በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

መልካም ምግባር ማሳየት አስፈላጊ ነው?

መልካም ምግባር ማሳየት አስፈላጊ ነው?

‘ሰዎች በር ከፍተው በማስገባት መልካም ምግባር አያሳዩኝም፤ ታዲያ እኔ እንዲህ ላደርግላቸው የሚገባው ለምንድን ነው?’

‘“እባክህ፣” “አመሰግናለሁ” ወይም “ይቅርታ” ማለቱ ብቻውን ምን ዋጋ አለው? ከዚህ የበለጡ አስፈላጊ ነገሮች አሉ።’

‘ለወንድሞቼና ለእህቶቼ መልካም ምግባር ማሳየት አይጠበቅብኝም። ምክንያቱም አንድ ቤተሰብ ነን።’

ከላይ ከተገለጹት አስተያየቶች መካከል የአንተን ስሜት የሚያንጸባርቅ ሐሳብ አለ? ካለ መልካም ምግባር ማሳየት ያሉት ጥቅሞች እየቀሩብህ ይሆናል!

 መልካም ምግባርን በተመለከተ ልታውቀው የሚገባ ነገር

 መልካም ምግባር ማሳየት በሚከተሉት ሦስት የሕይወትህ ዘርፎች ይጠቅምሃል፦

 1.   በሌሎች ዘንድ ያለህ ስም። ሰዎችን የምትይዝበት መንገድ ሌሎች ለአንተ ባላቸው አመለካከት ላይ በጥሩም ሆነ በመጥፎ ተጽዕኖ ያሳድራል። መልካም ምግባር የምታሳይ ከሆነ ሰዎች ብስለት ያለውና ኃላፊነት የሚሰማው ሰው እንደሆንክ አድርገው ይመለከቱሃል፤ እነሱም አንተን በተመሳሳይ መንገድ ለመያዝ ይነሳሳሉ። ሌሎችን ሥርዓት በጎደለው መንገድ የምትይዝ ከሆነ ግን ሰዎች ስለ ራስህ ብቻ የምታስብ ሰው አድርገው ይመለከቱሃል፤ ይህ ደግሞ ሥራ የመቀጠርና ሌሎች አጋጣሚዎች እንዲያመልጡህ ያደርጋል። መጽሐፍ ቅዱስ “ጨካኝ ሰው . . . በራሱ ላይ ውርደት ያመጣል” በማለት የሚናገረው ለዚህ ነው።—ምሳሌ 11:17 NW፤ የግርጌ ማስታወሻ

 2.   ማኅበራዊ ሕይወትህ። መጽሐፍ ቅዱስ “ፍቅርን ልበሱ፤ ምክንያቱም ፍቅር ፍጹም የሆነ የአንድነት ማሰሪያ ነው” በማለት ይናገራል። (ቆላስይስ 3:14) ከጓደኝነት ጋር በተያያዘ ይህ ሐሳብ እውነት ነው። ሰዎች መልካም ምግባር የሚያሳዩአቸውን ወይም ጥሩ አድርገው የሚይዟቸውን ሰዎች መቅረብ አይከብዳቸውም። ደግሞስ ሥርዓታማ ካልሆነና መልካም ምግባር ከሌለው ሰው ጋር ጓደኛ መሆን የሚፈልግ ሰው ይኖራል?

 3.   ሌሎች አንተን የሚይዙበት መንገድ። ጄኒፈር የተባለች አንዲት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “ሁልጊዜ ትሑት ለመሆን ጥረት የምታደርጉ ከሆነ ሥርዓታማ ያልሆኑ ሰዎችም እንኳ እናንተን የሚይዙበት መንገድ ሲሻሻል ማየት ትችላላችሁ።” መልካም ምግባር የማታሳዩ ከሆነ ደግሞ ከዚህ ተቃራኒ የሆነ ምላሽ ማግኘታችሁ አይቀርም። መጽሐፍ ቅዱስ “በምትሰፍሩበት መስፈሪያም ይሰፍሩላችኋል” ይላል።—ማቴዎስ 7:2

 ዋናው ነጥብ፦ በዕለት ተዕለት የሕይወት እንቅስቃሴያችን ከሰዎች ጋር መገናኘታችን አይቀርም። ሰዎችን የምትይዝበት መንገድ እነሱ ስለ አንተ ባላቸው አመለካከትም ሆነ አንተን በሚይዙበት መንገድ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። ስለዚህ በአጭሩ ለመናገር፣ መልካም ምግባር ማሳየትህ ትልቅ ለውጥ ያመጣል!

 ማሻሻል የምትችልበት መንገድ

 1.   ራስህን ገምግም። እንዲህ ያሉትን ጥያቄዎች ራስህን ጠይቅ፦ ‘ትላልቅ ሰዎችን የማነጋግረው በአክብሮት ነው? “እባክህ፣” “አመሰግናለሁ” ወይም “ይቅርታ” የሚሉትን ቃላት ምን ያህል ጊዜ እጠቀማለሁ? ከአንድ ሰው ጋር ሳወራ በትኩረት አዳምጣለሁ ወይስ ሌሎች ነገሮችን አደርጋለሁ? ምናልባት የተላከልኝን የጽሑፍ መልእክት አነብባለሁ ወይም ለዚያ መልስ እሰጣለሁ? ወላጆቼን እንዲሁም ወንድሞቼንና እህቶቼ በአክብሮት እይዛለሁ? ወይስ “ቤተሰብ ነን” በሚል እንደፈለግሁ ለመሆን ነፃነት ይሰማኛል?’

   መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “አንዳችሁ ሌላውን ለማክበር ቀዳሚ ሁኑ።”—ሮም 12:10

 2.   ግቦች አውጡ። ማሻሻያ ልታደርግባቸው የሚገቡ ሦስት አቅጣጫዎችን ጻፍ። ለምሳሌ ያህል፣ የ15 ዓመቷ አሊሰን “ጎበዝ ተናጋሪ ከመሆን ይልቅ ጥሩ አድማጭ መሆን” እንደሚያስፈልጋት ተናግራለች። የ19 ዓመቱ ዴቪድ ከቤተሰቡ ወይም ከጓደኞቹ ጋር በሚሆንበት ጊዜ የጽሑፍ መልእክት ላለመላላክ ጥረት ማድረግ እንዳለበት ገልጿል። እንዲህ ብሏል፦ “ይህን ማድረግ አክብሮት የጎደለው ድርጊት ነው። ‘ከእናንተ ጋር ከማውራት ይልቅ ከሌላ ሰው ጋር ባወራ እመርጣለሁ’ እንደ ማለት ነው።” የ17 ዓመቱ ኤድዋርድ ሌሎች ሲናገሩ ጣልቃ ከመግባት መቆጠብ እንዳለበት ተሰምቶታል። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ጄኒፈር ደግሞ በዕድሜ ለገፉ ሰዎች በምታሳየው ምግባር ረገድ ማስተካከያ ማድረግ እንዳለባት ተሰምቷት ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “አጭር ሰላምታ ከሰጠኋቸው በኋላ ሰበብ ፈልጌ ወጣት ወደሆኑት ጓደኞቼ እሄድ ነበር። አሁን ግን በዕድሜ የገፉ ሰዎች ጋር በደንብ ለመተዋወቅ ጥረት አደርጋለሁ። ይህም በማሳየው ምግባር ላይ ከፍተኛ ማስተካከያ እንዳደርግ ረድቶኛል።”

   መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ስለ ራሳችሁ ጉዳይ ብቻ ከማሰብ ይልቅ እያንዳንዳችሁ ለሌሎች ሰዎች ጉዳይም ትኩረት ስጡ።”—ፊልጵስዩስ 2:4

 3.   የምታደርገውን ማሻሻያ ተከታተል። ማሻሻያ ልታደርግበት ካሰብከው ነገር ጋር በተያያዘ ለአንድ ወር ያህል አነጋገርህንና ድርጊትህን ልብ ለማለት ሞክር። በወሩ መጨረሻ ላይ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘መልካም ምግባር ለማሳየት ጥረት ማድረጌ የተሻልኩ ሰው እንድሆን የረዳኝ እንዴት ነው? ማሻሻያ ላደርግባቸው የሚገቡ ሌሎች አቅጣጫዎች አሉ?’ ከዚህ ጋር በሚስማማ መልኩ አዳዲስ ግቦችን አውጣ።

   መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ልክ ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ እንደምትፈልጉት ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉላቸው።”—ሉቃስ 6:31