በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

ውፍረት መቀነስ የምችለው እንዴት ነው?

ውፍረት መቀነስ የምችለው እንዴት ነው?

 በእርግጥ ውፍረት መቀነስ ያስፈልገኛል?

 አንዳንድ ወጣቶች ውፍረት መቀነስ እንደሚፈልጉ ይናገራሉ። ሆኖም . . .

 •   ብዙዎቹ ውፍረት መቀነስ የሚፈልጉት ለጤናቸው ሳይሆን ለቁመናቸው ብለው ነው። አንዳንዶች ክብደት ለመቀነስ ሲሉ ፈጣን ውጤት ያስገኛሉ ተብለው የሚታሰቡ ነገሮችን ይሞክራሉ፤ ለምሳሌ ቁርስ፣ ምሳ ወይም ራት ይዘላሉ ወይም ክብደት የሚያስቀንስ ኪኒን ይውጣሉ። ሆኖም እንዲህ ያሉት ዘዴዎች ዘላቂ ውጤት አያስገኙም፤ እንዲያውም አደገኛ ሊሆኑ ይችላሉ።

   “አንዳንድ ሴቶች ቶሎ ውፍረት ለመቀነስ ሲሉ ራሳቸውን ያስርባሉ። ይሄ ግን አብዛኛውን ጊዜ ሰውነታቸውን ይጎዳዋል፤ ከጉዳቱ ለማገገም ረጅም ጊዜ ይወስድባቸዋል።”—ሄይሊ

 •   ውፍረት ለመቀነስ የሚያስቡ ብዙ ወጣቶች ወፍራም አይደሉም። እነዚህ ወጣቶች ክብደታቸው ጤናማ ቢሆንም ከእኩዮቻቸው ወይም ሚዲያዎች ጥሩ ቁመና አላቸው ብለው ከሚያቀርቧቸው ሰዎች ጋር ራሳቸውን ሲያወዳድሩ ወፍራም እንደሆኑ ይሰማቸዋል።

   “የ13 ዓመት ልጅ እያለሁ ራሴን ከጓደኞቼ ጋር አወዳድር ነበር። ጓደኞቼ ይበልጥ እንዲወዱኝ ከፈለግኩ እንደ እነሱ በጣም ቀጫጫ መሆን እንዳለብኝ ይሰማኝ ነበር።”—ፓውላ

 በሌላ በኩል ግን በእርግጥ ክብደት መቀነስ የሚያስፈልጋቸው ወጣቶች አሉ። የዓለም የጤና ድርጅት ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው . . .

 •   በዓለም ዙሪያ ከ5 እስከ 19 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ 340 ሚሊዮን የሚያህሉ ወጣቶች ክብደታቸው ከተገቢው በላይ ነው።

 •   በ1975 ከ5-19 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ካሉ ልጆች መካከል ክብደታቸው ከልክ በላይ የሆኑት 4 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ነበሩ። በ2016 ግን ይህ አኃዝ ወደ 18 በመቶ ከፍ ብሏል።

 •   በብዙ የዓለም ክፍሎች ውስጥ በጣም ቀጭን ከሆኑ ሰዎች ይልቅ በጣም ወፍራም የሆኑት ይበልጣሉ።

 •   ከልክ ያለፈ ውፍረት በድሃ አገሮች ውስጥም ጭምር የተለመደ ሆኗል፤ የተመጣጠነ ምግብ የማያገኙ ቤተሰቦች እንኳ በዚህ ችግር ሊጠቁ ይችላሉ።

 ውፍረት ለመቀነስ ከሁሉ የተሻለው ዘዴ የቱ ነው?

 የትኛው ዘዴ የተሻለ ይመስልሃል?

 1.   ቁርስ፣ ምሳ ወይም ራት አለመብላት።

 2.   የተመጣጠነ ምግብ መመገብና እንቅስቃሴ ማድረግ።

 3.   ውፍረት የሚያስቀንሱ ኪኒኖችን መዋጥ።

 ትክክለኛው መልስ፦ 2ኛው ዘዴ፦ የተመጣጠነ ምግብ መመገብና እንቅስቃሴ ማድረግ።

 ቁርስ፣ ምሳ ወይም ራት ባለመብላት ራስን ማስራብ ወይም አንድን የምግብ ቡድን ሙሉ በሙሉ መተው ቶሎ ክብደት ለመቀነስ ይረዳ ይሆናል። ሆኖም እንዲህ ያለው ዘዴ ጤናማ ላይሆን ይችላል፤ እንዲሁም ወደ ቀድሞ አመጋገብህ ስትመለስ ድጋሚ ውፍረት መጨመርህ አይቀርም።

 በሌላ በኩል ግን፣ ጤናማ ለመሆን የሚያስችልህን ዘዴ ከተከተልክ ጤንነትህም ሆነ ቁመናህ ይሻሻላል። ዶክተር ማይክል ብራድሊ እንደጻፉት “ከሁሉ የተሻለው፣ ጤናማ የሆነውና ዘላቂ ውጤት የሚያስገኘው ዘዴ . . . ዕድሜህን ሙሉ ልትከተለው የምትችለው የአኗኗር ለውጥ ማድረግ ነው።” a ነጥቡ ምንድን ነው? ውፍረት መቀነስ ካለብህ ለየት ያለ የአመጋገብ ሥርዓት (ዳየት) ከመከተል ይልቅ ይበልጥ ጤናማ ለመሆን የሚያስችል የአኗኗር ለውጥ አድርግ።

 ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

 መጽሐፍ ቅዱስ ‘በልማዶቻችን ልከኞች’ እንድንሆን ይመክረናል፤ ይህ ደግሞ አመጋገባችንንም ይጨምራል። (1 ጢሞቴዎስ 3:11) እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ከልክ በላይ መብላት እንደሌለብን በቀጥታ ይናገራል። (ምሳሌ 23:20፤ ሉቃስ 21:34) አኗኗርህን ጤናማ ማድረግ ከፈለግክ እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮች በአእምሮህ ይዘህ የሚከተሉትን ነጥቦች በሥራ ላይ ለማዋል ሞክር፦

 •   ጤናማ አመጋገብ ምን ነገሮችን እንደሚያካትት እወቅ።

   ስለምትበላው ምግብ ከልክ በላይ መጨነቅ ባይኖርብህም ጤናማ አመጋገብን በተመለከተ የተወሰነ እውቀት መቅሰምህ አመጋገብህን የተመጣጠነ ለማድረግ ይረዳሃል። የተመጣጠነ አመጋገብ ደግሞ ክብደት ለመቆጣጠር ከሚያስችሉ ውጤታማ ዘዴዎች አንዱ ነው።

 •   አዘውትረህ አካላዊ እንቅስቃሴ አድርግ።

   በየቀኑ እንቅስቃሴ ለማድረግ የሚያስችሉ ዘዴዎችን ፈልግ። ለምሳሌ በሊፍት ከመሄድ ይልቅ ደረጃ መጠቀም ትችላለህ። ወይም ደግሞ ቴሌቪዥን በማየት አሊያም ኢንተርኔት በመጠቀም ከምታሳልፈው ጊዜ ላይ 30 ደቂቃውን ወጥተህ በእግርህ ለመንሸራሸር ልትጠቀምበት ትችላለህ።

 •   የሚያወፍሩ ምግቦችን በጤናማ ምግቦች ተካ።

   ሶፊያ የተባለች ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “እንደ አትክልትና ፍራፍሬ ያሉ ጤናማ ምግቦች ሁልጊዜ በአቅራቢያዬ እንዲኖሩ አደርጋለሁ። ይህ ደግሞ የሚያወፍሩ ምግቦችን እንዳላበዛ ይረዳኛል።”

 •   ቀስ ብለህ ብላ።

   አንዳንድ ሰዎች ቶሎ ቶሎ ስለሚበሉ መጥገባቸው አይታወቃቸውም። ስለዚህ ቀስ ብለህ ብላ! ምግብ ከመጨመርህ በፊት ጥቂት ደቂቃ ቆይ። እንዲህ ስታደርግ እንደጠገብክ ትገነዘብ ይሆናል።

 •   የምትበላውን ምግብ የካሎሪ መጠን አጣራ።

   የምትበላው ምግብ ምን ያህል ካሎሪ እንዳለው ከእሽጉ ላይ አንብብ። ለምሳሌ ለስላሳ መጠጦች እንዲሁም ቅባታማና ጣፋጭ የሆኑ ምግቦች ብዙ ካሎሪ ስላላቸው ያወፍራሉ።

 •   ሚዛናዊ ሁን።

   የ16 ዓመቷ ሳራ እንዲህ ብላለች፦ “በአንድ ወቅት ሥራዬ ሁሉ ካሎሪ መቁጠር ብቻ ሆኖ ነበር፤ ምግብ ሳይ የሚታየኝ ቁጥር ነበር።” አልፎ አልፎ ብዙ ካሎሪ ያለው ምግብ ብትመገብ ችግር ላይኖረው ይችላል።

 ጠቃሚ ምክር፦ ክብደትህን በተመለከተ የሚያሳስብህ ነገር ካለ ሐኪምህን አማክር። ሐኪምህ አጠቃላይ ጤንነትህን ግምት ውስጥ በማስገባት ምን ዓይነት አኗኗር ሊኖርህ እንደሚገባ ምክር ሊሰጥህ ይችላል።

a ዌን ቲንግስ ጌት ክሬዚ ዊዝ ዩር ቲን ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ።