በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ለቤተሰብ | የወላጅ ሚና

ወላጆች ስለ ሕፃናት ማቆያ ማዕከላት ምን ማወቅ ይኖርባቸዋል?

ወላጆች ስለ ሕፃናት ማቆያ ማዕከላት ምን ማወቅ ይኖርባቸዋል?

 ሥራ ቦታ የሚውሉ አንዳንድ ወላጆች ትምህርት ቤት ለመግባት ዕድሜያቸው ያልደረሰ ልጆቻቸውን ወደ ሕፃናት ማቆያ ማዕከል ይልካሉ፤ እነዚህ ማዕከላት ከትምህርት ቤት ጋር ተመሳሳይ አሠራር ይከተላሉ። እናንተስ እንዲህ ያለውን ውሳኔ ማድረጋችሁ ለልጃችሁ ይጠቅመው ይሆን?

 ልታስቡባቸው የሚገቡ ጥያቄዎች

 ልጃችሁን ወደ ሕፃናት ማቆያ መላካችሁ በመካከላችሁ ያለውን ዝምድና ይነካዋል? ሊነካው ይችላል። ልጃችሁ ከተወለደ በኋላ ባሉት የመጀመሪያዎቹ ዓመታት አእምሮው በፍጥነት የሚያድግ ሲሆን ይህም ከሌሎች ጋር ባለው ግንኙነት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። የልጃችሁ ማንነት በሚቀረጽባቸው በእነዚህ ጊዜያት አቅማችሁ በፈቀደው መጠን ከልጃችሁ ጋር ለመሆን ጥረት አድርጉ።—ዘዳግም 6:6, 7

 •    ልጃቸውን ወደ ሕፃናት ማቆያ ለመላክ የሚያስቡ ወላጆች ከልጃቸው ጋር ያላቸውን የጠበቀ ዝምድና ይዘው መቀጠል የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ማሰብ ይኖርባቸዋል።

 ልጃችሁን ወደ ሕፃናት ማቆያ መላካችሁ በልጃችሁ ላይ የምታሳድሩትን ተጽዕኖ ያዳክመዋል? ሊያዳክመው ይችላል። ሆልድ ኦን ቱ ዮር ኪድስ የተባለው መጽሐፍ “ትምህርት ቤት ለመግባት ዕድሜያቸው ያልደረሰ ልጆች አብረው የሚያሳልፉት ጊዜ በጨመረ መጠን እኩዮቻቸው የሚያሳድሩባቸው ተጽዕኖም የዚያኑ ያህል ይጨምራል” ይላል።

 •    ልጃቸውን ወደ ሕፃናት ማቆያ ለመላክ የሚያስቡ ወላጆች ‘በልጃችን ሕይወት ውስጥ የምናሳድረው ተጽዕኖ እየተዳከመ ይሄድ ይሆን?’ ብለው ራሳቸውን ሊጠይቁ ይገባል።

 ልጃችሁን ወደ ሕፃናት ማቆያ መላካችሁ ትምህርት ቤት ሲገባ ጎበዝ ተማሪ እንዲሆን ይረዳዋል? አንዳንዶች ‘አዎ’ ብለው ይመልሳሉ። ሌሎች ደግሞ ልጆችን ወደ ሕፃናት ማቆያ መላክ ትምህርት በመቀበል ችሎታቸው ላይ ያን ያህል ለውጥ እንደማያመጣ ይናገራሉ። ያም ሆነ ይህ፣ ወላጆች የሕፃናት ሥነ ልቦና ባለሙያ የሆኑት ፔነሎፒ ሊች የጻፉትን የሚከተለውን ሐሳብ ልብ ማለታቸው ጠቃሚ ነው፦ “ስኬታማ ለመሆን ቁልፉ ‘ትምህርት’ እንደሆነና ልጃችሁ በተቻለ መጠን ቀደም ብሎ ወደ ትምህርት ተቋም መግባቱ ጥሩ እንደሆነ አድርጋችሁ አታስቡ። እንዲህ ብሎ ማሰብ፣ ልጃችሁ ከተወለደ ጀምሮ ስትሰጡት የነበረው ‘ትምህርት’ ያን ያህል ጠቃሚ እንዳልሆነ አድርጎ መቁጠር ይሆንባችኋል።”

 •   ልጃቸውን ወደ ሕፃናት ማቆያ ለመላክ የሚያስቡ ወላጆች እንዲህ ማድረጋቸው የሚያስገኘው ጥቅም ስለመኖሩ ሊያስቡበት ይገባል።

 ከሁለት አንዳችሁ ሥራችሁን አቁማችሁ ቤት መዋል ትችሉ ይሆን? አንዳንድ ጊዜ ሁለቱም ወላጆች የሚሠሩት መሠረታዊ ነገሮችን ለማሟላት ሳይሆን የተደላደለ ኑሮ ለመምራት ነው። ሆኖም እንዲህ ማድረጋቸው የሚያስገኘው ጥቅም ከሚከፈለው መሥዋዕት ይበልጣል?

 •   ልጃቸውን ወደ ሕፃናት ማቆያ ለመላክ የሚያስቡ ወላጆች ወጪያቸውን በመቀነስ ከሁለት አንዳቸው ቤት መዋል ይችሉ እንደሆነ ሊያስቡበት ይገባል።

 ልጃችሁን ወደ ሕፃናት ማቆያ ማዕከል ለመላክ መወሰን ያለባችሁ እንዲህ ማድረጋችሁ ያለውን አዎንታዊና አሉታዊ ጎን በጥንቃቄ ካሰባችሁበት በኋላ ነው። ጉዳዩን ካመዛዘናችሁ በኋላ ልጃችሁን ወደ ሕፃናት ማቆያ መላካችሁ ለቤተሰባችሁ የተሻለ አማራጭ እንደሆነ ከተሰማችሁስ?

 ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

 መጽሐፍ ቅዱስ “ብልህ . . . አካሄዱን አንድ በአንድ ያጤናል” ይላል። (ምሳሌ 14:15) ይህን ምክር በአእምሯችሁ በመያዝ ልጃችሁን የምታስገቡበትን የሕፃናት ማቆያ በጥንቃቄ ምረጡ።

 ምን አማራጮች እንዳሏችሁ ለማወቅ ሞክሩ

 •   አንዳንድ ወላጆች በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ የተወሰኑ ሕፃናትን ወደሚንከባከቡ ሞግዚቶች ልጆቻቸውን ለመላክ ይመርጣሉ፤ በእነዚህ መዋያዎች ውስጥ አንድ ወይም ሁለት ሞግዚቶች ሊኖሩ ይችላሉ።

 •   ሌሎች ወላጆች ደግሞ ዘመድ፣ አብሯቸው የሚኖር የቤት ሠራተኛ ወይም ሞግዚት ልጃቸውን እንዲንከባከብላቸው ያደርጋሉ።

 ሁሉም አማራጮች አዎንታዊና አሉታዊ ጎን አላቸው። ሌሎች ወላጆች የተጠቀሙባቸውን አማራጮች ለምን አትጠይቋቸውም? መጽሐፍ ቅዱስ “ምክር በሚሹ ዘንድ . . . ጥበብ ትገኛለች” ይላል።—ምሳሌ 13:10

 ልጃችሁን ወደ ሕፃናት ማቆያ ማዕከል ለመላክ ከወሰናችሁ የሚከተሉትን ነገሮች አድርጉ፦

 ስለ ማዕከሉ ለማወቅ ሞክሩ

 •   ማዕከሉ ሕጉ በሚጠይቀው መሠረት ፈቃድ የተሰጠውና እንዲህ ካሉ ማዕከላት የሚጠበቀውን መሥፈርት የሚያሟላ ነው? ምን ማረጋገጫ ተሰጥቶታል? ምን ዓይነት ስምስ አትርፏል?

 •   ተቋሙ ንጹሕና ለደህንነት ስጋት የማይፈጥር ነው?

 •   በማዕከሉ ውስጥ ልጆች በምን ዓይነት እንቅስቃሴዎች ይካፈላሉ? a

 ስለ ሞግዚቶቹ ለማወቅ ሞክሩ

 •   ምን ሥልጠና አግኝተዋል? ሥልጠናው ሕፃናትን የማስተማር ሙያን፣ የመጀመሪያ ሕክምና እርዳታን እንዲሁም ልባቸውና ሳንባቸው መሥራቱን ላቆመ ሰዎች የሚሰጥ እርዳታን ሊጨምር ይችላል።

 •   ልጃችሁን እንዲንከባከቡላችሁ አምናችሁ የምትሰጧቸው ሰዎች በወንጀል ድርጊት ተጠይቀው የሚያውቁ መሆን አለመሆናቸውን ማጣራት የምትችሉበት መንገድ አለ?

 •   ሞግዚቶቹ ቶሎ ቶሎ ይቀያየራሉ? ይህ ከሆነ ልጃችሁ በየጊዜው ከአዳዲስ ሞግዚቶች ጋር መላመድ ሊያስፈልገው ይችላል ማለት ነው።

 •   በማዕከሉ ውስጥ ያሉት ሞግዚቶች ብዛት ከሕፃናቱ ብዛት ጋር ሲወዳደር እንዴት ነው? ልጆቹ ብዙ ሆነው ሞግዚቶቹ ግን ጥቂት ከሆኑ ልጃችሁ የሚያስፈልገውን ትኩረት ላያገኝ ይችላል። እርግጥ ነው፣ አንድ ልጅ ምን ያህል ትኩረት ያስፈልገዋል የሚለው ጉዳይ፣ በልጁ ዕድሜና ሁኔታ ላይ የተመካ ነው።

 •   ሞግዚቶቹ እነሱንም ሆነ እናንተን ስላሳሰቧችሁ ነገሮች ለመወያየት ፈቃደኛ ናቸው?

a ለምሳሌ ያህል፣ ልጆች ሙሉ ቀን ቴሌቪዥን ሲያዩ እንዲውሉ ይደረጋሉ ወይስ አእምሮንና አካልን ይበልጥ በሚያሠሩ እንቅስቃሴዎች ይካፈላሉ?