በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

ቁጣዬን መቆጣጠር የምችለው እንዴት ነው?

ቁጣዬን መቆጣጠር የምችለው እንዴት ነው?

 ጥያቄ

 •  የምትቆጣው በየስንት ጊዜው ነው?

  •  ጨርሶ አልቆጣም ማለት ይቻላል

  •  አንዳንድ ጊዜ

  •  በየቀኑ

 •  የቁጣህን መጠን እንዴት ትገልጸዋለህ?

  •  መጠነኛ

  •  ከፍተኛ

  •  በጣም ከፍተኛ

 •  አብዛኛውን ጊዜ የምትቆጣው በማን ላይ ነው?

  •  በወላጆችህ

  •  በወንድሞችህና በእህቶችህ

  •  በጓደኞችህ

 ቁጡ ሰው እንደሆንክ የሚሰማህ ከሆነ ይህ ርዕስ ይረዳሃል! በመጀመሪያ ግን፣ የሚያበሳጭ ነገር በሚያጋጥምህ ጊዜ ቁጣህን መቆጣጠርህ አስፈላጊ የሆነው ለምን እንደሆነ እንመልከት።

 ይህን ማወቅ ለምን አስፈለገ?

 ጤንነትህን ይነካል። ምሳሌ 14:30 “የሰከነ ልብ ለሰውነት ሕይወት ይሰጣል” ይላል። በሌላ በኩል ግን ‘ቁጣ ለልብ በሽታ ሊያጋልጥ እንደሚችል’ ጆርናል ኦቭ ሚዲስን ኤንድ ላይፍ ገልጿል።

 ከጓደኞችህ ጋር ያለህን ግንኙነት ይነካል። መጽሐፍ ቅዱስ “ከግልፍተኛ ሰው ጋር አትግጠም፤ በቀላሉ ቱግ ከሚል ሰውም ጋር አትቀራረብ” ይላል። (ምሳሌ 22:24) ስለዚህ ቁጡ ከሆንክ ሰዎች ቢርቁህ ሊገርምህ አይገባም። ጃዝሚን የተባለች አንዲት ወጣት “ቁጣህን የማትቆጣጠር ከሆነ ጥሩ ወዳጅነት የመመሥረት አጋጣሚ ሊያመልጥህ ይችላል።”

 በሌሎች ዘንድ የሚኖርህን ስም ይነካል። ኤታን የተባለ የ17 ዓመት ወጣት እንዲህ ብሏል፦ “በቁጣ ብትገነፍል ሌሎች ስለ ጉዳዩ መስማታቸው አይቀርም፤ ከዚያም ስለ አንተ የሚኖራቸው አመለካከት በዚህ ላይ የተመሠረተ ይሆናል።” እንዲህ በማለት ራስህን ጠይቅ፦ ‘ሰዎች እንዴት አድርገው እንዲያዩኝ ነው የምፈልገው? የተረጋጋና ሰላም ፈጣሪ ወይስ መቼ እንደሚፈነዳ የማይታወቅ እሳተ ገሞራ?’ መጽሐፍ ቅዱስ “ቶሎ የማይቆጣ ሰው ትልቅ ማስተዋል አለው፤ ትዕግሥት የሌለው ሰው ግን ሞኝነቱን ይገልጣል” ይላል።—ምሳሌ 14:29

ሁልጊዜ በቁጣ ከሚገነፍል ሰው ጋር መሆን የሚፈልግ ማንም የለም

 ምን ማድረግ ትችላለህ?

 ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ሰዎች የሰጧቸውን ሐሳቦች ካነበብክ በኋላ ከሥር የተቀመጡትን ጥያቄዎች ራስህን ጠይቅ።

 •   ምሳሌ 29:22 “በቀላሉ የሚቆጣ ሰው ጠብ ያስነሳል፤ ግልፍተኛ የሆነም ብዙ በደል ይፈጽማል።”

   “በአሥራዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ አካባቢ ሳለሁ ቁጣዬን መቆጣጠር በጣም እቸገር ነበር። የአባቴ ዘመዶችም ተመሳሳይ ችግር አለባቸው። እንዲያውም አንዳንዴ ‘ቁጣ በደማችን ውስጥ ነው ያለው’ ብለን እንቀልዳለን። ቶሎ መቆጣት ይቀናናል።”—ኬሪ

   በቀላሉ እቆጣለሁ? ጥሩ ባሕርዬ የራሴ ጥረት ውጤት እንደሆነ፣ መጥፎ ባሕርዬ ግን በዘር የወረስኩት እንደሆነ መናገር ምክንያታዊ ነው?

 •   ምሳሌ 15:1 “የለዘበ መልስ ቁጣን ያበርዳል፤ ክፉ ቃል ግን ቁጣን ያነሳሳል።”

   “ስሜታችንን እንዴት እንደምንቆጣጠር ማወቅ ይኖርብናል። ገርና አዎንታዊ ከሆን በቁጣ የመገንፈል ችግር አይኖርብንም።”—ዳረል

   የሚያበሳጭ ነገር ሲያጋጥመኝ የምሰጠው የመጀመሪያ ምላሽ በጣም ወሳኝ የሆነው ለምንድን ነው?

 •   ምሳሌ 26:20 “እንጨት ከሌለ እሳት ይጠፋል።”

   “አብዛኛውን ጊዜ፣ በደግነት ምላሽ ስሰጥ ሌላኛውም ሰው ይረጋጋል፤ ከዚያም ነገሮች ከቁጥጥር ውጭ ሳይሆኑ በሰላም መነጋገር እንችላለን።”—ጃዝሚን

   ንግግሬ ወይም ድርጊቴ በእሳት ላይ እንጨት እንደ መጨመር ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?

 •   ምሳሌ 22:3 “ብልህ ሰው አደጋ ሲያይ ይሸሸጋል፤ ተሞክሮ የሌለው ግን ዝም ብሎ ይሄዳል፤ መዘዙንም ይቀበላል።”

   “አንዳንድ ጊዜ ከአካባቢው መራቅና ጊዜ ወስጄ ስለ ሁኔታው ማሰብ ይኖርብኛል፤ ከዚያም ከተረጋጋሁ በኋላ እርምጃ መውሰድ እችላለሁ።”—ጌሪ

   አለመግባባት ሲፈጠር ግለሰቡን እንደናቅከው እንዲሰማው በማያደርግ መንገድ አካባቢውን ለቀህ መሄድ የምትችለው እንዴት ነው?

 •   ያዕቆብ 3:2 “ሁላችንም ብዙ ጊዜ እንሰናከላለን።”

   “ስህተት ስንሠራ መጸጸት እንዳለብን ግልጽ ነው፤ ሆኖም ከስህተታችን መማርም ይኖርብናል። ስንወድቅ ወዲያው መነሳትና ስህተታችንን ላለመድገም ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ አለብን።”—ኬሪ

 ጠቃሚ ምክር፦ ግብ አውጣ። ለተወሰነ ጊዜ ያህል (ለምሳሌ ለአንድ ወር) በቁጣ ሳትገነፍል ለመቆየት ግብ ልታወጣ ትችላለህ። ከዚያም የየዕለቱን ሁኔታ በጽሑፍ በማስፈር ምን ደረጃ ላይ እንደደረስክ ራስህን ገምግም።