በዚህ ረገድ የሚረዱህ ነገሮች ከዚህ በታች ቀርበዋል

ለትምህርት አዎንታዊ አመለካከት ይኑርህ። ጉዳዩን ሰፋ አድርገህ ለመመልከት ሞክር። በሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥ ከተካተቱት የትምህርት ዓይነቶች አንዳንዶቹ ቢያንስ ለአሁኑ ሕይወትህ እንደማይጠቅሙህ ይሰማህ ይሆናል። ያም ቢሆን ስለተለያዩ የትምህርት ዓይነቶች እውቀት መቅሰምህ በዙሪያህ ስላለው ዓለም ግንዛቤህን ያሰፋልሃል። ይህም “ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ሁሉንም ነገር [መሆን]” እንድትችል ስለሚረዳህ የተለያየ ባሕልና አስተዳደግ ካላቸው ሰዎች ጋር ለመግባባት ያስችልሃል። (1 ቆሮንቶስ 9:22) ሌላው ቢቀር የማመዛዘን ችሎታህን ያሻሽልልሃል፤ ይህ ደግሞ ለወደፊት ሕይወትህ እንደሚጠቅምህ ምንም ጥርጥር የለውም።

የትምህርት ቤት ሕይወትን ማለፍ ጥቅጥቅ ካለ ደን ለመውጣት የሚያስችል መንገድ ከመክፈት ጋር ሊመሳሰል ይችላል፤ ትክክለኛውን መሣሪያ ከተጠቀምክ ግን ሁለቱንም በተሳካ ሁኔታ መወጣት ትችላለህ

ለአስተማሪህ አዎንታዊ አመለካከት ይኑርህ። አስተማሪህ የሚያስተምርበት መንገድ አሰልቺ ከሆነብህ በእሱ ላይ ሳይሆን በትምህርቱ ላይ ትኩረት ለማድረግ ሞክር። አስተማሪህ አንድን የትምህርት ዓይነት ለተለያዩ ተማሪዎች በመቶዎች ለሚቆጠሩ ጊዜያት አስተምሮ ሊሆን እንደሚችል አስታውስ። ስለዚህ መጀመሪያ ሲያስተምር ያደርግ እንደነበረው ትምህርቱን በግለት ማቅረብ ፈታኝ ሊሆንበት ይችላል።

ጠቃሚ ምክር፦ ማስታወሻ ያዝ፤ ጥያቄ ሲኖርህ በአክብሮት ጠይቅ፤ እንዲሁም ትምህርቱን በጉጉት ለመከታተል ጥረት አድርግ። አንተ ለትምህርቱ ያለህ ጉጉት ሌሎችም ተመሳሳይ ስሜት እንዲኖራቸው ያደርጋል።

ላሉህ ችሎታዎች ተገቢ አመለካከት ይኑርህ። በትምህርት ቤት የምትቀስመው ትምህርት የተደበቁ ተሰጥኦዎችህን ለማወቅ ሊረዳህ ይችላል። ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ “የተቀበልከውን የአምላክ ስጦታ እንደ እሳት እንድታቀጣጥል አሳስብሃለሁ” በማለት ጽፎለታል። (2 ጢሞቴዎስ 1:6) ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው ጢሞቴዎስ፣ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት የተሰጠው ስጦታ ነበረው። ሆኖም ይህ “ስጦታ” በውስጡ ታፍኖ እንዳይቀር ወይም እንዳይባክን ሊያዳብረው ይገባ ነበር። እርግጥ ነው፣ በትምህርት ቤት የሚኖርህ ችሎታ በቀጥታ ከአምላክ ያገኘኸው ስጦታ አይደለም። ያም ቢሆን ከሌሎች የተለየ የራስህ የሆነ ተሰጥኦ አለህ። ትምህርት ቤት መግባትህ፣ ከዚህ በፊት ያላስተዋልካቸው በውስጥህ የተቀበሩ አንዳንድ ችሎታዎች እንዳሉህ እንድታውቅና እነዚህን ችሎታዎች እንድታዳብራቸው ሊረዳህ ይችላል።