መጽሐፍ ቅዱስ ‘በልማዶቻችን ልከኛ እንድንሆን’ ያበረታታል። (1 ጢሞቴዎስ 3:2) ይህ ደግሞ የአመጋገብ ልማድንም ይጨምራል። ለምን የሚከተሉትን ነገሮች ተግባራዊ ለማድረግ አትሞክሪም? *

^ አን.3 በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የተጠቀሱት ነጥቦች ለሁለቱም ፆታዎች ይሠራሉ።

ልክን ማወቅ፦ የ19 ዓመቷ ጁሊያ እንዲህ ብላለች፦ “የምበላው ምግብ ምን ያህል ካሎሪ እንዳለው የማስላት ልማድ ነበረኝ፤ አሁን ግን ሆዴ እንደሞላ ሲሰማኝ መብላት አቆማለሁ።

ለጤና የማይጠቅሙ ምግቦችን አለመመገብ፦ የ21 ዓመቱ ፒተር “ለስላሳ መጠጣት ሳቆም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ አምስት ኪሎ ቀነስኩ!” ብሏል።

የአመጋገብ ልማድን ማስተካከል፦ ኤሪን የተባለች የ19 ዓመት ወጣት “ደጋግሜ እየጨመርኩ ላለመብላት ጥረት አደርጋለሁ” በማለት ተናግራለች።

ቁልፉ፦ ቁርስም ሆነ ምሳ አሊያም ራት አትዝለዪ! እንዲህ ማድረግ በጣም ስለሚያስርብሽ ብዙ ልትበዪ ትችያለሽ።

እርግጥ ነው፣ የክብደታቸው ጉዳይ የሚያሳስባቸው አንዳንድ ሰዎች ስለ መልካቸው ያላቸው አመለካከት የተዛባ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ እነዚህ ሰዎች ክብደት መቀነስ አያስፈልጋቸውም። ይሁንና በእርግጥ ክብደት መቀነስ የሚያስፈልግሽ ከሆነ ምን ማድረግ ትችያለሽ? ካትሪን የተባለች ወጣት ምን እንዳለች ልብ በዪ።

“በአሥራዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ ሳለሁ ከመጠን በላይ ወፍራም ነበርኩ፤ እንደዚያ መሆን ደግሞ ፈጽሞ አልፈልግም ነበር። ቁመናዬ ስለሚያስጠላኝ ደስተኛ አልነበርኩም! ከዚህም ሌላ ጤንነት አይሰማኝም ነበር።

“ለየት ያለ የአመጋገብ ሥርዓት በመከተል ክብደት ለመቀነስ የሞከርኩባቸው ጊዜያት ቢኖሩም መልሼ እወፍር ነበር። ስለዚህ 15 ዓመት ሲሆነኝ ትልቅ ለውጥ ለማድረግ ቆርጬ ተነሳሁ። ውፍረቴን መቀነስ ያለብኝ በትክክለኛው መንገድ ይኸውም ሁልጊዜ ልከተለው የምችል ልማድ በማዳበር እንደሆነ ወሰንኩ።

“ስለተመጣጠነ ምግብና ስለ ሰውነት እንቅስቃሴ የሚናገር መጽሐፍ ገዛሁና ያነበብኩትን ነገር ተግባራዊ ማድረግ ጀመርኩ። ፕሮግራሜን መከተል ቢያቅተኝ ወይም ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር ቢያጋጥመኝም እንኳ ጥረት ማድረጌን ከነጭራሹ ላለመተው ቆርጬ ነበር።

“ባይገርማችሁ ተሳካልኝ! በአንድ ዓመት ውስጥ ከ25 ኪሎ ግራም በላይ ቀነስኩ። ከዚያ በኋላ ለሁለት ዓመት ያህል ክብደት ሳልጨምር በዚያው መቀጠል ቻልኩ። ይህ ይሆናል ብዬ ፈጽሞ አላሰብኩም ነበር!

“ሊሳካልኝ የቻለው የአመጋገብ ልማዴን ስላስተካከልኩ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ለውጥ ስላደረግሁ እንደሆነ ይሰማኛል።”​—ካትሪን፣ 18