በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

ሌሎች ጓደኛቸው ሊያደርጉኝ ባይፈልጉ ምን ላድርግ?

ሌሎች ጓደኛቸው ሊያደርጉኝ ባይፈልጉ ምን ላድርግ?

 “ከሌሎች ጋር ተመሳስለህ መኖር አለብህ፤ አለዚያ ጓደኛ አይኖርህም፤ ሕይወትህ ይበላሻል፤ ተስፋ አይኖርህም። የሚያስታውስህ አይኖርም፤ ብቻህን ትቀራለህ።”—ካርል

 ካርል የተናገረው ሐሳብ የተጋነነ ነው? ሊሆን ይችላል። ያም ቢሆን አንዳንድ ሰዎች ካርል የተናገረው ችግር እንዳይደርስባቸው ሲሉ ማንኛውንም መሥዋዕት ለመክፈል ፈቃደኛ ናቸው። አንተስ? ይህ ርዕስ ለዚህ ችግር የተሻለ መፍትሔ ማግኘት የምትችልበትን መንገድ ይጠቁምሃል።

 ሰዎች በሌሎች ለመወደድ ጥረት የሚያደርጉት ለምንድን ነው?

 •   ሌሎች እንዲያገሏቸው ስለማይፈልጉ ነው። “ማኅበራዊ ድረ ገጽ ስጠቀም የተወሰኑ ሰዎች እኔ በሌለሁበት ተሰባስበው ሲዝናኑ የተነሷቸውን ፎቶዎች ተመለከትኩ። እኔን ያልጠሩኝ ለምን እንደሆነ ማሰብ ጀመርኩ፤ እንደማልመጥናቸው ስለተሰማኝ በጣም ተረበሽኩ።”—ናታሊ

   ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ሌሎች እንዳገለሉህ ተሰምቶህ ያውቃል? ታዲያ ጓደኛቸው አድርገው እንዲቀበሉህ ያደረግከው ነገር አለ?

 •   ከሌሎች የተለዩ ሆነው መታየት ስለማይፈልጉ ነው። “ወላጆቼ ስልክ እንድይዝ አይፈቅዱልኝም። አንዳንድ ልጆች ስልክ ቁጥሬን ጠይቀውኝ ስልክ እንደሌለኝ ስነግራቸው ‘እንዴ? እንዴት በዚህ ዕድሜሽ ስልክ አይኖርሽም?’ ይሉኛል። በ13 ዓመቴ ስልክ እንደሌለኝ ሲያውቁ እንደተበደልኩ ይሰማቸዋል።”—ሜሪ

   ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ከእኩዮችህ ወጣ ያልክ እንደሆንክ እንዲሰማህ ያደረገ ወላጆችህ የሰጡህ መመሪያ አለ? ታዲያ ይህን መመሪያ ታከብራለህ?

 •   ጉልበተኞች እንዳያጠቋቸው ሲሉ ነው። “ትምህርት ቤት ያሉት ልጆች ከእነሱ የተለየ ምግባር፣ አነጋገር ወይም ሃይማኖት ያለውን ልጅ አይወዱም። ከእነሱ ጋር ካልተመሳሰልክ አደጋ ውስጥ ነህ።”—ኦሊቪያ

   ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ከሌሎች ጋር ባለመመሳሰልህ የተነሳ ጥቃት ደርሶብህ ያውቃል? ታዲያ ሁኔታውን የያዝከው እንዴት ነው?

 •   ጓደኞቻቸውን ማጣት ስለማይፈልጉ ነው። “ጓደኞቼን ላለማጣት ስል እነሱን ለመምሰል እሞክር ነበር። አነጋገሬ እንደ እነሱ ነበር። የማያስቅ ነገር ቢሆን እንኳ ለእነሱ ብዬ እስቃለሁ። ሌላው ቀርቶ ልጆቹ ሌላን ሰው ሲያበሽቁ ከእነሱ ጋር እተባበር ነበር፤ ይህን የማደርገው ትክክል እንዳልሆነ እያወቅኩ ነበር።”—ሬቸል

   ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ በእኩዮችህ ዘንድ ተወዳጅነት ማግኘት ምን ያህል ያሳስብሃል? እነሱ እንዲወዱህ ለማድረግ ስትል ያልሆንከውን ለመሆን ሞክረህ ታውቃለህ?

 ልታውቀው የሚገባ ነገር

 •   በሌሎች ለመወደድ ብሎ እነሱን ለመምሰል መሞከር ተቃራኒ ውጤት ሊኖረው ይችላል። ለምን? ምክንያቱም ብዙውን ጊዜ ሰዎች፣ ለማስመሰል የሚደረግን ጥረት ማወቅ አይከብዳቸውም። የ20 ዓመቱ ብራያን እንዲህ ብሏል፦ “ያልሆንኩትን ለመሆን ስሞክር አብረውኝ ከሚማሩት ልጆች ጋር የባሰ እንደማልጣጣም አስተውያለሁ። ራስን መሆን ከሁሉ የተሻለ አማራጭ እንደሆነ ተምሬያለሁ፤ ምክንያቱም ስታስመስል ሰዎች ያውቁብሃል።”

   የተሻለ አማራጭ፦ በሕይወትህ ውስጥ ትልቅ ቦታ ስለምትሰጣቸው ነገሮች አስብ። መጽሐፍ ቅዱስ “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ [እወቁ]” ይላል። (ፊልጵስዩስ 1:10) በመሆኑም ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘ትልቅ ቦታ የምሰጠው ነገር ምንድን ነው? የእኔ ዓይነት አቋም በሌላቸው ሰዎች መወደድ ወይስ ራሴን መሆን?’

   “ሌሎችን ለመምሰል መሞከር ምንም ጥቅም የለውም። ሰዎች እንዲወዱህ አያደርግም፤ የተሻለ ሰው እንድትሆንም አይረዳህም።”—ጄምስ

 •   በሌሎች ለመወደድ መሞከር ማንነትህ እንዲጠፋ ሊያደርግ ይችላል። እንዲህ ለማድረግ የሚሞክር ሰው ለሌሎች ሲል የሚኖርና የራሱ ማንነት የሌለው ሰው ይሆናል። ጄረሚ የተባለ ወጣት እንዲህ ብሏል፦ “በሌሎች ለመወደድ ስል እነሱን ለመምሰል የማላደርገው ነገር አልነበረም፤ እነሱ እስከወደዱኝ ድረስ ስሜን የሚያበላሽ ነገር ለማድረግ እንኳ ፈቃደኛ ነበርኩ። የሚቆጣጠሩኝ እነሱ ነበሩ። የእነሱ አሻንጉሊት ሆኜ ነበር።”

   የተሻለ አማራጭ፦ ሕይወትህን የምትመራባቸው መሥፈርቶች ይኑሩህ፤ እንደ አካባቢዋ ቀለሟን እንደምትቀያይረው እስስት ከመሆን ይልቅ በእነዚህ መሥፈርቶች ተመራ። መጽሐፍ ቅዱስ “ብዙዎች ስላደረጉት ብቻ አንድን ነገር አታድርግ” በማለት ጥሩ ምክር ይሰጣል።—ዘፀአት 23:2 ሆሊ ባይብል—ኢዚ ቱ ሪድ ቨርዥን

   “እነሱ የሚወዷቸውን ነገሮች ሁሉ ለመውደድ እጥር ነበር፤ ከሙዚቃ፣ ከጌም፣ ከልብስ፣ ከቴሌቪዥን ፕሮግራም፣ ከመኳኳያና ከሌሎች ነገሮች ጋር በተያያዘ የእነሱን ምርጫ እከተል ነበር። እነሱም ቢሆን እያስመሰልኩ እንደሆነ ገብቷቸው ነበር። ለነገሩ ይህን የማያውቅ ሰው ያለ አይመስለኝም። የተረፈኝ ነገር ቢኖር ሐዘንና ብቸኝነት ነው፤ ማን እንደሆንኩ ራሱ ጠፋኝ። ሰው ሁሉ ጓደኛዬ እንዲሆን ወይም እንዲወደኝ መጠበቅ እንደሌለብኝ ተምሬያለሁ። ይህ ሲባል ጓደኛ ለማግኘት የምናደርገውን ጥረት እናቆማለን ማለት አይደለም፤ ሆኖም ማንነታችንን በደንብ እስክናውቅ ድረስ ለራሳችን ጊዜ መስጠታችን ጥሩ ነው።”—ሜሊንዳ

 •   በሌሎች ለመወደድ መሞከር መልካም ምግባርህን ሊያበላሸው ይችላል። ክሪስ የተባለ ወጣት፣ አንድ ዘመዱ ያጋጠመው ነገር የዚህን ሐሳብ እውነተኝነት እንደሚያሳይ ይሰማዋል። ክሪስ ዘመዱን አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ “በሌሎች ለመወደድ ሲል ብቻ ቀደም ሲል የማያደርጋቸውን ነገሮች ማድረግ ጀመረ፤ ለምሳሌ ዕፅ መውሰድ ጀመረ። በኋላም የዕፅ ሱሰኛ ሆነ፤ በዚህ የተነሳም በአንድ ወቅት ሊሞት ነበር።”

   የተሻለ አማራጭ፦ አነጋገራቸውና ምግባራቸው መጥፎ የሥነ ምግባር መሥፈርት እንደሚከተሉ ከሚያሳይ ሰዎች ራቅ። መጽሐፍ ቅዱስ “ከጥበበኞች ጋር የሚሄድ ጥበበኛ ይሆናል፤ ከሞኞች ጋር የሚገጥም ግን ጉዳት ይደርስበታል” ይላል።—ምሳሌ 13:20

   “በሌሎች ለመወደድ ጥረት ማድረግ አንዳንድ ጊዜ ስህተት ላይኖረው ይችላል። ሆኖም ለዚህ ብለህ፣ ትክክል እንደሆነ የምታውቀውን ነገር መጣስ የለብህም። እውነተኛ ጓደኞች ማንነትህን እንድትቀይር አይጠብቁብህም።”—ሜላኒ

   ጠቃሚ ምክር፦ ጓደኛ ለማግኘት ጥረት ስታደርግ የአንተ ዓይነት ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ብቻ አትፈልግ። ከዚህ ይልቅ አንተ የምትመራባቸውን መንፈሳዊና ሥነ ምግባራዊ መሥፈርቶች የሚከተሉ ሰዎችን ምረጥ።

  አንዳንድ ልብሶች ውበትህ እንዳይወጣ ያደርጋሉ። በተመሳሳይም አንዳንድ ሰዎች ያለህ ጥሩ አቋም እንዲደበቅ ያደርጋሉ