በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወላጆቼ እንድዝናና የማይፈቅዱልኝ ለምንድን ነው?

ወላጆቼ እንድዝናና የማይፈቅዱልኝ ለምንድን ነው?

እስቲ የሚከተለውን ሁኔታ አስብ፦

በአንድ ግብዣ ላይ መገኘት ፈልገሃል፤ ወላጆችህ ግን የሚፈቅዱልህ አልመሰለህም። ታዲያ ምን ማድረግ ትችላለህ?

  1.  ሳታስፈቅድ መሄድ

  2.  ማስፈቀዱንም መሄዱንም መተው

  3.  መጠየቅና የሚሉትን መስማት

 1. ሳታስፈቅድ መሄድ

 ይህን ማድረግ የምትፈልግበት ምክንያት፦ የወላጆችህን ፈቃድ ሳትጠይቅ የፈለግኸውን ማድረግ እንደምትችል ለእኩዮችህ ለማሳየት ብለህ ይሆናል። ወይም ከወላጆችህ የበለጠ እንደምታውቅ ስለሚሰማህ አሊያም የእነሱ አመለካከት ትክክል እንዳልሆነ ስለምታስብ ይሆናል።—ምሳሌ 14:18

 ውጤቱ፦ እንዲህ በማድረግህ ጓደኞችህ ሊያደንቁህ ቢችሉም አታላይ እንደሆንህ ማሰባቸው አይቀርም። ዛሬ ወላጆችህን ካታለልህ ነገ ጓደኞችህንም ልታታልል ትችላለህ። ወላጆችህ ስለ ጉዳዩ ካወቁ ደግሞ በጣም ሊያዝኑብህ አልፎ ተርፎም በአንተ ላይ ያላቸውን እምነት ሊያጡና ተጨማሪ ገደብ ሊጥሉብህ ይችላሉ!—ምሳሌ 12:15

 2. ማስፈቀዱንም መሄዱንም መተው

 ይህን ማድረግ የምትፈልግበት ምክንያት፦ መዝናኛው አንተ ከምትከተላቸው መመሪያዎች ጋር እንደማይሄድ ወይም በቦታው ከሚገኙት መካከል አንዳንዶቹ ጥሩ ምግባር የሌላቸው እንደሆኑ ስለተገነዘብህ ሊሆን ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 15:33፤ ፊልጵስዩስ 4:8) በሌላ በኩል ደግሞ ለመሄድ ብትፈልግም ወላጆችህን ማስፈቀድ ትፈራ ይሆናል።

 ውጤቱ፦ የጓደኞችህን ግብዣ ያልተቀበልከው መዝናኛው ጥሩ እንዳልሆነ ስለተሰማህ ከሆነ ጓደኞችህ ለምን እንደቀረህ ሲጠይቁህ በልበ ሙሉነት መልስ መስጠት ትችላለህ። ላለመሄድ የወሰንከው ወላጆችህን መጠየቁ ስላስፈራህ ብቻ ከሆነ ግን ጓደኞችህ ሲዝናኑ አንተ ብቻ እንደቀረህ በማሰብ ቤትህ ቁጭ ብለህ ስትብሰለሰል ልትውል ነው።

 3. መጠየቅና የሚሉትን መስማት

 ይህን ማድረግ የምትፈልግበት ምክንያት፦ ወላጆችህ በአንተ ላይ ሥልጣን እንዳላቸውና ከአንተ የተሻለ እንደሚያውቁ ስለተገነዘብህ ሊሆን ይችላል። (ቆላስይስ 3:20) አሊያም ወላጆችህን ስለምትወዳቸውና ከእነሱ ተደብቀህ በመሄድ ልታሳዝናቸው ስለማትፈልግ ይሆናል። (ምሳሌ 10:1) ይህን አማራጭ የምትፈልግበት ሌላው ምክንያት ደግሞ ምን እንደምትፈልግ ለወላጆችህ ለመግለጽ አጋጣሚ ስለሚፈጥርልህ ሊሆን ይችላል።

 ውጤቱ፦ ወላጆችህ እንደምትወዳቸውና እንደምታከብራቸው ይሰማቸዋል። በዚያ ላይ ደግሞ ጥያቄህን ምክንያታዊ ሆኖ ካገኙት ሊፈቅዱልህ ይችላሉ።

ወላጆች ላይፈቅዱ የሚችሉበት ምክንያት

እንደ ሕይወት አድን ሠራተኞች ሁሉ ወላጆችህም አደጋ የሚያስከትሉ ሁኔታዎችን ለማየት በሚያስችል የተሻለ ቦታ ላይ ናቸው

 አንዱን ምክንያት ለመረዳት ቀጥሎ ያለውን ምሳሌ ተመልከት፦ ለመዋኘት አስበሃል እንበል፤ በምትዋኝበት ወቅት ከተቻለ ሕይወት አድን ሠራተኞች በአካባቢው እንዲኖሩ እንደምትፈልግ የታወቀ ነው። ለምን? ምክንያቱም አብዛኛውን ጊዜ ውኃው ውስጥ ስትሆን መዝናናትህ እንጂ ሊመጣ የሚችለው አደጋ አይታይህም። ሕይወት አድን ሠራተኞቹ የተቀመጡት ግን አደጋ የሚያስከትሉ ሁኔታዎችን ለማየት በሚያስችላቸው የተሻለ ቦታ ላይ ነው። በተመሳሳይም ወላጆችህ ከአንተ የተሻለ እውቀትና ተሞክሮ ስላላቸው አንተ የማታያቸውን አደጋዎች ሊያስተውሉ ይችላሉ። እንደ ሕይወት አድን ሠራተኞቹ ሁሉ የወላጆችህም ዓላማ እንዳትዝናና ማድረግ ሳይሆን ደስታህን ሊያሳጡህ ከሚችሉ አደጋዎች አንተን መጠበቅ ነው።

 ሌላው ምክንያት ደግሞ፦ ወላጆችህ አንተን ከጉዳት ለመጠበቅ ይፈልጋሉ። አንተን ስለሚወዱህ፣ የጠየቅኸው ነገር ተገቢ ሲሆን ሊፈቅዱልህ የሚፈልጉ ቢሆንም አደጋ ሊያጋጥምህ እንደሚችል ከተሰማቸው ይከለክሉሃል። አንድ ነገር ጠይቀሃቸው ከመፍቀዳቸው በፊት ሁኔታው ጉዳት የማያስከትል መሆን አለመሆኑን በደንብ ያስቡበታል። የጠየቅኸውን ነገር የሚፈቅዱልህ ምንም ጉዳት እንደማይደርስብህ ለማመን የሚያበቃ ምክንያት ካለ ብቻ ነው።

ፈቃድ ለማግኘት ምን ማድረግ ትችላለህ?

አራት ነጥቦችን እንመልከት።

 ሐቀኛ ሁን። ራስህን እንዲህ እያልክ በሐቀኝነት መጠየቅ ይኖርብሃል፦ ‘መሄድ የምፈልግበት ዋነኛ ምክንያት ምንድን ነው? መዝናኛውን ስለምወደው ነው ወይስ በእኩዮቼ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት ስለፈለግኩ? ወይም ደግሞ ደስ የምትለኝ ልጅ እዚያ ስለምትመጣ ነው?’ ወላጆችህን በምታስፈቅድበት ጊዜም ሐቀኛ ሁን። እነሱም በአንድ ወቅት ወጣቶች እንደነበሩ አትዘንጋ፤ ደግሞም አንተን በደንብ ያውቁሃል። ስለዚህ ለመሄድ የፈለግህበትን ትክክለኛ ምክንያት ልትደብቃቸው ብትሞክርም እንኳ ማወቃቸው አይቀርም። እውነቱን ብትነግራቸው ግን ደስ ይላቸዋል፤ አንተም ብትሆን እነሱ ከሚሰጡህ ጥበብ ያዘለ ምክር ትጠቀማለህ። (ምሳሌ 7:1, 2) በሌላ በኩል ግን ሐቀኛ ካልሆንህ በእነሱ ዘንድ ያለህን አመኔታ የምታጣ ከመሆኑም በላይ ፈቃድ የማግኘት አጋጣሚህ የጠበበ ይሆናል።

 ጊዜ ምረጥ። ወላጆችህ ሥራ ውለው ገና እግራቸው ቤት ከመርገጡ ወይም አእምሯቸው በሌሎች ጉዳዮች ተወጥሮ ባለበት ሰዓት ጥያቄ ማቅረብ ወይም ፈቃድ እንዲሰጡህ መጎትጎት ጥበብ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ዘና በሚሉበት ጊዜ ጠይቃቸው። በሌላ በኩል ደግሞ ቀኑ እስኪደርስ አትጠብቅ፤ ባለቀ ሰዓት መጠየቅና መልስ እንዲሰጡህ መጎትጎት አያዋጣም። ወላጆችህ የችኮላ ውሳኔ ማድረግ አይፈልጉም። ቀደም ብለህ ብትጠይቃቸው ግን በጉዳዩ ላይ ለማሰብ ጊዜ ያገኛሉ።

 የተሟላ መረጃ ስጥ። ፈቃድ ስትጠይቅ ግልጽ ያልሆነ ነገር ከመናገር ይልቅ ማድረግ የፈለግኸውን ነገር በዝርዝር ንገራቸው። ወላጆችህ “እነማን ይገኛሉ?” “ኃላፊነት የሚሰማው ትልቅ ሰው በቦታው ይኖራል?” ወይም “ስንት ሰዓት ትመለሳለህ?” ብለው ሲጠይቁህ “እኔ እንጃ” የሚል መልስ የምትሰጥ ከሆነ ስጋት ሊያድርባቸው ይችላል።

 ጥሩ አመለካከት ይኑርህ። ወላጆችህን እንደ ጠላት አትያቸው። ከዚህ ይልቅ ከአንተ ጎን እንደቆሙ አድርገህ ተመልከታቸው፤ ደግሞም ቆም ብለህ ካሰብህበት እውነታው ይህ ነው። ወላጆችህ ከጎንህ እንደሆኑ የምታስብ ከሆነ ስትናገር ቆጣ ቆጣ ከማለት ትቆጠባለህ፤ ይህ ደግሞ እንዲፈቅዱልህ ሊያነሳሳቸው ይችላል።

 የወላጆችህን ውሳኔ በመቀበልና በመታዘዝ ብስለት እንዳለህ ማሳየት ትችላለህ። እንዲህ ካደረግህ እነሱም ያከብሩሃል። ደግሞም በሌላ ጊዜ ፈቃድ ስትጠይቃቸው በተቻለ መጠን አንተን ለማስደሰት ጥረት ያደርጋሉ።