በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

ራሴን ችዬ ለመኖር ደርሻለሁ?

ራሴን ችዬ ለመኖር ደርሻለሁ?

 ራስን ችሎ የመኖር ሐሳብ አስደሳችም አስፈሪም ሊሆን ይችላል። ራስህን ችለህ ለመኖር ዝግጁ መሆንህን ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው?

 ምክንያትህ ምንድን ነው?

 ከቤት ለመውጣት እንድትወስን የሚያደርጉ የተለያዩ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፤ አንዳንዶቹ ግን አጥጋቢ ምክንያት አይደሉም። ለምሳሌ ማሪዮ የተባለ አንድ ወጣት “ከቤት መውጣት የፈለግኩት፣ ቤት ውስጥ ካሉብኝ ኃላፊነቶች ለመገላገል ስል ነበር” በማለት በሐቀኝነት ተናግሯል።

 እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ከቤት ከወጣህ በኋላ የሚኖርህ ነፃነት ከአሁኑ ያነሰ ሊሆን ይችላል። የ18 ዓመት ወጣት የሆነችው ኦንያ እንዲህ ብላለች፦ “ከቤት ከወጣህ የራስህን ቤት ማጽዳት፣ ምግብህን ራስህ ማብሰል እንዲሁም ወጪህን ራስህ መክፈል አለብህ፤ በዚያ ላይ ወላጆችህ አብረውህ ስላልሆኑ በፈለግከው ጊዜ ሊረዱህ አይችሉም!”

 ዋናው ነጥብ፦ ራስህን ችለህ ለመኖር ዝግጁ መሆን አለመሆንህን ለማወቅ በመጀመሪያ ከቤት መውጣት የፈለግክበትን ምክንያት በትክክል መረዳት ይኖርብሃል።

 ወጪህን አስላ

 ኢየሱስ “ከእናንተ መካከል፣ ግንብ ለመገንባት ፈልጎ ለመጨረስ የሚያስችል በቂ ገንዘብ እንዳለው ለማወቅ በመጀመሪያ ተቀምጦ ወጪውን የማያሰላ ማን ነው?” ብሏል። (ሉቃስ 14:28) ከቤት መውጣት የሚያስከትለውን ‘ወጪ ማስላት’ የምትችለው እንዴት ነው? በሚከተሉት ነገሮች ረገድ እንዴት እንደሆንክ ራስህን ገምግም።

የገንዘብ አያያዝህ እንዴት ነው?

 መጽሐፍ ቅዱስ “ገንዘብ ጥበቃ እንደሚያስገኝ” ይናገራል።—መክብብ 7:12

  •  ገንዘብ መቆጠብ ያስቸግርሃል?

  •  ብዙ ገንዘብ የማጥፋት ልማድ አለህ?

  •  በተደጋጋሚ ብድር ትጠይቃለህ?

 ከእነዚህ ጥያቄዎች መካከል ለአንዱም ቢሆን አዎ የሚል መልስ ከሰጠህ ራስህን ችለህ መኖር አስቸጋሪ ሊሆንብህ ትችላለህ።

 “ወንድሜ ከቤት የወጣው በ19 ዓመቱ ነበር። በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ያለውን ገንዘብ ሁሉ ጨረሰ፤ ዕዳውን መክፈል ስላቃተው መኪናውን ተወሰደበት እንዲሁም ባንኮች ብድር ከለከሉት፤ ከዚያም ወደ ቤት ለመመለስ ወላጆቼን ጠየቀ።”—ዳኒዬል

 አሁን ምን ማድረግ ትችላለህ? በየወሩ በአማካይ ምን ያህል ገንዘብ እንደሚያወጡ ወላጆችህን ጠይቃቸው። የትኞቹን ክፍያዎች መፈጸም ይጠበቅባቸዋል? እነዚህን ክፍያዎች ለመፈጸም የሚያስችል ምን ዓይነት በጀት አውጥተዋል? ገንዘብ የሚቆጥቡት እንዴት ነው?

 ዋናው ነጥብ፦ ቤት እያለህ የገንዘብ አያያዝ መማርህ ብቻህን ስትኖር የሚያጋጥምህን ከገንዘብ ጋር የተያያዘ ችግር ለመወጣት ያዘጋጅሃል።

ራስህን ትገዛለህ?

 መጽሐፍ ቅዱስ “እያንዳንዱ የራሱን የኃላፊነት ሸክም ይሸከማል” ይላል።—ገላትያ 6:5

  •  ዛሬ ነገ የማለት ልማድ አለህ?

  •  የቤት ውስጥ ሥራዎችን የምትሠራው ወላጆችህ ወትውተውህ ነው?

  •  ቤት እንድትገባ ከተወሰነልህ ሰዓት ዘግይተህ የመግባት ልማድ አለህ?

 ከእነዚህ ጥያቄዎች መካከል ለአንዱም ቢሆን አዎ የሚል መልስ ከሰጠህ ራስህን ችለህ ስትኖር ኃላፊነት የሚሰማህ ሰው ለመሆን ይበልጥ ትቸገራለህ።

 “ብቻህን ስትኖር ማድረግ የማትፈልጋቸውን አንዳንድ ነገሮችም የግድ ማድረግ ይጠበቅብሃል። ማንም ሰው እነዚህን ነገሮች እንድታደርግ አይነግርህም፤ በራስህ ተነሳስተህ ኃላፊነቶችህን መወጣትና የፕሮግራም ሰው መሆን አለብህ።”—ጄሲካ

 አሁን ምን ማድረግ ትችላለህ? ለአንድ ወር ያህል ቤት ውስጥ የምትችለውን ያህል ሥራ ለማከናወን ሞክር። ለምሳሌ ቤቱን ለብቻህ ለማጽዳት፣ የራስህን ልብስ ለማጠብ፣ የምግብ ሸቀጣ ሸቀጦችን ለመግዛት፣ በየቀኑ ምግብ ለማብሰልና ዕቃ ለማጠብ ጥረት አድርግ። ይህን ማድረግህ ለብቻ መኖር ምን ኃላፊነት እንደሚያስከትል ለመገንዘብ ይረዳሃል።

 ዋናው ነጥብ፦ ራስህን ችለህ ለመኖር ራስህን መግዛት ያስፈልግሃል።

ዝግጁ ሳይሆኑ ከቤት መውጣት የፓራሹትን አጠቃቀም ሳይማሩ ከአውሮፕላን ላይ ከመዝለል ጋር ይመሳሰላል

ስሜትህን መቆጣጠር ትችላለህ?

 መጽሐፍ ቅዱስ “ቁጣን፣ ንዴትን፣ ክፋትንና ስድብን ሁሉ ከእናንተ አስወግዱ” ይላል።—ቆላስይስ 3:8

  •  ከሌሎች ጋር ተስማምተህ መኖር ይከብድሃል?

  •  ቁጣህን መቆጣጠር ያስቸግርሃል?

  •  ሁልጊዜ ‘እኔ ያልኩት ብቻ ካልሆነ’ ትላለህ?

 ከእነዚህ ጥያቄዎች መካከል ለአንዱም ቢሆን አዎ የሚል መልስ ከሰጠህ ከሌላ ሰው ጋር ወይም ወደፊት ትዳር ስትመሠርት ደግሞ ከትዳር ጓደኛህ ጋር አብሮ መኖር አስቸጋሪ ይሆንብሃል።

 “ከጓደኞቼ ጋር መኖሬ ድክመቶቼን እንዳውቅ አድርጎኛል። ውጥረት ውስጥ ስሆን የሚፈጠርብኝን የስሜት መለዋወጥ ሌሎች ችለው እንዲያልፉ መጠበቅ እንደሌለብኝ ተምሬያለሁ። ውጥረቴን ለመቋቋም የሚያስችል ሌላ መንገድ መፈለግ ነበረብኝ።”—ሄለና

 አሁን ምን ማድረግ ትችላለህ? ከወላጆችህ እንዲሁም ከወንድሞችህና ከእህቶችህ ጋር ተስማምተህ ለመኖር ጥረት አድርግ። በአሁኑ ወቅት አብረውህ የሚኖሩ ሰዎችን ድክመት የምትመለከትበት መንገድ ወደፊት አብረውህ የሚኖሩ ሰዎችን ድክመት የምትመለከትበትን መንገድ ይጠቁማል።

 ዋናው ነጥብ፦ ራስን ችሎ መኖር አሁን ካሉብህ ኃላፊነቶችና ችግሮች ማምለጫ መንገድ አይደለም፤ ራስን ችሎ መኖር ብዙ ዝግጅት ይጠይቃል። ታዲያ በዚህ ረገድ የተሳካላቸውን ሰዎች ለምን አታማክርም? ወደ ኋላ መለስ ብለው ሲያስቡት በተለየ መንገድ ሊያከናውኑት የሚፈልጉት ወይም ‘ያኔ ባውቀው ኖሮ’ ብለው የሚመኙት ነገር ካለ ጠይቃቸው። የትኛውንም ከባድ ውሳኔ ከማድረግህ በፊት ሰዎችን ማማከርህ ጠቃሚ ነው።