በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ለቤተሰብ | ትዳር

ቴክኖሎጂ ሕይወታችንን እንዳይቆጣጠረው ማድረግ

ቴክኖሎጂ ሕይወታችንን እንዳይቆጣጠረው ማድረግ

 የቴክኖሎጂ ውጤቶችን የምትጠቀሙበት መንገድ በትዳራችሁ ላይ አዎንታዊ ወይም አሉታዊ ውጤት ሊኖረው ይችላል። ቴክኖሎጂ በትዳራችሁ ላይ ምን ዓይነት ተጽዕኖ እያደረገ ነው?

 ማወቅ የሚኖርባችሁ ነገር

  •   የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በጥበብ መጠቀም ለትዳራችሁ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ አንዳንድ ባለትዳሮች አብረው በማይሆኑበት ሰዓት ለመነጋገር የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ይጠቀማሉ።

     “‘እወድሻለሁ’ ወይም ‘ናፍቀሽኛል’ የሚል አጭር መልእክት መላክ ብቻ ይበልጥ ለመቀራረብ ይረዳል።”—ጆናታን

  •   የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በጥበብ አለመጠቀም ትዳራችሁን ይጎዳዋል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ሰዎች ስልካቸውን ወይም ታብሌታቸውን ያለማቋረጥ ስለሚጠቀሙ ለትዳር ጓደኛቸው በቂ ጊዜና ትኩረት አይሰጡም።

     “ባለቤቴ ሊያነጋግረኝ ፈልጎ ስልኬን እየተጠቀምኩ በመሆኑ ምክንያት ሳያነጋግረኝ የቀረበት ጊዜ እንደሚኖር ምንም ጥርጥር የለውም።”—ጁሊሳ

  •   አንዳንድ ሰዎች ስልካቸውን እየተጠቀሙም ከትዳር ጓደኛቸው ጋር ትርጉም ያለው የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ እንደሚችሉ ይናገራሉ። የሥነ ልቦና ባለሙያ የሆኑት ሼሪ ተርክል ‘በአንድ ጊዜ ብዙ ነገር ማከናወን እችላለሁ ብሎ ማሰብ ሞኝነት’ እንደሆነ ገልጸዋል። ደግሞም በአንድ ጊዜ ብዙ ነገር ማከናወን ጠቃሚ ክህሎት አይደለም። አክለውም “ብዙ ነገር ለማከናወን በሞከርን መጠን ለእያንዳንዱ ነገር የምንሰጠው ትኩረት እየቀነሰ ይመጣል” ብለዋል። a

     “ከባለቤቴ ጋር መነጋገር ያስደስተኛል፤ ሌላ ነገር እያከናወነ ከሆነ ግን መነጋገር አልፈልግም። ስልኩን እየተጠቀመ ሲያነጋግረኝ፣ እኔን ከማነጋገር ይልቅ ስልኩን መጠቀም እንደሚያስደስተው ይሰማኛል።”—ሳራ

 ዋናው ነጥብ፦ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን የምትጠቀሙበት መንገድ በትዳራችሁ ላይ አዎንታዊ አሊያም አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል።

 ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

 ቅድሚያ የምትሰጡትን ነገር ወስኑ። መጽሐፍ ቅዱስ “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ [እወቁ]” ይላል። (ፊልጵስዩስ 1:10) ራሳችሁን እንዲህ ብላችሁ ጠይቁ፦ ‘እኔና ባለቤቴ ለቴክኖሎጂ ውጤቶች የምንሰጠው ጊዜና ትኩረት፣ አንዳችን ለሌላው ልንሰጠው የሚገባውን ጊዜና ትኩረት ይሻማብናል?’

 “አንድ ወንድና አንዲት ሴት ምግብ ቤት ተቀምጠው ስልካቸው ላይ ብቻ ሲያተኩሩ ማየት በጣም ያሳዝናል። የቴክኖሎጂ ውጤቶች ባሪያ ሆነን ይበልጥ አስፈላጊ የሆነውን ነገር ማለትም እርስ በርስ ያለንን ወዳጅነት መዘንጋት የለብንም።”—ማቲው

 ገደብ አብጁ። መጽሐፍ ቅዱስ “የምትመላለሱት ጥበብ እንደጎደላቸው ሳይሆን እንደ ጥበበኛ ሰዎች መሆኑን ምንጊዜም በጥንቃቄ አስተውሉ፤ . . . ጊዜያችሁን በተሻለ መንገድ ተጠቀሙበት” የሚል ምክር ይሰጣል። (ኤፌሶን 5:15, 16) ራሳችሁን እንዲህ ብላችሁ ጠይቁ፦ ‘የመጡልኝን መልእክቶች ሁሉ ወዲያውኑ ከመመለስ ይልቅ አጣዳፊ ያልሆኑ መልእክቶችን ሌላ ጊዜ አንብቤ መመለስ እችል ይሆን?’

 “ስልኬን ሳይለንት ማድረጉንና የመጡልኝን መልእክቶች አመቺ ጊዜ ሳገኝ መመለሱን ጠቃሚ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። አብዛኛው የስልክ ጥሪ፣ የጽሑፍ መልእክት ወይም ኢ-ሜይል አፋጣኝ ምላሽ የሚፈልግ አንገብጋቢ ጉዳይ አይደለም።”—ጆናታን

 የሚቻል ከሆነ ሥራችሁን ሥራ ቦታ ተዉት። መጽሐፍ ቅዱስ “ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው” ይላል። (መክብብ 3:1) ራሳችሁን እንዲህ ብላችሁ ጠይቁ፦ ‘ሥራዬ በስልኬ አማካኝነት ቤት ድረስ ተከትሎኝ ይመጣል? ከሆነ ይህ ሁኔታ በትዳሬ ላይ ምን ዓይነት ተጽዕኖ አሳድሯል? የትዳር ጓደኛዬ በዚህ ረገድ ምን ትላለች?’

 “ቴክኖሎጂ በማንኛውም ጊዜና በየትኛውም ቦታ ሥራችንን እንድንሠራ አስችሎናል። በመሆኑም ከባለቤቴ ጋር ስሆን በተደጋጋሚ ስልኬን እየተመለከትኩ ከሥራ ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ትኩረት ላለመስጠት ልዩ ጥረት ማድረግ አስፈልጎኛል።”—ማቲው

 የቴክኖሎጂ አጠቃቀማችሁን በተመለከተ ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ተነጋገሩ። መጽሐፍ ቅዱስ “እያንዳንዱ ሰው ምንጊዜም የራሱን ጥቅም ሳይሆን የሌላውን ሰው ጥቅም ይፈልግ” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 10:24) የቴክኖሎጂ አጠቃቀማችሁን ገምግሙ፤ ከዚያም ምን ማስተካከያዎች ማድረግ እንዳለባችሁ ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ተነጋገሩ። በዚህ ርዕስ ውስጥ ያለውን መወያያ ሐሳብ እንደ መነሻ ልትጠቀሙበት ትችላላችሁ።

 “ባለቤቴ ስልኩን ወይም ታብሌቱን ረዘም ላለ ጊዜ እየተጠቀመ እንዳለ ከተሰማኝ በሐቀኝነት እነግረዋለሁ፤ እሱም ይነግረኛል። የቴክኖሎጂ አጠቃቀማችን ችግር ሊፈጥር እንደሚችል ሁለታችንም ስለምናውቅ የትዳር ጓደኛችንን ስሜት ምንጊዜም ግምት ውስጥ እናስገባለን።”—ዳንዬል

 ዋናው ነጥብ፦ ቴክኖሎጂ አገልጋያችሁ እንጂ ጌታችሁ እንዳይሆን ተጠንቀቁ።

a ሪክሌሚንግ ኮንቨርሴሽን—ዘ ፓወር ኦቭ ቶክ ኢን ኤ ዲጂታል ኤጅ ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ።