በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ብቸኝነትን ማሸነፍ የምችለው እንዴት ነው?

ብቸኝነትን ማሸነፍ የምችለው እንዴት ነው?

ምን ማድረግ ትችላለህ?

 1. በጠንካራ ጎኖችህ ላይ ማተኮር። (2 ቆሮንቶስ 11:6) ጉድለቶችህን ማወቁ ጥሩ ቢሆንም ብዙ ጠንካራ ጎኖችም እንዳሉህ አትርሳ። ጠንካራ ጎኖችህን ማወቅህ በራስ የመተማመን መንፈስ ለማዳበር ስለሚረዳህ ስለ ራስህ ያለህን አሉታዊ አመለካከት ለማስወገድ እንዲሁም ብቸኝነትን ለማሸነፍ ያስችልሃል። ‘ምን ጠንካራ ጎኖች አሉኝ?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ። ያሉህን አንዳንድ ተሰጥኦዎች ወይም ግሩም ባሕርያት ለማሰብ ሞክር።

 2. ከሌሎች ጋር ለመግባባት ልባዊ ጥረት ማድረግ። መጀመሪያ ላይ ከአንድ ሰው ጋር ለመግባባት መሞከር ትችላለህ። ሆርሄ የተባለ አንድ ወጣት እንደተናገረው “ሰዎችን ይበልጥ ለማወቅ ስለ ደኅንነታቸው ወይም ስለ ሥራቸው መጠየቅ ብቻ እንኳ በቂ ሊሆን ይችላል።”

ከእኩዮችህ ጋር እንዳትቀራረብ የሚያግድህን ገደል ለመሻገር ድልድይ መሥራት ትችላለህ

 ጠቃሚ ምክር፦ በአንተ ዕድሜ ላይ ከሚገኙ ሰዎች ጋር ብቻ ለመቀራረብ አትሞክር። በጣም ጥሩ ጓደኛሞች እንደነበሩ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተገለጹት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ሰፊ የዕድሜ ልዩነት ነበራቸው፤ ከእነዚህም መካከል ሩትና ኑኃሚን፣ ዳዊትና ዮናታን እንዲሁም ጢሞቴዎስና ጳውሎስ ይገኙበታል። (ሩት 1:16, 17፤ 1 ሳሙኤል 18:1፤ 1 ቆሮንቶስ 4:17) በተጨማሪም ጭውውት በሰዎች መካከል የሚደረግ የሐሳብ ልውውጥ እንጂ አንድ ሰው ብቻ የሚቆጣጠረው መድረክ አለመሆኑን አትዘንጋ። ሰዎች ከሚያዳምጣቸው ሰው ጋር መጨዋወት ደስ ይላቸዋል። በመሆኑም ዓይናፋር ከሆንክ አንድ ነገር አስታውስ፦ ከሰዎች ጋር ስትጨዋወት ብዙ ማውራት አይጠበቅብህም!

 3.የሌላውን ስሜት መረዳት።’ (1 ጴጥሮስ 3:8) አንድ ሰው በሚናገረው ነገር ባትስማማም እንኳ በትዕግሥት አዳምጠው። ትኩረትህን በሚያግባቧችሁ ነጥቦች ላይ በማድረግ ሐሳብ ለመስጠት ጥረት አድርግ። በአንድ ጉዳይ እንደማትስማማ መግለጽ እንዳለብህ ከተሰማህ ሐሳብህን በዘዴና በረጋ መንፈስ ተናገር።

 ጠቃሚ ምክር፦ ሰዎችን የምታናግረው ሌሎች አንተን እንዲያናግሩህ በምትፈልግበት መንገድ ሊሆን ይገባል። አላስፈላጊ ክርክር መጀመር ወይም በሌሎች ላይ ማሾፍ እንዲሁም ራስን በማመጻደቅ ሌሎችን መተቸት ወይም መንቀፍ ሰዎች እንዲርቁህ ያደርጋል። ’ንግግርህ ምንጊዜም ለዛ ያለው’ ከሆነ ግን ሰዎች የበለጠ ይወዱሃል።—ቆላስይስ 4:6