በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

በቤት ውስጥ ሕግ ያስፈልጋል?

በቤት ውስጥ ሕግ ያስፈልጋል?

 ወላጆችህ ያወጡት ሕግ የማያፈናፍን ሆኖብሃል? ይህ ርዕስና አብሮት ያለው የመልመጃ ሣጥን በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ወላጆችህን ለማነጋገር ይረዳሃል።

 ትክክለኛው አመለካከት

 የተሳሳተ አመለካከት፦ ልክ ከቤት ስትወጣ ከሕግ ትገላገላለህ።

 እውነታ፦ ከቤት መውጣት ከሕግ ነፃ አያደርግህም። ተጠያቂ የምትሆንበት አካል መኖሩ አይቀርም፤ ለምሳሌ አሠሪህ፣ አከራይህ አሊያም መንግሥት። የ19 ዓመቷ ዳንዬል እንዲህ ብላለች፦ “የወላጆቻቸውን ሕግ የማያከብሩ ወጣቶች ራሳቸውን ችለው መኖር ሲጀምሩ ያልጠበቁት ሁኔታ እንደሚያጋጥማቸው ይሰማኛል።”

 መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? ‘ለመንግሥታትና ለባለሥልጣናት ታዘዙ።’ (ቲቶ 3:1) ወላጆችህ ያወጧቸውን ሕጎች ለማክበር ጥረት የምታደርግ ከሆነ አዋቂ ስትሆን በተለያዩ የሕይወትህ ዘርፎች የሚያጋጥሙህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመወጣት የሚያስችል ጥሩ ሥልጠና ታገኛለህ።

 ምን ማድረግ ትችላለህ? ወላጆችህ ያወጧቸው ሕጎች የሚያስገኙልህን ጥቅሞች ለማሰብ ሞክር። ጄሬሚ የተባለ ወጣት እንዲህ ብሏል፦ “ወላጆቼ ያወጧቸው ሕጎች ጥሩ ጓደኞች እንድመርጥና ጊዜዬን በአግባቡ እንድጠቀም ረድተውኛል። እነዚህ ሕጎች ቴሌቪዥን በመመልከትና የቪዲዮ ጌሞችን በመጫወት ብዙ ሰዓት እንዳላጠፋ እንዲሁም አሁንም ድረስ የሚጠቅሙኝን ጥሩ ልማዶች እንዳዳብር ረድተውኛል።”

 ትክክለኛው መንገድ

 ወላጆችህ ያወጡት ሕግ ምክንያታዊ እንዳልሆነ ቢሰማህስ? ለምሳሌ ያህል፣ ታማራ የተባለች ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “ወላጆቼ ወደ ሌላ አገር እንድሄድ ፈቅደውልኝ ነበር፤ ከተመለስኩ በኋላ ግን 20 ደቂቃ ብቻ ርቆ ወደሚገኝ ከተማ እንኳ እየነዳሁ እንድሄድ አይፈቅዱልኝም!”

 የአንተም ሁኔታ ተመሳሳይ ከሆነ፣ ሕጉን አስመልክቶ ወላጆችህን ማነጋገርህ ስህተት ነው ማለት ነው? በፍጹም! ቁልፉ ነገር እነሱን መቼ እና እንዴት ማነጋገር እንዳለብህ ማወቅ ነው።

 መቼ። አማንዳ የተባለች በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኝ ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “አንድ ሕግ እንዲስተካከል ከወላጆችህ ጋር ከመነጋገርህ በፊት ኃላፊነት የሚሰማህ መሆንህን ማሳየት አለብህ።”

 ዳሪያ የተባለች ወጣትም በዚህ ትስማማለች። “እናቴ ለውጥ ለማድረግ የወሰነችው ላወጣቻቸው ሕጎች ታዛዥ እንደሆንኩ ካየች በኋላ ነው” ብላለች። ሌሎች በአንተ ላይ እምነት የሚጥሉት፣ አንተ ስለፈለግክ ሳይሆን እምነት የሚጣልብህ መሆንህን ስላስመሠከርክ እንደሆነ አስታውስ።

ወላጆች የሚያወጧቸው ሕጎች በማይከበሩበት ቤት ውስጥ መኖር የአየር ትራፊክ ሕጎች ተግባራዊ በማይሆኑበት የአየር ማረፊያ ውስጥ አውሮፕላን ለማሳረፍ እንደመሞከር ነው

 መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “የአባትህን ትእዛዝ ጠብቅ፤ የእናትህንም መመሪያ ቸል አትበል።” (ምሳሌ 6:20) ይህን ምክር ተግባራዊ ማድረግህ ወላጆችህ እምነት እንዲጥሉብህ ስለሚያደርግ ከእነሱ ጋር መወያየት ቀላል ይሆንልሃል።

 እንዴት። ስቲቨን የተባለ ወጣት እንዲህ ብሏል፦ “ከወላጆቻችን ጋር በምንነጋገርበት ጊዜ ከመነጫነጭና ከመጮህ ይልቅ አክብሮት ማሳየታችንና መረጋጋታችን የተሻለ ውጤት አለው።”

 ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ዳሪያም በዚህ ሐሳብ ትስማማለች። እንዲህ ብላለች፦ “ከእናቴ ጋር በመጨቃጨቅ መፍትሔ አግኝቼ አላውቅም። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ሕጉን የባሰ ጥብቅ ታደርገዋለች።”

 መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ሞኝ ስሜቱን ሁሉ እንዳሻው ይገልጻል፤ ጥበበኛ ግን ስሜቱን ይቆጣጠራል።” (ምሳሌ 29:11) ስሜትህን መቆጣጠር መማርህ በቤት ውስጥ ብቻ ሳይሆን በትምህርት ቤት፣ በሥራ እንዲሁም በሌሎች ቦታዎች ከፍተኛ ጥቅም ያስገኝልሃል።

 ምን ማድረግ ትችላለህ? ከመናገርህ በፊት አስብ። እምነት የሚጣልብህ በመሆን ረገድ ያተረፍከውን መልካም ስም፣ አንድ ጊዜ ብቻ በቁጣ በመገንፈል ልታጣው ትችላለህ። በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ “ቶሎ የማይቆጣ ሰው ትልቅ ማስተዋል አለው” ማለቱ ተገቢ ነው።—ምሳሌ 14:29

 ጠቃሚ ምክር፦ ወላጆችህ ያወጧቸውን ሕጎች ለማጤን፣ አስፈላጊ ከሆነ ደግሞ ከእነሱ ጋር ለመነጋገር የመልመጃ ሣጥኑን ተጠቀም።