ምን ማድረግ ትችላለህ?

አብረሃቸው የምትውላቸውን ሰዎች በጥንቃቄ ምረጥ። ጓደኞችህ እና አብረውህ የሚማሩት ልጆች የብልግና ወሬ ሲያወሩ በጨዋታው መሳተፍህ በአእምሮህ የሚመላለሱትን ሐሳቦች ለመቆጣጠር የምታደርገው ትግል ይበልጥ አስቸጋሪ እንዲሆንብህ ከማድረግ ውጪ የሚጠቅምህ ነገር የለም። እንደተመጻደቅህ በማያስመስል መንገድ ወይም ለፌዝ የሚጋብዝ ነገር ሳታደርግ ትተሃቸው መሄድ ትችላለህ።

ኮምፒውተርህ ውስጥ ቫይረስ ቢገባ ዝም ብለህ ትመለከታለህ? ታዲያ ብልግና ያለባቸው መዝናኛዎችስ አእምሮህን እንዲመርዙት ለምን ትፈቅዳለህ?

የፆታ ብልግና ከሚንጸባረቅባቸው መዝናኛዎች ራቅ። በዛሬው ጊዜ ያለው አብዛኛው መዝናኛ ተገቢ ያልሆነ የፆታ ስሜትን ለማነሳሳት ታልሞ የተዘጋጀ ነው። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ምክር ይሰጣል? “ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳችንን እናንጻ፤ እንዲሁም አምላካዊ ፍርሃት በማሳየት ቅድስናችንን ፍጹም እናድርግ” ይላል። (2 ቆሮንቶስ 7:1) የብልግና ሐሳቦች ወደ አእምሮህ እንዲመጡ ሊያደርግ የሚችል ማንኛውም ዓይነት መዝናኛ ባለበት ላለመድረስ ጥረት አድርግ።

ልታስታውሰው የሚገባ ነገር፦ የፆታ ፍላጎት በራሱ መጥፎ ነገር አይደለም። ደግሞም አምላክ ወንድና ሴትን የፈጠራቸው በመካከላቸው ጠንካራ መሳሳብ እንዲኖር አድርጎ ነው፤ በመሆኑም በትዳር ውስጥ እስከሆነ ድረስ የፆታ ስሜትን ማርካት ምንም ስህተት የለውም። እንግዲያው አንዳንድ ጊዜ የፆታ ስሜትህ ቢያይል መጥፎ ሰው እንደሆንክ ወይም የሥነ ምግባር ንጽሕናህን መጠበቅ እንደማትችል አድርገህ አታስብ።

ሊታሰብበት የሚገባው ነገር፦ በአእምሮህ የምታውጠነጥነውን ነገር መምረጥ ትችላለህ። አንተ እስከፈለግህ ድረስ በአስተሳሰብህም ሆነ በድርጊትህ የሥነ ምግባር ንጽሕናህን መጠበቅ ትችላለህ!