕስ፣ ከታች የተጠቀሱት ዓይነት ሁኔታዎች ቢኖሩም እንኳ ዛሬ ነገ የማለት ልማድን መተው እንድትችል ይረዳሃል፦

ይህን ርዕስ ካነበብህ በኋላ  ዛሬ ነገ ማለት—ጥያቄዎች የሚለውን መልመጃ ሥራ።

መጽሐፍ ቅዱስ ዛሬ ነገ ማለት ያለውን ጉዳት ይገልጻል። እንዲህ ይላል፦ “ነፋስን የሚጠባበቅ አይዘራም፤ ደመናትንም የሚያይ አያጭድም።መክብብ 11:4

ለዚህ ዓይነቱ ችግር አስተዋጽኦ የሚያደርጉ አንዳንድ ነገሮችን እንዲሁም ዛሬ ነገ የማለት ልማድን ለመተው ልትወስዳቸው የምትችላቸው እርምጃዎችን ተመልከት።

 ሥራው ከአቅምህ በላይ እንደሆነና በወቅቱ ልታጠናቅቀው እንደማትችል ሲሰማህ።

እውነቱን ለመናገር፣ አንዳንድ ሥራዎች በጣም ከባድ ሊሆኑ ይችላሉ፤ በመሆኑም ሥራውን ለሌላ ጊዜ ለማስተላለፍ ትፈተን ይሆናል። ከሆነ፣ በዚህ ረገድ ሊረዱህ የሚችሉ አንዳንድ ሐሳቦች ከታች ቀርበዋል።

  • ሥራውን ከፋፍለው። ሜሊሳ የተባለች ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “ሥራውን የጀመርኩት በጣም ዘግይቼ ቢሆንም እንኳ በአንድ ጊዜ የተወሰነ ነገር በማከናወን ሥራውን ለማጠናቀቅ እጥራለሁ።

  • ወዲያውኑ ጀምር። አንድ ሥራ ሲሰጥህ ወዲያውኑ ጀምረው፤ በተሰጠህ ሰዓት ሥራውን ለማከናወን በቂ ጊዜ እንደሌለህ ቢሰማህ እንኳ ሥራውን እንዳትረሳው ማስታወሻህ ላይ እንደ ማስፈር ወይም ስለ ሥራው የተወሰኑ ሐሳቦችን ጫር ጫር እንደ ማድረግ ያሉ ትናንሽ ነገሮችን ወዲያውኑ ማከናወን ትችላለህ።—ቬራ

  • የሌሎችን እርዳታ ጠይቅ። ወላጆችህ ወይም አስተማሪዎችህ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሟቸው ያውቅ ይሆናል። ታዲያ እነሱ ተሞክሯቸውን እንዲያካፍሉህ ለምን አትጠይቃቸውም? ሥራውን ማቀናጀትና እቅድ ማውጣት እንድትችል ሊረዱህ ይችላሉ።

ጠቃሚ ምክር ፕሮግራም አውጣ። እርግጥ ነው፣ ይህን ማድረግ የተደራጀህ መሆንንና ፕሮግራምህን በጥብቅ መከተልን ይጠይቅብሃል፤ ይሁን እንጂ ሥራዎችህን ሁሉ ባሰብኸው ጊዜ እንድታጠናቅቅ ስለሚያስችልህ ውጤታማ ዘዴ ነው።—አቢ

 የመሥራት ተነሳሽነት ሳይኖርህ ሲቀር።

አብዛኛውን ጊዜ አንዳንድ ሥራዎች ከባድ የሚሆኑብህ አሰልቺ እንደሆኑ ስለሚሰማህ ሊሆን ይችላል። ታዲያ የማትወደው ዓይነት ሥራ በሚሰጥህ ጊዜ ምን ማድረግ ትችላለህ? የሚከተሉትን ነገሮች ለማድረግ ሞክር።

  • ሥራውን በጊዜ ማከናወንህ ያለውን ጥቅም አስብ። ለምሳሌ ያህል፣ ሥራውን ስታጠናቅቅ ምን ያህል እንደምትደሰት ለማሰብ ሞክር። ኤሚ የተባለች ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “አንድን ሥራ በጊዜው ሳጠናቅቅ ወይም ሥራውን ማጠናቀቅ ከሚጠበቅብኝ ጊዜ በፊት ጨርሼ ዘና ማለት ስችል በጣም ደስ ይለኛል።

  • ሥራን በጊዜ አለማጠናቀቅ ያሉትን ጉዳቶች አስታውስ። ሥራህን በጊዜ አለማጠናቀቅህ የበለጠ ውጥረት የሚጨምርብህ ከመሆኑም ሌላ ሥራውን በአግባቡ እንዳትወጣ እንቅፋት ሊሆንብህ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “አንድ ሰው ምንም ዘራ ምን ያንኑ መልሶ ያጭዳል” ይላል።ገላትያ 6:7

  • ሥራውን እንድታጠናቅቅ ከሚጠበቅብህ ቀን ቀድመህ ለመጨረስ ራስህን አሳምን። አሊስያ የተባለች ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “አንድን ሥራ ማጠናቀቅ ያለብኝ እንዳጠናቅቅ ከሚጠበቅብኝ ጊዜ አንድ ወይም ሁለት ቀን በፊት እንደሆነ አድርጌ ማሰቤ ጠቅሞኛል። ይህም ያከናወንኩትን ሥራ መለስ ብዬ ለመገምገም የሚያስችለኝ ከመሆኑም ሌላ አንድ ወይም ሁለት ቀን ስላለኝ ዘና ማለት እችላለሁ።

ጠቃሚ ምክር ቁልፉ ያለው አመለካከትህ ላይ ነው። መሥራት ያለብህን ነገር ማከናወን እንዳለብህና ምንም ዓይነት እንቅፋት ቢያጋጥምህ ሥራውን ማጠናቀቅ እንደምትችል ራስህን አሳምነው። ራሴን እንዲህ ብዬ ካሳመንኩት ማከናወን ያለብኝን ነገር አከናውናለሁ።—አሌክሲስ

 በሌሎች ሥራዎች ስትወጠር።

ናታን የተባለ ወጣት እንዲህ ብሏል፦ “ብዙውን ጊዜ ሰዎች፣ ዛሬ ነገ የማለት ልማድ እንዳለኝ ይናገራሉ፤ ይህ ግን ትክክል አይደለም! እነዚህ ሰዎች ምን ያህል ሥራ እንደሚበዛብኝ አልገባቸውም!” አንተም እንደ ናታን የሚሰማህ ከሆነ ከታች የተጠቀሱትን ምክሮች በተግባር ለማዋል ሞክር።

  • ቀላል የሆኑትን ሥራዎች መጀመሪያ ላይ አከናውን። አንድ ሥራ፣ የሚወስደው ጊዜ ከአምስት ደቂቃ ያነሰ ከሆነ ወዲያውኑ እንዳከናውነው አንድ ሰው ነግሮኝ ነበር” በማለት አምበር የተባለች ወጣት ተናግራለች። “ለምሳሌ እንደ ማጽዳት፣ ልብሶቼን መስቀል፣ ዕቃ ማጠብ ወይም ስልክ መደወል ያሉ ሥራዎች ያን ያህል ብዙ ጊዜ አይጠይቁም።

  • ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ነገሮች ወስን። መጽሐፍ ቅዱስ “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ [እወቁ]” ይላል። (ፊልጵስዩስ 1:10) ይህን ሐሳብ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎችህ ተግባራዊ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? አና የተባለች ወጣት እንዲህ ትላለች፦ “ማከናወን የሚገቡኝን ሥራዎች ዝርዝር እንዲሁም መቼ ማጠናቀቅ እንደሚገባኝ እጽፋለሁ። እያንዳንዱን ሥራ መቼ ለመጀመርና ለማጠናቀቅ እንዳሰብኩ በማስታወሻ ማስፈሬ ደግሞ ከሁሉ የበለጠ ጠቅሞኛል።

እንዲህ ማድረግ መፈናፈኛ እንደሚያሳጣህ ይሰማሃል? እስቲ ጉዳዩን ቆም ብለህ ለማሰብ ሞክር! እውነቱን ለመናገር፣ ባወጣኸው ፕሮግራም የምትመራ ከሆነ ከጊዜ ጋር ከመሯሯጥ ይልቅ አንተ ራስህ ጊዜህን በፈለግኸው መንገድ መጠቀም ትችላለህ። ይህ ደግሞ ውጥረት ይቀንስልሃል። ኬሊ የተባለች ወጣት “እቅድ ማውጣቴ የሚያረጋጋኝ ከመሆኑም ሌላ ነገሮችን በተቀናጀ መንገድ እንዳከናውን ያስችለኛል” ብላለች።

  • ትኩረት የሚከፋፍሉ ነገሮችን አስወግድ። ጄኒፈር እንዲህ ብላለች፦ “አንድ ዓይነት ሥራ ለማከናወን ሳስብ ቤት ውስጥ ላሉት ሁሉ ይህን አሳውቃቸዋለሁ። እንዳደርግላቸው የሚፈልጉት ነገር ካለ ሥራዬን ከመጀመሬ በፊት እንዲያሳውቁኝ እጠይቃቸዋለሁ። እንዲሁም ስልኬና የኢ-ሜይል መልእክቶች እንዳይረብሹኝ ሁሉንም ነገር አጠፋለሁ።

ጠቃሚ ምክር አንድን ሥራ መሥራታችሁ ካልቀረላችሁ ስለ ሥራው እያሰባችሁ ከመጨነቅ ይልቅ ሠርታችሁ ብትገላገሉት ይሻላል። ከዚያ በኋላ እፎይ ትላላችሁ።—ጆርዳን