በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

ለማግባት ዝግጁ ነኝ?

ለማግባት ዝግጁ ነኝ?

 ይህንን ጥያቄ ለመመለስ እንድትችል ስለ ራስህ ማወቅ ያለብህ አንዳንድ ነገሮች አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ የሚከተሉትን ነጥቦች ተመልከት፦

ከሌሎች ጋር ያለህ ግንኙነት

ከወላጆችህ ብሎም ከወንድሞችህና ከእህቶችህ ጋር ያለህ ግንኙነት ምን ይመስላል? ብዙ ጊዜ ከእነሱ ጋር ስትነጋገር ራስህን መቆጣጠር ያቅትሃል? ምናልባትም ስሜትህን ለመግለጽ የሚጎዳ ወይም የሽሙጥ አነጋገር ትጠቀማለህ? በዚህ ረገድ እነሱ ስለ አንተ ቢጠየቁ ምን ይላሉ? የቤተሰብህን አባላት የምትይዝበት መንገድ የትዳር ጓደኛ ብትኖርህ እንዴት እንደምትይዛት ይጠቁማል።—ኤፌሶን 4:31

አመለካከትህ

ለነገሮች ያለህ አመለካከት አዎንታዊ ነው ወይስ አሉታዊ? ምክንያታዊ ነህ ወይስ ሁልጊዜ እኔ ያልኩት ካልሆነ ትላለህ? ውጥረት የሚፈጥር ሁኔታ ሲያጋጥምህ ነገሮችን በረጋ መንፈስ ማከናወን ትችላለህ? ትዕግሥተኛ ነህ? የአምላክን መንፈስ ፍሬ ከአሁኑ ለማፍራት ጥረት ማድረግህ ስታገባ ጥሩ የትዳር ጓደኛ ለመሆን ይረዳሃል።—ገላትያ 5:22, 23

የገንዘብ አያያዝ

በገንዘብ አያያዝ ረገድ እንዴት ነህ? ብዙ ጊዜ ትበደራለህ? በአንድ ሥራ ላይ መቆየት ትችላለህ? ካልሆነ ምክንያቱ ምንድን ነው? የሥራው ጸባይ ነው ወይስ የአሠሪህ ባሕርይ? ወይስ ማስተካከል የሚያስፈልጉህ አንዳንድ መጥፎ ባሕርያት ወይም ልማዶች አሉህ? ብቻህን እያለህ ገንዘብ አያያዝ ካልተማርክ እንዴት አድርገህ ቤተሰብ ማስተዳደር ትችላለህ?—1 ጢሞቴዎስ 5:8

መንፈሳዊነት

የይሖዋ ምሥክር ከሆንክ ጥሩ መንፈሳዊ አቋም እንዲኖርህ ጥረት ታደርጋለህ? ማንም ሳይጎተጉትህ የአምላክን ቃል ለማንበብ፣ በአገልግሎት ለመካፈልና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ለመሳተፍ ጥረት ታደርጋለህ? የምታገባት ሴት ጠንካራ መንፈሳዊ አቋም ያለው ባል ያስፈልጋታል ቢባል አትስማማም?—መክብብ 4:9, 10

 ራስህን ይበልጥ እያወቅህ በሄድህ መጠን፣ ከድክመትህ ይልቅ በጠንካራ ጎንህ ላይ በማተኮር የተሻልህ ሰው እንድትሆን የምትረዳህን ሴት ለማግኘት የሚያስችል ብቃት እያዳበርህ ትሄዳለህ።