እስቲ ቀጥሎ የቀረቡትን ነጥቦች አስብባቸው

አንተ በምትኖርበት አካባቢ ያለው ሕግ የሚያዝዘው እስከ ስንተኛ ክፍል እንድትማር ነው? ታዲያ አንተ እዚያ ደረጃ ደርሰሃል? ’ለበላይ ባለሥልጣናት ተገዙ’ የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ችላ ብለህ ሕጉ የሚጠብቅብህ የትምህርት ደረጃ ላይ ሳትደርስ መማር ብታቆም ትምህርትህን አቋርጠሃል ማለት ነው።—ሮም 13:1

ያወጣሃቸው ግቦች ላይ ደርሰሃል? በትምህርት ቤት ቆይታህ የትኞቹ ግቦች ላይ መድረስ ትፈልጋለህ? እርግጠኛ አይደለህም? በዚህ ረገድ ግብ ሊኖርህ ይገባል! አለዚያ የት መሄድ እንደሚፈልግ ሳይወስን ባቡር ላይ እንደተሳፈረ መንገደኛ ነህ ማለት ነው። ስለዚህ “ የምማርበት ዓላማ” በሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር የሚገኘውን ክፍል ከወላጆችህ ጋር ሆነህ ተወያይበት። የምትማርበትን ዓላማ በተመለከተ አንተም ሆንክ ወላጆችህ ያወጣችኋቸው ግቦች ላይ ከመድረስህ በፊት መማር ብታቆም ትምህርትህን አቋርጠሃል ማለት ነው።

ትምህርት ማቋረጥ፣ ያሰብክበት ቦታ ከመድረስህ በፊት ከባቡር ላይ ዘለህ እንደ መውረድ ሊቆጠር ይችላል

ለማቋረጥ የፈለግኸው ለምንድን ነው? ምናልባት ሠርተህ ቤተሰብህን ለመርዳት ወይም ስለ አምላክ በመስበኩ ሥራ የበለጠ ለመካፈል አስበህ ይሆናል። ከፈተና ወይም የቤት ሥራ ከመሥራት መገላገል እንደሚሉት ያሉ አጥጋቢ ያልሆኑ ምክንያቶችም ታቀርብ ይሆናል። ተፈታታኝ የሚሆነው ጉዳይ ትምህርትህን ለማቋረጥ በዋነኝነት ያነሳሳህ ነገር አጥጋቢ ምክንያት ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ለይቶ ማወቁ ነው። ከችግሮች ለመሸሽ ብለህ ብቻ ትምህርትህን ብታቋርጥ ያላሰብከው ነገር ሊያጋጥምህ ይችላል።

ትምህርት ማቋረጥ፣ ያሰብክበት ቦታ ከመድረስህ በፊት ከባቡር ላይ ዘለህ እንደ መውረድ ሊቆጠር ይችላል። እርግጥ ባቡሩ ምቾት ላይኖረው ተሳፋሪዎቹ ደግሞ አስቸጋሪ ሊሆኑብህ ይችላሉ፤ ያም ሆኖ ከባቡሩ ላይ ዘለህ ብትወርድ ያሰብክበት ቦታ ሳትደርስ የምትቀር ከመሆኑም ሌላ ከባድ ጉዳት ሊያጋጥምህ ይችላል። በተመሳሳይም ትምህርትህን ብታቋርጥ ሥራ ማግኘት ከባድ ሊሆንብህ ይችላል። ሥራ ብታገኝ እንኳ አብዛኛውን ጊዜ ደሞዝህ ትምህርትህን ብትጨርስ ኖሮ ልታገኘው ከምትችለው ያነሰ ነው።

ትምህርትህን ከማቋረጥ ይልቅ በትምህርት ቤት የሚያጋጥሙህን ችግሮች በትዕግሥት ለመወጣት ጥረት አድርግ። እንዲህ ካደረግህ ጽናትን የምታዳብር ከመሆኑም ሌላ በሥራው ዓለም የሚያጋጥሙህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመቋቋም ዝግጁ ትሆናለህ።

 የምማርበት ዓላማ

የምትማርበት ዋነኛ ዓላማ ራስህን ለመቻል የሚረዳህ ሥልጠና ማግኘት ነው፤ ትምህርት፣ ወደፊት ትዳር ከመሠረትክ ለቤተሰብህ የሚያስፈልገውን ለማሟላት የሚያስችል ሥራ ለመያዝም ሊረዳህ ይችላል። (2 ተሰሎንቄ 3:10, 12) በሥራው ዓለም በምን መስክ መሰማራት እንደምትፈልግ ወስነሃል? ታዲያ በምትፈልገው የሥራ መስክ ለመሰማራት ሊረዳህ የሚችል ትምህርት እየቀሰምክ ነው? የምትከታተለው ትምህርት ግብህ ላይ ለመድረስ ያስችልህ እንደሆነ ለማወቅ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር፦

  • ምን ተሰጥኦዎች አሉኝ? (ለአብነት ያህል፣ ከሌሎች ጋር የመግባባት ችሎታ አለህ? የእጅ ሙያ አለህ? ለምሳሌ አንዳንድ ነገሮችን መሥራት ወይም መጠገን ያስደስትሃል? የችግሮችን መንስኤ በማወቅና መፍትሔ በማግኘት ረገድ ጥሩ ችሎታ አለህ?)

  • ችሎታዬን መጠቀም የምችለው ምን ዓይነት ሥራ ብይዝ ነው?

  • በምኖርበት አካባቢ ምን ዓይነት ሥራዎችን መሥራት ይቻላል?

  • ወደፊት ሥራ ለማግኘት የሚረዳኝ ምን ትምህርት እየተከታተልኩ ነው?

  • አሁን ከምከታተለው ትምህርት በተጨማሪ ግቦቼ ላይ ለመድረስ የሚረዱኝ ምን ሌሎች ትምህርቶች አሉ?

በሌላ በኩል ደግሞ ወደ ሌላው ጽንፍ እንዳትሄድ ተጠንቀቅ። የምትማርበት ዓላማ ጥሩ ሥልጠና አግኝተህ ሥራ መያዝ መሆኑን አትርሳ። በመሆኑም ኑሮ የሚያመጣቸውን ሌሎች ኃላፊነቶች መሸከም ስለሚያስፈራህ ብቻ “ከባቡሩ” ሳትወርድ እንዳትቀር በሌላ አባባል ዕድሜ ልክህን ተማሪ እንዳትሆን ተጠንቀቅ።