በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

የወጣቶች ጥያቄ

ወላጆቼ ስላወጧቸው ሕጎች ከእነሱ ጋር መነጋገር የምችለው እንዴት ነው?

ወላጆቼ ስላወጧቸው ሕጎች ከእነሱ ጋር መነጋገር የምችለው እንዴት ነው?

የሚያስፈልግህ ነገር፦ የሐሳብ ልውውጥ የማድረግ ችሎታ

የሐሳብ ልውውጥ የማድረግ ችሎታ የሚከተሉትን ነገሮች ለማድረግ አስፈላጊ ነው፦

  • ሌሎች ስሜትህን እንዲረዱህ ለማድረግ

  • የፈለግኸውን እንዳታደርግ ያልተፈቀደልህ ለምን እንደሆነ ለማወቅ

በእርግጥም፣ እንደ አዋቂ መታየት ከፈለግህ ንግግርህም እንደ አዋቂ ሊሆን ይገባል። ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

ስሜትህን መቆጣጠር ተማር። ጥሩ ውይይት ለማድረግ ራስህን መግዛት ያስፈልግሃል። መጽሐፍ ቅዱስ “ተላላ ሰው ቍጣውን ያለ ገደብ ይለቀዋል፤ ጠቢብ ሰው ግን ራሱን ይቈጣጠራል” ይላል።ምሳሌ 29:11

ከዚህ ምን ትምህርት ታገኛለህ? አትነጫነጭ፤ አታኩርፍ፤ በር አታላትም ወይም እየተመናጨቅክ አትሂድ። ይህ ዓይነቱ ባሕርይ ይበልጥ ነፃነት ከማስገኘት ይልቅ ተጨማሪ ገደቦች እንዲጣሉብህ ሊያደርግ ይችላል።

የወላጆችህን አመለካከት ለመረዳት ሞክር። ለምሳሌ ያህል፣ ወላጆችህ ወደ አንድ ግብዣ እንድትሄድ አልፈቀዱልህም እንበል። ከእነሱ ጋር ከመከራከር ይልቅ እንዲህ ብለህ ልትጠይቃቸው ትችላለህ፦

“በሳል የሆነና እምነት የሚጣልበት ሰው ከእኔ ጋር ቢሄድስ?”

እርግጥ እንዲህ ብትልም ወላጆችህ የጠየቅከውን ነገር ላይፈቅዱልህ ይችላሉ። ሆኖም ያሳሰባቸው ምን እንደሆነ ለመረዳት መሞከርህ ተቀባይነት ያለው ሌላ ሐሳብ ለማቅረብ ያስችልሃል።

የወላጆችን መመሪያ መታዘዝ የባንክ ዕዳን ከመክፈል ጋር ይመሳሰላል፤ እምነት የሚጣልብህ በሆንክ መጠን ተጨማሪ ብድር ታገኛለህ፤ በሌላ አባባል የበለጠ አመኔታ ታተርፋለህ

ወላጆችህ እንዲተማመኑብህ አድርግ። አንድ ሰው ከባንክ ገንዘብ ተበድሯል እንበል። ይህ ሰው ዕዳውን ሁልጊዜ የሚከፍለው በወቅቱ ከሆነ የባንኩን አመኔታ ስለሚያተርፍ ባንኩ ወደፊት ተጨማሪ ብድር ሊሰጠው ይችላል።

ከወላጆችህ ጋር ባለህ ግንኙነትም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ወላጆችህን የመታዘዝ “ዕዳ” አለብህ። በመሆኑም የወላጆችህን ትእዛዝ በተደጋጋሚ የምትጥስ ከሆነ ወላጆችህ በአንተ ላይ ያላቸው እምነት ቢቀንስ ወይም እስከነጭራሹ ቢጠፋ ልትገረም አይገባም።

በሌላ በኩል ግን በትናንሽ ነገሮችም እንኳ እምነት የሚጣልብህ መሆንህን ካስመሠከርክ በወላጆችህ ዘንድ የበለጠ አመኔታ ታተርፋለህ።