በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

ስፖርት የመሥራት ፍላጎት እንዲኖረኝ ምን ላድርግ?

ስፖርት የመሥራት ፍላጎት እንዲኖረኝ ምን ላድርግ?

 ስፖርት መሥራት ያለብኝ ለምንድን ነው?

 በአንዳንድ አገሮች የሚኖሩ ወጣቶች ብዙ አይንቀሳቀሱም፤ ይህ ደግሞ ጤንነታቸውን አደጋ ላይ ጥሎታል። መጽሐፍ ቅዱስ “የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በጥቂቱ ይጠቅማል” የሚል ግሩም ምክር ይሰጣል። (1 ጢሞቴዎስ 4:8) የሚከተሉትን ነጥቦች ልብ በል፦

 •   ስፖርት ጥሩ ስሜት እንዲሰማህ ያደርጋል። አካላዊ እንቅስቃሴ ስናደርግ አንጎላችን ኢንዶርፊን የተባለ ኬሚካል ያመነጫል፤ ይህ ኬሚካል ዘና እንድንልና ጥሩ ስሜት እንዲሰማን ያደርጋል። በመሆኑም ስፖርት መሥራት ከድብርት ያላቅቃል።

   “በጠዋት ተነስቼ ዱብ ዱብ ካልኩ ቀኑን ሙሉ ደስ ብሎኝና ውጤታማ ሆኜ እውላለሁ። ስሮጥ ደስ ይለኛል።”—ሬጂና

 •   ስፖርት ቁመናህን ያሳምረዋል። በተገቢው መጠን ስፖርት መሥራትህ ጠንካራ እንድትሆን፣ ጥሩ ቁመና እንዲኖርህና በራስ የመተማመን ስሜትህ እንዲጨምር ያደርጋል።

   “አሥር ፑልአፕ መሥራት መቻሌ በጣም አስደስቶኛል፤ ከዓመት በፊት አንድ እንኳ መሥራት አልችልም ነበር! ከሁሉ በላይ ደግሞ ሰውነቴን እየተንከባከብኩ እንደሆነ ማወቄ ያስደስተኛል።”—ኦሊቪያ

 •   ስፖርት ዕድሜህን ያረዝመዋል። አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ የልብንና የሳንባን ጤንነት ለመጠበቅ ይረዳል። እንዲሁም ኤሮቢክስ መሥራት ኮሮናሪ አርተሪ ዲዚዝ የተባለውን የብዙ ሰዎችን ሕይወት የሚቀጥፍ የልብ በሽታ ይከላከላል።

   “አዘውትረን ስፖርት የምንሠራ ከሆነ ፈጣሪያችን ለሰጠን አካል አድናቆት እንዳለን እናሳያለን።”—ጄሲካ

 ዋናው ነጥብ፦ ስፖርት መሥራት ለወደፊት ሕይወታችን በጣም ይጠቅመናል፤ እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ ደስታ ያስገኝልናል። ቶንያ የተባለች ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “‘ምነው ባልሮጥኩ ኖሮ!’ የምትሉበት ጊዜ ሊኖር አይችልም። ሰበብ አስባብ መደርደሬን ትቼ ስፖርት ስሠራ በፍጹም አልቆጭም።”

መኪና ተገቢው እንክብካቤ ካልተደረገለት እንደሚበላሽ ሁሉ ስፖርት ካልሠራን ሰውነታችን ሊበላሽ ይችላል

 እንቅፋት የሆነብኝ ምንድን ነው?

 እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ብዙ ነገሮች አሉ፦

 •   ተነሳሽነት ማጣት። “ወጣቶች የሚታመሙ አይመስላቸውም። በሽታ ሊይዘኝ ይችላል ብላችሁ ስለማታስቡ ስለ ጤናቸው መጨነቅ ያለባቸው ትላልቅ ሰዎች ብቻ እንደሆኑ ይሰማችሁ ይሆናል።”—ሶፊያ

 •   ጊዜ ማጣት። “ፕሮግራሜ ቢጣበብም እንኳ ለመብላትና ለመተኛት ጊዜ እመድባለሁ፤ ለስፖርት ጊዜ ማግኘት ግን በጣም ይከብደኛል።”—ክላሪሳ

 •   የጂምናዚየም ክፍያ። “ጤንነትን መጠበቅ ውድ ሆኗል፤ ጂም መግባት ከፈለጋችሁ ገንዘብ ያስፈልጋችኋል።”—ጂና

 ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦

 ስፖርት እንዳትሠራ እንቅፋት የሆነብህ ነገር ምንድን ነው? እንቅፋቱን ማሸነፍ ጥረት ቢጠይቅም መልሶ ይክስሃል።

 ስፖርት ለመሥራት ምን ይረዳኛል?

 አንዳንድ ምክሮች ከዚህ በታች ቀርበዋል፦

 •   ጤንነትህን መንከባከብ የራስህ ኃላፊነት እንደሆነ አስታውስ።—ገላትያ 6:5

 •   ሰበብ አስባብ አታቅርብ። (መክብብ 11:4) ለምሳሌ ስፖርት ለመሥራት የግድ ጂም መግባት አያስፈልግህም። የምትወደውን ስፖርት ምረጥና አዘውትረህ ለመሥራት ሞክር።

 •   የምትሠራውን የስፖርት ዓይነት ለመምረጥ እንዲረዱህ ስፖርት የሚሠሩ ሰዎችን አማክር።—ምሳሌ 20:18

 •   ቋሚ ፕሮግራም ይኑርህ። ግብ አውጣ፤ እንዲሁም ተነሳሽነትህ እንዳይጠፋ የደረስክባቸውን ግቦች በጽሑፍ አስፍር።—ምሳሌ 21:5

 •   አብሮህ ስፖርት የሚሠራ ሰው ፈልግ። እንዲህ ያለ ጓደኛ ሊያበረታታህና ቋሚ ፕሮግራም እንዲኖርህ ሊረዳህ ይችላል።—መክብብ 4:9, 10

 •   ሁልጊዜ ላይሳካልህ እንደሚችል ጠብቅ፤ ግን ባይሳካልህም ተስፋ አትቁረጥ።—ምሳሌ 24:10

 ሚዛናዊ ሁን

 መጽሐፍ ቅዱስ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ‘በልማዶቻቸው ልከኛ መሆን’ እንዳለባቸው ይናገራል። (1 ጢሞቴዎስ 3:2, 11) ስለዚህ ከስፖርት ጋር በተያያዘ ሚዛናዊ ሁን። ለስፖርት ከመጠን ያለፈ ቦታ የሚሰጡ ሰዎች ብስለት የጎደላቸው ሆነው ሊታዩ ይችላሉ። “ጡንቻው ከአእምሮው የሚበልጥ ወንድ አይማርከኝም” በማለት ጁሊያ የተባለች ወጣት ተናግራለች።

 “ቢደክምህም አታቁም፤ መሥራትህን ቀጥል” እንደሚሉ ያሉ መፈክሮች ያላቸውን አደጋ አስተውል። እንዲህ ያለው ምክር ሰውነትህን የሚጎዳው ከመሆኑም ሌላ “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑት” ነገሮች ላይ እንዳታተኩር እንቅፋት ይሆንብሃል።—ፊልጵስዩስ 1:10

 በተጨማሪም፣ ስፖርት የሚሠሩ ሰዎችን ለማበረታታት የሚቀርቡ ማስታወቂያዎች ተስፋ ሊያስቆርጡህ ይችላሉ። ቬራ የተባለች ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “ብዙ ሴቶች ለስፖርት ተነሳሽነት በሚያጡበት ጊዜ ማበረታቻ እንዲሆናቸው ሲሉ የሚያምር ቁመና ያላቸውን ሰዎች ፎቶ ያስቀምጣሉ። ግን ራሳቸውን ከእነዚያ ሰዎች ጋር ማወዳደራቸው ተስፋ እንዲቆርጡ ያደርጋቸዋል። ስለዚህ ስለ ቁመናችን ከመጨነቅ ይልቅ ለጤናችን ብለን ስፖርት መሥራታችን የተሻለ ነው።”