በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

ኃላፊነት የሚሰማው ሰው ነኝ?

ኃላፊነት የሚሰማው ሰው ነኝ?

 ራስህን ገምግም!

 •  ከታች ያሉትን ባሕርያት በማሳየት ረገድ እንዴት ነህ? እነዚህን ባሕርያት በሕይወትህ ውስጥ የሚታዩት ሁልጊዜ፣ አብዛኛውን ጊዜ ወይም አልፎ አልፎ ነው? ወይስ ጨርሶ አይታዩም?

  •  ሐቀኛ

  •  እምነት የሚጣልበት

  •  ሰዓት አክባሪ

  •  ታታሪ ሠራተኛ

  •  ሥርዓታማ

  •  ሌሎችን የሚረዳ

  •  ፍትሐዊ

  •  ሰው አክባሪ

  •  አሳቢ

 •   ከእነዚህ ባሕርያት ውስጥ አንተን በደንብ የሚገልጸው የትኛው ነው?

   ይህን ባሕርይ በደንብ ማንጸባረቅህን ቀጥል።​—ፊልጵስዩስ 3:16

 •   ይበልጥ ልትሠራበት የሚገባው ባሕርይ የትኛው ነው?

 የሚከተሉት ሐሳቦች በዚህ ረገድ ማሻሻያ ለማድረግ ይረዱሃል።

 ኃላፊነት የሚሰማው ሰው መሆን ሲባል ምን ማለት ነው?

 ኃላፊነት የሚሰማው ሰው በቤቱ፣ በሚማርበት ቦታና በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለበትን ኃላፊነት ይወጣል። እንዲሁም ለሚያደርገው ድርጊት ተጠያቂ መሆኑን ይገነዘባል። በመሆኑም ስህተት ሲሠራ ጥፋቱን የሚያምን ከመሆኑም ሌላ ይቅርታ ጠይቆ ስህተቱን ለማረም ይጥራል።

  መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “እያንዳንዱ የራሱን የኃላፊነት ሸክም ይሸከማል።”​—ገላትያ 6:5

 ኃላፊነት የሚሰማው ሰው መሆን ያለብኝ ለምንድን ነው?

ኃላፊነት የሚሰማው ሰው ተሰጥኦውን የሚጠቀመው በጥበብ ሲሆን ሰዎችም ከፍ አድርገው ይመለከቱታል፤ በተጨማሪም እንደ ትልቅ ሰው የሚታይ ከመሆኑም በላይ ነፃነትና መብት ያገኛል።

  መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “በሙያው ሥልጡን የሆነውን ሰው አይተሃልን? በነገሥታት ዘንድ ባለሟል ይሆናል።”​—ምሳሌ 22:29

ኃላፊነት የሚሰማው ሰው አብዛኛውን ጊዜ ለጋስ ነው፤ እንዲሁም ጥሩ ጓደኞች ይኖሩታል።

  መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ሰጪዎች ሁኑ፤ ሰዎችም ይሰጧችኋል።”​—ሉቃስ 6:38

ኃላፊነት የሚሰማው ሰው በሥራው እርካታ የሚያገኝ ከመሆኑም በላይ በሥራው ይኮራል፤ ይህም በራስ የመተማመን ስሜቱን ከፍ ያደርግለታል።

  መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “እያንዳንዱ ሰው የራሱን ሥራ ምንነት ፈትኖ ያሳይ፤ ከዚያም . . . ከራሱ ጋር ብቻ በተያያዘ የሚመካበት ነገር ያገኛል።”​—ገላትያ 6:4

 ይበልጥ ኃላፊነት የሚሰማው ሰው መሆን የምችለው እንዴት ነው?

 ይህን ጥያቄ ለመመለስ እንዲረዳህ የሚከተሉትን ሐሳቦች ተመልከት። አንተ የሚሰማህን ስሜት ይበልጥ የሚገልጸው የትኛው ነው?

 “ሁልጊዜ እንደ ሕፃን ልጅ መታየት በጣም ያበሳጫል፤ እናትና አባቴ የት እንደሆንኩ ሳልነግራቸው ለአንድ ሰዓት እንኳ ጊዜ እንዳሳልፍ አይፈቅዱልኝም!”​—ኬሪ

 “ከጓደኞቼ ጋር ወጣ ማለት ስፈልግ አብዛኛውን ጊዜ ወላጆቼ ወዲያውኑ ይፈቅዱልኛል።”​—ሪቻርድ

 “እኩዮቼ ማድረግ የሚፈቀድላቸውን ነገር ባየሁ ቁጥር ‘እንዴ! ወላጆቼ እንዲህ እንዳደርግ የማይፈቅዱልኝ ለምንድን ነው?’ ብዬ አስባለሁ።”​—አን

 “ወላጆቼ የፈለኩትን እንዳደርግ ይፈቅዱልኛል ማለት እችላለሁ። እንዲህ ያለ ነፃነት ስለሰጡኝ በጣም አመሰግናቸዋለሁ።”​—ማሪና

 ዋናው ነጥብ፦ አንዳንድ ወጣቶች ከሌሎች ይልቅ ነፃነት ይሰጣቸዋል። ለምን?

 የሕይወት እውነታ፦ አብዛኛውን ጊዜ፣ የሚሰጥህ ነፃነት የተመካው ባተረፍከው አመኔታ ላይ ነው።

 ለምሳሌ ያህል፣ ከላይ ከተጠቀሱት ወጣቶች መካከል ሁለቱ ምን እንዳሉ ተመልከት።

 ሪቻርድ፦ “በአንድ ወቅት ወላጆቼ ነፃነቴን ስለምጠቀምበት መንገድ ጥርጣሬ አድሮባቸው ነበር። አሁን ግን ነፃነቴን የምጠቀምበት ኃላፊነት እንደሚሰማኝ በሚያሳይ መንገድ መሆኑን በማየታቸው እምነት ጥለውብኛል። የት እንደምሄድ ወይም ከማን ጋር እንደምሄድ ፈጽሞ አልዋሻቸውም። እንዲያውም አብዛኛውን ጊዜ፣ እነሱ ሳይጠይቁኝ ምን ላደርግ እንዳሰብኩ አስቀድሜ እነግራቸዋለሁ።”

 ማሪና፦ “በሕይወቴ ወላጆቼን የዋሸኋቸው ሁለት ጊዜ ብቻ ነው፤ ደግሞም በሁለቱም ወቅት እንደዋሸሁ ታውቆብኛል። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ምንጊዜም ለወላጆቼ ሐቀኛ ነኝ። ለምሳሌ ያህል፣ ምን እያደረኩ እንደሆነ በዝርዝር እነግራቸዋለሁ፤ እንዲሁም ወደ ውጪ ስወጣ እደውልላቸዋለሁ። አሁን በእኔ ላይ የበለጠ እምነት አላቸው።”

የምታስቀድመው የቱን ነው?​—የቤት ውስጥ ሥራን ወይስ መዝናኛን?

 አንተስ ወላጆችህ እንደ ሪቻርድና ማሪና እንዲመለከቱህ ትፈልጋለህ? ከሆነ የሚከተሉትን ነጥቦች አስብባቸው፦

ቤት

 •   የተሰጠህን የቤት ውስጥ ሥራ በታማኝነት ታከናውናለህ?

 •   የወጣልህን ቤት መግቢያ ሰዓት ታከብራለህ?

 •   ወላጆችህን እንዲሁም ወንድሞችህንና እህቶችህን በአክብሮት ትይዛለህ?

 ከእነዚህ መካከል ልትሠራባቸው የሚገቡ ነጥቦች አሉ?

  መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ለወላጆቻችሁ ታዘዙ።”​—ኤፌሶን 6:1

ትምህርት ቤት

 •   የቤት ሥራህን በተሰጠህ የጊዜ ገደብ ታጠናቅቃለህ?

 •   ውጤትህን ለማሻሻል ጥረት እያደረግህ ነው?

 •   ጥሩ የጥናት ልማድ አለህ?

 ከእነዚህ መካከል ልትሠራባቸው የሚገቡ ነጥቦች አሉ?

  መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ ‘ጥበብ ጥላ ከለላ ነው።’ (መክብብ 7:12) ጥሩ ትምህርት ጥበብን እንድታዳብር ይረዳሃል።

ያተረፍከው ስም

 •   ለወላጆችህም ሆነ ለሌሎች ሰዎች ሐቀኛ ነህ?

 •   ገንዘብህን የምትጠቀመው ኃላፊነት የሚሰማው ሰው እንደሆንክ በሚያሳይ መንገድ ነው?

 •   እምነት የሚጣልበት የሚል ስም አትርፈሃል?

 ከእነዚህ መካከል ልትሠራባቸው የሚገቡ ነጥቦች አሉ?

  መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ ‘አዲሱን ስብዕና ልበሱ።’ (ኤፌሶን 4:24) ባሕርይህን ማሻሻል እንዲሁም ጥሩ ስም ማትረፍ ትችላለህ።

 የመፍትሔ ሐሳብ፦ ማሻሻያ ማድረግ የሚያስፈልግህን አንድ ዘርፍ ምረጥ። ከዚያም በዚህ ረገድ ጥሩ ስም ያተረፉ ሰዎች ምክር እንዲሰጡህ ጠይቅ። ይህን ባሕርይ ለማዳበር ማድረግ ያሉብህን ነገሮች ለይተህ ጻፍ፤ ከዚያም ምን መሻሻል እንዳደረግክ ለአንድ ወር ያህል ተከታተል። ያገኘኸውን ስኬትና ማድረግ ያቃተህን ነገር ማስታወሻህ ላይ መዝግብ። በወሩ መጨረሻ ላይ ምን ያህል እድገት እንዳደረግክ ገምግም።