በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የአንድን የእስራኤል ነገድ መኖሪያ ያረጋገጡ ጥንታዊ መዛግብት

የአንድን የእስራኤል ነገድ መኖሪያ ያረጋገጡ ጥንታዊ መዛግብት

እስራኤላውያን ተስፋይቱን ምድር ድል አድርገው ምድሪቱን በየነገዶቻቸው ሲከፋፈሉ አሥሩ የምናሴ ነገድ ጎሣዎች ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ ከሌሎቹ ጎሣዎች የተለየ መሬት እንደተሰጣቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ኢያሱ 17:1-6) ይህ ታሪክ ትክክል መሆኑን የሚያረጋግጥ የአርኪኦሎጂ ማስረጃ አለ?

የዕብራይስጥ ጽሑፍ የተቀረጸባቸው የሸክላ ስብርባሪዎች ሰማርያ ውስጥ በ1910 በቁፋሮ ተገኝተዋል። በእነዚህ ስብርባሪዎች ላይ የተገኘው ጽሑፍ ወይን ጠጅንና ለመዋቢያነት የሚውል ዘይትን ጨምሮ የተለያዩ የቅንጦት ዕቃዎች በዋና ከተማዋ ውስጥ ወዳለው ቤተ መንግሥት ይመጡ እንደነበረ ይጠቁማል። እነዚህ ሸክላዎች በስምንተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. የተሠሩ እንደሆኑ ይታመናል። የተገኙት ስብርባሪዎች በድምሩ 102 ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል በግልጽ የሚነበብ ጽሑፍ ያላቸው 63ቱ ብቻ ናቸው። ይሁንና በ63ቱ ስብርባሪዎች ላይ የሚገኘው መረጃ በጥቅሉ ሲታይ ቀኖችን፣ የጎሣዎችን ስም እንዲሁም ሸቀጦቹን የላኩትንና የተቀበሉትን ሰዎች ማንነት ይገልጻል።

የሚገርመው በሰማርያ በተገኙት ስብርባሪዎች ላይ የተጠቀሱት ጎሣዎች በሙሉ ከምናሴ ነገድ ናቸው። ኤንአይቪ አርኪኦሎጂካል ስተዲ ባይብል እንደገለጸው እነዚህ ስብርባሪዎች የምናሴ ነገድ ጎሣዎች የሰፈሩበትን ቦታ በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ የያዘው ሐሳብ ትክክል መሆኑን የሚያረጋግጥ መረጃ ይሰጡናል።

ይህ የተቀረጸ ጽሑፍ ከምናሴ ነገድ የሆነችን ኖኅ የተባለች ሴት ይጠቅሳል

በተጨማሪም በሰማርያ የተገኙት ስብርባሪዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው አሞጽ በዚያ ዘመን የነበሩትን ባለጸጋ ሰዎች በተመለከተ “በትላልቅ ጽዋዎች የወይን ጠጅ ሞልተው ይጠጣሉ፤ ምርጥ የሆኑ ዘይቶችም ይቀባሉ” በማለት የተናገረውን ሐሳብ ትክክለኛነት ያረጋግጣሉ። (አሞጽ 6:1, 6) በሰማርያ የተገኙት ስብርባሪዎች እነዚህ የቅንጦት ሸቀጦች የምናሴ ነገድ አሥሩ ጎሣዎች ወደሚገኙበት ቦታ ይላኩ እንደነበር በግልጽ ያሳያሉ።