መጽሐፍ ቅዱስ “በድካምና ነፋስን በመከተል ከሚገኝ ሁለት ዕፍኝ ይልቅ፣ በርጋታ [“በዕረፍት፣” የ1954 ትርጉም] የሚገኝ አንድ ዕፍኝ ይሻላል” ይላል። (መክብብ 4:6) በቂ እንቅልፍ ካላገኘህ ነገሮችን በቅልጥፍና ማከናወን አትችልም።

  • “በቂ እንቅልፍ ካላገኘሁ ምንም ነገር በትክክል መሥራት አልችልም። ሐሳቤን ማሰባሰብ እቸገራለሁ!”—ሬቸል፣ 19

  • “ከቀኑ 8 ሰዓት ገደማ ሲሆን በጣም ስለሚደክመኝ ከሰዎች ጋር እያወራሁ እንኳ እንቅልፍ ሊወስደኝ ይችላል!”—ክሪስቲን፣ 19

በቂ እንቅልፍ እንደማታገኝ ይሰማሃል? አንዳንድ እኩዮችህ ምን እንዳደረጉ እስቲ እንመልከት።

በጊዜ መተኛት፦ የ18 ዓመቷ ካትሪን “በጊዜ ለመተኛት ጥረት እያደረግሁ ነው” ብላለች።

በእንቅልፍ ሰዓት ወሬ ማቆም፦ የ21 ዓመቱ ሪቻርድ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “አንዳንድ ጊዜ ጓደኞቼ በጣም ከመሸ በኋላ ይደውሉልኛል ወይም በሞባይል መልእክት ይልኩልኛል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ወሬ ትቼ በጊዜ መተኛት ጀምሬያለሁ።

በተመሳሳይ ሰዓት መተኛት፦ የ20 ዓመቷ ጄኒፈር “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የምተኛበት እና የምነሳበት ሰዓት ቋሚ እንዲሆን ለማድረግ እየጣርኩ ነው” ብላለች።

ቁልፉ፦ በየቀኑ ቢያንስ ስምንት ሰዓት ለመተኛት ጥረት አድርግ።

በቂ እንቅልፍ ለማግኘት ቀላል የሆኑ ጥቂት እርምጃዎችን ብቻ መውሰድ ብዙ ጥቅሞች ያስገኝልሃል። ጥሩ ጤንነት የተሻለ ቁመና እንዲኖርህ፣ ጥሩ ስሜት እንዲሰማህና ቀልጣፋ እንድትሆን እንደሚረዳህ አትዘንጋ።

በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙህን አንዳንድ ነገሮች መለወጥ አትችልም፤ ጥሩ ጤንነት እንዲኖርህ ግን ማድረግ የምትችለው ነገር አለ። የ19 ዓመቷ ኤሪን እንደተናገረችው “ጤናማ መሆንህ ዞሮ ዞሮ የተመካው በአንተ ላይ ነው።