በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ከአስተማሪዬ ጋር ለመስማማት ምን ላድርግ?

ከአስተማሪዬ ጋር ለመስማማት ምን ላድርግ?

እስቲ ቆም ብለህ አስብ!

ሬቸል ያጋጠማትን ሁኔታ እንመልከት። ሬቸል ምንጊዜም ከፍተኛ ውጤት ታገኝ ነበር። ሰባተኛ ክፍል ስትደርስ ግን ሁኔታዎች ተለወጡ። ሬቸል “ከአስተማሪዎቼ አንዱ እኔን ለመጣል የማያደርገው ነገር አልነበረም” ብላለች። ችግሩ ምን ነበር? አስተማሪው የሬቸልንም ሆነ የእናቷን ሃይማኖት እንደሚጠላው በግልጽ ይታይ ነበር።

አስተማሪዎች፣ ውኃ ላይ እንዳሉ የመሸጋገሪያ ድንጋዮች ካለማወቅ ወደ ማወቅ እንድትሸጋገር ይረዱሃል፤ መሸጋገሪያውን መጠቀም ግን የአንተ ድርሻ ነው

ታዲያ ሬቸል ምን አደረገች? እንዲህ ብላለች፦ “አስተማሪዬ ውጤቴን የሚያበላሸው እኛን በእምነታችን ስለሚጠላን እንደሆነ በሚሰማን ጊዜ እናቴ መጥታ ታነጋግረዋለች። ውሎ አድሮ ይህን ማድረጉን አቆመ።”

አንተም ተመሳሳይ ሁኔታ ካጋጠመህ ጉዳዩን ለወላጆችህ ከመናገር ወደኋላ አትበል። ወላጆችህ ለጉዳዩ መፍትሔ ለማግኘት ከአስተማሪህ እንዲሁም ከትምህርት ቤቱ ኃላፊዎች ጋር መነጋገራቸው አይቀርም።

እርግጥ ነው፣ ሁሉም ዓይነት ችግሮች በቀላሉ መፍትሔ ያገኛሉ ማለት አይደለም። አንዳንድ ጊዜ ሁኔታውን ችሎ ከመኖር ሌላ አማራጭ አይኖርህ ይሆናል። (ሮም 12:17, 18) ታንያ እንዲህ ብላለች፦ “አንደኛው አስተማሪያችን ለተማሪዎቹ ጥሩ አመለካከት አልነበረውም። ብዙውን ጊዜ ‘ደደቦች’ እያለ ይሰድበን ነበር። መጀመሪያ ላይ አስተማሪያችን ሲሰድበን አለቅስ ነበር፤ እያደር ግን ችግሩ ከእኔ ጋር ብቻ እንዳልሆነ ተገነዘብኩ። ትምህርቴ ላይ ትኩረት ለማድረግ መጣር ጀመርኩ። በመሆኑም የሚናገረው ነገር ያን ያህል አይረብሸኝም፤ እንዲያውም በእሱ ትምህርት ጥሩ ውጤት ካመጡት ጥቂት ተማሪዎች መካከል አንዷ መሆን ቻልኩ። ከሁለት ዓመት በኋላ አስተማሪው ተባረረ።”

ሊታሰብበት የሚገባው ነገር፦ አስቸጋሪ ከሆነ አስተማሪ ጋር እንዴት መስማማት እንደምትችል ማወቅህ ጥሩ ሥልጠና ይሰጥሃል፤ ወደፊት እንዲህ ያለ ባሕርይ ያለው አሠሪ ቢያጋጥምህ እንዴት ልትይዘው እንደሚገባ ታውቃለህ። (1 ጴጥሮስ 2:18) ከዚህም በላይ ጥሩ አስተማሪዎች ሲገጥሙህ ይበልጥ ታደንቃቸዋለህ።