በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

በአፍ የሚፈጸም ወሲብ የፆታ ግንኙነት ነው ሊባል ይችላል?

በአፍ የሚፈጸም ወሲብ የፆታ ግንኙነት ነው ሊባል ይችላል?

 የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል ያወጣው አንድ ሪፖርት እንደገለጸው ከሆነ ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው ከ15 እስከ 19 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ወጣቶች መካከል ግማሽ ያህሉ የአፍ ወሲብ ፈጽመዋል። ኦራል ሴክስ ኢዝ ዘ ኒው ጉድናይት ኪስ የተባለው መጽሐፍ ደራሲ የሆኑት ሻርሊን አዛም እንዲህ ብለዋል፦ “በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ካሉ ወጣቶች ጋር [በአፍ ስለሚፈጸም ወሲብ] ብታወሩ ምንም ችግር እንደሌለው ይነግሯችኋል። እንዲያውም እንደ ፆታ ግንኙነት አይቆጥሩትም።”

 ምን ይመስልሃል?

 ለሚከተሉት ጥያቄዎች አዎ ወይም አይ የሚል መልስ ስጥ።

 1.   አንዲት ወጣት የአፍ ወሲብ ብትፈጽም በዚህ ምክንያት ልታረግዝ ትችላለች?

  1.  ሀ. አዎ

  2.  ለ. አይ

 2.   በአፍ ወሲብ መፈጸም የጤና ችግር ሊያስከትል ይችላል?

  1.  ሀ. አዎ

  2.  ለ. አይ

 3.   የአፍ ወሲብ የፆታ ግንኙነት ነው ሊባል ይችላል?

  1.  ሀ. አዎ

  2.  ለ. አይ

 እውነታው ምንድን ነው?

 የሰጠሃቸውን መልሶች ቀጥሎ ከቀረቡት መልሶች ጋር አወዳድር።

 1.   አንዲት ወጣት የአፍ ወሲብ ብትፈጽም በዚህ ምክንያት ልታረግዝ ትችላለች?

   መልስ፦ አይ። ብዙ ሰዎች በአፍ የሚፈጸም ወሲብ ጉዳት የለውም የሚል የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ እንዲደርሱ የሚደርጋቸው አንዱ ምክንያት ይህ ነው።

 2.   በአፍ ወሲብ መፈጸም የጤና ችግር ሊያስከትል ይችላል?

   መልስ፦ አዎ። የአፍ ወሲብ የሚፈጽም ሰው ሄፐታይተስ (ኤ ወይም ቢ)፣ የፆታ ብልቶች ላይ የሚወጣ ኪንታሮት፣ ጨብጥ፣ ኸርፐስ፣ ኤች አይ ቪና ቂጥኝ ሊይዘው ይችላል።

 3.   የአፍ ወሲብ የፆታ ግንኙነት ነው ሊባል ይችላል?

   መልስ፦ አዎ። የግብረ ሥጋ ግንኙነትን፣ የአፍ ወይም የፊንጢጣ ወሲብንና የሌላን ሰው የፆታ ብልት ማሻሸትን ጨምሮ የሌላን ሰው የፆታ ብልት በመጠቀም የሚፈጸም ድርጊት በሙሉ የፆታ ግንኙነት ነው።

 ሊያሳስበን የሚገባው ለምንድን ነው?

 እስቲ የአፍ ወሲብን በተመለከተ ሊኖረን የሚገባውን አመለካከት የሚጠቁሙ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች እንመልከት።

 መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “የአምላክ ፈቃድ እንድትቀደሱና ከፆታ ብልግና እንድትርቁ ነው።”—1 ተሰሎንቄ 4:3

 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘የፆታ ብልግና’ ተብሎ የተተረጎመው ቃል የግብረ ሥጋ ግንኙነትን፣ በአፍ ወይም በፊንጢጣ የሚፈጸም ወሲብንና የሌላን ሰው የፆታ ብልት ማሻሸትን ጨምሮ ከጋብቻ ውጪ የሚፈጸምን ማንኛውንም ወሲባዊ ድርጊት ያመለክታል። የፆታ ብልግና የሚፈጽም ሰው አስከፊ መዘዞችን ማጨዱ አይቀርም፤ ከሚያጋጥሙት አደጋዎች ሁሉ የከፋው ከአምላክ ጋር ያለውን ዝምድና ማጣት ነው።—1 ጴጥሮስ 3:12

 መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ዝሙት የሚፈጽም ሁሉ ግን በራሱ አካል ላይ ኃጢአት እየሠራ ነው።”—1 ቆሮንቶስ 6:18

 በአፍ የሚፈጸም ወሲብ አካላዊም ሆነ መንፈሳዊ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል። በተጨማሪም የስሜት ቀውስ ያስከትላል። ቶኪንግ ሴክስ ዊዝ ዩር ኪድስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “አንድ ሰው የሌሎች መጠቀሚያ እንደሆነ የሚሰማው እንዲሁም የጸጸት ወይም የስጋት ስሜት የሚያድርበት የተለመደውን ዓይነት የግብረ ሥጋ ግንኙነት ሲፈጽም ብቻ አይደለም። . . . አንድ ሰው አግባብ ባልሆነ ሁኔታ የግብረ ሥጋ ግንኙነት በመፈጸሙ ምክንያት የሚሰማው መጥፎ ስሜት በሙሉ በማንኛውም መንገድ የፆታ ብልግና የፈጸመ ሰው ሊሰማው ይችላል። ወሲብ፣ ለየት ባለ መንገድ ስለተፈጸመ ብቻ ወሲብ መሆኑ አይቀርም።”

 መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “የሚጠቅምህን ነገር የማስተምርህ፣ . . . እኔ ይሖዋ አምላክህ ነኝ።”—ኢሳይያስ 48:17

 አምላክ የፆታ ግንኙነትን አስመልክቶ የሰጠው ሕግ አንተን እንደሚጠቅምህ ይሰማሃል? ወይስ መፈናፈኛ እንዳሳጣህ ይሰማሃል? የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት በተጨናነቀ አውራ ጎዳና ላይ ስላሉ የተለያዩ የትራፊክ ምልክቶች አስብ። እነዚህን ምልክቶች የምትመለከታቸው ነፃነትህን እንደሚጋፉ ነገሮች አድርገህ ነው? ወይስ አደጋ እንዳይደርስብህ እንደሚረዱህ አድርገህ ትመለከታቸዋለህ? አንተም ሆንክ ሌሎች አሽከርካሪዎች እነዚህን ምልክቶች ችላ ብትሉ ምን ሊፈጠር ይችላል?

የትራፊክ ሕጎች ነፃነትህን ቢገድቡትም ከአደጋ ይጠብቁሃል። በተመሳሳይም የአምላክ ሕጎች ነፃነትህን ቢገድቡትም ጥበቃ ይሆኑልሃል

 ከአምላክ መመሪያዎች ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ችላ ካልካቸው የዘራኸውን ማጨድህ ሳይታለም የተፈታ ነው። (ገላትያ 6:7) ሴክስ ስማርት የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “የምታምንባቸውን ነገሮችና መርሆዎች ችላ ብለህ ትክክል እንዳልሆኑ የምታውቃቸውን ነገሮች የምትፈጽም ከሆነ ለራስህ ያለህ አክብሮት ይቀንሳል።” ከዚህ በተቃራኒ ከአምላክ መመሪያዎች ጋር በሚስማማ መንገድ የምትኖር ከሆነ በትክክለኛ ሥነ ምግባር የታነጽክ ሰው ትሆናለህ። ከዚህም በላይ ንጹሕ ሕሊና ይኖርሃል።—1 ጴጥሮስ 3:16