በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

በከፍተኛ ሐዘን ስዋጥ ምን ማድረግ እችላለሁ?

በከፍተኛ ሐዘን ስዋጥ ምን ማድረግ እችላለሁ?

“ጓደኞቼ ችግር ሲያጋጥማቸው ቶሎ የምደርስላቸውና የማጽናናቸው እኔ ነኝ። ቤቴ ስሆን ግን መኝታ ክፍሌ ገብቼ ስቅስቅ ብዬ አለቅሳለሁ፤ ይህን የሚያውቁት ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው።”​—⁠ኬሊ

“በጣም ሲከፋኝ ብቻዬን መሆን እፈልጋለሁ። የተጋበዝኩበት ቦታ ካለም ላለመሄድ ሰበብ እፈጥራለሁ። ቤተሰቦቼ እንደማዝን እንዳያውቁ በጣም ስለምጠነቀቅ ችግር እንዳለብኝ አይሰማቸውም።”​—⁠ሪክ

ኬሊ ወይም ሪክ የተሰማቸው ዓይነት ስሜት ተሰምቶህ ያውቃል? ከሆነ፣ ችግር አለብኝ ብለህ ለመደምደም አትቸኩል። እውነቱን ለመናገር፣ ሁሉም ሰው አልፎ አልፎ በሐዘን መዋጡ አይቀርም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች እንኳ እንዲህ ያለ ስሜት ተሰምቷቸው ያውቃል።​—⁠1 ሳሙኤል 1:6-8፤ መዝሙር 35:14

አንዳንድ ጊዜ በሐዘን እንድትዋጥ ያደረገህ ምክንያት ሊኖር ይችላል፤ በሌሎች ጊዜያት ግን ምን እንዳሳዘነህ እንኳ ግራ ይገባህ ይሆናል። የ19 ዓመቷ አና እንዲህ ብላለች፦ “የከፋ ነገር ባይደርስባችሁም እንኳ ልታዝኑ ትችላላችሁ። በሕይወታችሁ ውስጥ ያጋጠማችሁ ችግር ባይኖርም በማንኛውም ጊዜ እንዲህ ዓይነት ስሜት ሊሰማችሁ ይችላል። ነገሩ ግራ የሚያጋባ ቢሆንም ሊያጋጥም የሚችል ነው!”

እንድታዝን ያደረገህ ነገር ምንም ይሁን ምን ሌላው ቀርቶ በሐዘን የተዋጥከው አለምንም ምክንያት እንደሆነ ቢሰማህም እንኳ እንዲህ ካለው ሁኔታ ለመላቀቅ ምን ማድረግ ትችላለህ? የሚከተሉትን ሐሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ ሞክር፦

 1. ስሜትህን አውጥተህ ተናገር። ኢዮብ ሕይወቱ ምስቅልቅሉ በወጣበት ጊዜ ‘በነፍሴ ምሬት እናገራለሁ’ ብሎ ነበር።​—⁠ኢዮብ 10:1

  ኬሊ፦ “ስሜቴን አውጥቼ ስናገር ትልቅ እፎይታ አገኛለሁ። ምን እየተሰማኝ እንዳለ የሚያውቅ ሰው መኖሩ በራሱ ያጽናናኛል። ከገባሁበት አዘቅት በገመድ ጎትተው ያወጡኝ ያህል ይሰማኛል!”

 2. ስሜትህን በጽሑፍ አስፍረው። በሚሰማህ ሐዘን የተነሳ ሁሉ ነገር ሲጨልምብህና ብሩህ ነገር አልታይ ሲልህ ስሜትህን በጽሑፍ ማስፈርህ ሊረዳህ ይችላል። ዳዊት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን በመንፈስ ተመርቶ በጻፋቸው መዝሙሮች ላይ የገለጸባቸው ጊዜያት ነበሩ። (መዝሙር 6:6) ስሜትህን በጽሑፍ ማስፈርህ ነገሮችን ‘በጥበብና በማስተዋል’ እንድትመለከት ይረዳሃል።​—⁠ምሳሌ 3:21 የ1980 ትርጉም

  ሄዘር፦ “በሐዘን ስዋጥ መያዣ መጨበጫ የሌላቸው በርካታ ሐሳቦች በአእምሮዬ ይጉላላሉ፤ ስሜቴን በጽሑፍ ማስፈሬ ሐሳቤን ለማሰባሰብ ይረዳኛል። ስሜትህን መግለጽህና እንድታዝን ያደረገህ ምን እንደሆነ መረዳትህ ሐዘንህ ቀለል እንዲልልህ ያደርጋል።”

 3. ስለ ጉዳዩ ጸልይ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ስለሚያሳስብህ ነገር የምትጸልይ ከሆነ ‘ከማሰብ ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም ልብህንና አእምሮህን እንደሚጠብቅ’ ይናገራል።​—⁠ፊልጵስዩስ 4:6, 7

  ኤስተር፦ “እንዳዝን ያደረገኝ ምን እንደሆነ ለማሰብ ብሞክርም ምንም ሊመጣልኝ አልቻለም። ደስተኛ እንድሆን እንዲረዳኝ ይሖዋን ለመንኩት። አለምንም ምክንያት በሐዘን መዋጤ ያበሳጨኝ ነበር። በመጨረሻ ግን ከሐዘን መላቀቅ ቻልኩ። ጸሎት ያለውን ኃይል ፈጽሞ አቅልላችሁ አትመልከቱት!”

  ሌሎች የሚሰጡህን እርዳታ ከተቀበልህና ጥረት ማድረግህን ከቀጠልህ ካለህበት አዘቅት መውጣት ትችላለህ

  የመፍትሔ ሐሳብ፦ ወደ ይሖዋ በምትጸልይበት ጊዜ መዝሙር 139:23, 24ን እንደ ናሙና መጠቀም ትችላለህ። የልብህን አውጥተህ ለይሖዋ ንገረው፤ እንዲሁም እንድታዝን ያደረገህን ምክንያት ለማወቅ እንዲረዳህ ጠይቀው።

ከላይ ከተጠቀሱት የመፍትሔ ሐሳቦች በተጨማሪ የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ከፍተኛ እርዳታ ሊያበረክትልህ ይችላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖርህ የሚረዱ ሐሳቦችን ማንበብህ ስሜትህን ሊያረጋጋልህ ይችላል።​—⁠መዝሙር 1:1-3

የሐዘን ስሜትህን ማሸነፍ ሲያቅትህ

ራያን የተባለ ወጣት “መኖር ትርጉም የለሽ ስለሆነብኝ ጠዋት ከእንቅልፌ ስነቃ ከአልጋ መውጣት የሚያስጠላኝ ጊዜ አለ” በማለት ተናግሯል። ራያን ከባድ የመንፈስ ጭንቀት አለበት፤ እንደ ራያን በዚህ ሕመም የሚሠቃዩ በርካታ ወጣቶች አሉ። አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከ4 ወጣቶች 1ዱ ለአካለ መጠን ከመድረሱ በፊት የመንፈስ ጭንቀት ይይዘዋል።

አንተስ የመንፈስ ጭንቀት ይዞህ እንደሆነ እንዴት ማወቅ ትችላለህ? የመንፈስ ጭንቀት ያለበት ሰው ከሚታዩበት ምልክቶች መካከል ጉልህ የስሜትና የጠባይ መለዋወጥ፣ ራስን ማግለል፣ ምንም ነገር የማድረግ ፍላጎት ማጣት፣ ከፍተኛ የአመጋገብ ለውጥ፣ የእንቅልፍ መዛባት እንዲሁም ሥር የሰደደ የዋጋ ቢስነት ስሜት ወይም መሠረት የሌለው የጥፋተኝነት ስሜት ይገኙበታል።

እርግጥ ነው፣ ከላይ ከተጠቀሱት ምልክቶች መካከል አንዳንዶቹ አልፎ አልፎ በማንኛውም ሰው ላይ ሊታዩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ምልክቶቹ ከሁለት ሳምንት በላይ ከቆዩ ወላጆችህ ወደ ሐኪም ቤት እንዲወስዱህ ጠይቃቸው። ሐኪሙ፣ ጥልቅ የሐዘን ስሜት የሚሰማህ በመንፈስ ጭንቀት ምክንያት መሆን አለመሆኑን ሊነግርህ ይችላል።

የመንፈስ ጭንቀት ካለብህ ይህ ሊያሳፍርህ አይገባም። እንዲህ ዓይነት ሕመም ያለባቸው በርካታ ሰዎች የሕክምና እርዳታ በማግኘታቸው ጤንነታቸው ተሻሽሏል፤ በዚህም ምክንያት ለረጅም ጊዜ ተሰምቷቸው የማያውቅ ጥሩ ስሜት ሊሰማቸው ችሏል! ለሐዘንህ መንስኤ የሆነው ነገር የመንፈስ ጭንቀት ሆነም አልሆነ፣ በ⁠መዝሙር 34:18 ላይ የሚገኘውን “እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል” የሚለውን የሚያጽናና ሐሳብ አስታውስ።