በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ለቤተሰብ

ልጄን ጉልበተኞች ቢያስቸግሩት ምን ላድርግ?

ልጄን ጉልበተኞች ቢያስቸግሩት ምን ላድርግ?

ልጃችሁ ትምህርት ቤት ጉልበተኛ ልጆች እንዳስቸገሩት ነገራችሁ እንበል። ምን ታደርጋላችሁ? ትምህርት ቤቱ ጉልበተኞቹን እንዲቀጣቸው ትጠይቃላችሁ? ወይስ ልጃችሁ አጸፋውን እንዲመልስ ታሠለጥኑታላችሁ? ውሳኔ ከማድረጋችሁ በፊት ጉልበተኞች የሚሰነዝሩትን ጥቃት በተመለከተ አንዳንድ ነጥቦችን ልብ በሉ። *

 ጉልበተኞች የሚሰነዝሩትን ጥቃት በተመለከተ ምን ማወቅ ይኖርብኛል?

‘ጉልበተኞች’ ስንል ምን ማለታችን ነው? ጉልበተኞች ስንል ሆነ ብለው እና በተደጋጋሚ አካላዊ ወይም ስሜታዊ ጥቃት የሚሰነዝሩ ልጆችን መጥቀሳችን ነው። በመሆኑም ልጃችሁ ስለተሰደበ ወይም ደስ የማይል ነገር ስለተደረገበት ብቻ ጉልበተኞች ጥቃት ሰንዝረውበታል ብሎ መናገር አይቻልም።

ይህን ማወቅ ለምን አስፈለገ? አንዳንድ ልጆች ትንሽም ሆነ ትልቅ ደስ የማይል ነገር ስለተደረገባቸው ብቻ ጉልበተኞች ጥቃት እንደሰነዘሩባቸው ይናገራሉ። ይሁንና ልጃችሁ ትንሽ ነገር እንኳ ሲያጋጥመው ጣልቃ የምትገቡ ከሆነ አለመግባባቶችን የመፍታት ችሎታ እንዳያዳብር እንቅፋት ትሆኑበታላችሁ፤ ይህ ደግሞ አሁንም ሆነ ትልቅ ሰው ሲሆን የሚያስፈልገው ችሎታ ነው።

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ለቁጣ አትቸኩል።”—መክብብ 7:9

ዋናው ነጥብ፦ አንዳንድ ጊዜ ጣልቃ ገብታችሁ እርምጃ መውሰድ ሊያስፈልጋችሁ ይችላል፤ ይሁንና አንዳንድ ሁኔታዎችን ልጃችሁ ችግሮችን የመቋቋምና ሰዎችን እንደ ባሕርያቸው የመያዝ ችሎታን እንዲያዳብር የሚያስችሉ አጋጣሚዎች አድርጋችሁ ተመልከቷቸው።—ቆላስይስ 3:13

ይሁንና ልጃችሁ ጉልበተኞች ሆነ ብለው በተደጋጋሚ ጥቃት እየሰነዘሩበት እንደሆነ ቢነግራችሁስ?

 ልጄን መርዳት የምችለው እንዴት ነው?

 • ልጃችሁን በትዕግሥት አዳምጡት። ልጃችሁ (1) ምን እየደረሰበት እንዳለ እንዲሁም (2) ጥቃት እየተሰነዘረበት ያለው ለምን እንደሆነ ለማወቅ ሞክሩ። የተሟላ መረጃ ሳታገኙ መደምደሚያ ላይ ለመድረስ አትቸኩሉ። ‘ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የማላውቀው ነገር ይኖር ይሆን?’ ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ። የተሟላ መረጃ ለማግኘት የልጃችሁን አስተማሪ ወይም የሌላኛውን ልጅ ወላጆች ማነጋገር ሊኖርባችሁ ይችላል።

  የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “እውነታውን ከመስማቱ በፊት መልስ የሚሰጥ ሰው፣ ሞኝነት ይሆንበታል፤ ውርደትም ይከናነባል።”—ምሳሌ 18:13

 • ልጃችሁ ጉልበተኞች ጥቃት እየሰነዘሩበት ከሆነ፣ የሚሰጠው ምላሽ ችግሩን ሊያሻሽለው ወይም ሊያባብሰው እንደሚችል ንገሩት። ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ “የለዘበ መልስ ቁጣን ያበርዳል፤ ክፉ ቃል ግን ቁጣን ያነሳሳል” ይላል። (ምሳሌ 15:1) ደግሞም አጸፋ መመለስ ችግሩ እንዲቀንስ ከማድረግ ይልቅ እንዲባባስ ያደርጋል።

  የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ክፉን በክፉ ወይም ስድብን በስድብ አትመልሱ።”—1 ጴጥሮስ 3:9

 • አጸፋ አለመመለሱ ፈሪ እንደማያስብለው ለልጃችሁ ግለጹለት። እንዲያውም በተቃራኒው ሌሎች እንዲቆጣጠሩት አለመፍቀዱ ጠንካራ መሆኑን ያሳያል። እንዲህ ማድረጉ ጉልበተኛ መሆን ሳያስፈልገው ጉልበተኞችን እንዲያሸንፍ ያስችለዋል።

  በተለይ ልጃችሁ ጥቃት የሚሰነዘርበት በኢንተርኔት አማካኝነት ከሆነ ይህን ማወቁ ወሳኝ ነው። ልጃችሁ በኢንተርኔት አማካኝነት ጥቃት ለሚሰነዝርበት ሰው በቁጣ ምላሽ የሚሰጥ ከሆነ ጉልበተኛው ጥቃት መሰንዘሩን እንዲቀጥል በር ይከፍትለታል፤ ይባስ ብሎም ልጃችሁ ራሱ ጉልበተኛ እንደሆነ ሊያስመስልበት ይችላል! በመሆኑም ከሁሉ የተሻለው ምላሽ ዝምታ ሊሆን ይችላል፤ ይህ ዘዴ አብዛኛውን ጊዜ ጉልበተኛው ጥቃት መሰንዘሩን እንዲያቆም ያደርገዋል።

  የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “እንጨት ከሌለ እሳት ይጠፋል።”—ምሳሌ 26:20

 • ልጃችሁ ለጉልበተኞች ጥቃት ሊያጋልጡት ከሚችሉ ሰዎች ወይም ቦታዎች መራቅ ይችል ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ የሚያስቸግረው ልጅ ወይም ልጆች የት እንደሚሆኑ ካወቀ መንገድ ሊቀይር ይችላል።

  የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ብልህ ሰው አደጋ ሲያይ ይሸሸጋል፤ ተሞክሮ የሌለው ግን ዝም ብሎ ይሄዳል፤ መዘዙንም ይቀበላል።”—ምሳሌ 22:3

የልጃችሁን አስተማሪ ወይም የሌላኛውን ልጅ ወላጆች ማነጋገር ሊኖርባችሁ ይችላል

እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ ልጃችሁ ያሉት አማራጮች ያላቸውን ጥቅምና ጉዳት እንዲያመዛዝን እርዱት። ለምሳሌ ያህል፦

 • ጉልበተኛውን ችላ ብሎት ቢያልፍስ?

 • ኮስተር ብሎ ጉልበተኛውን “እረፍ” ቢለውስ?

 • ስለ ጉልበተኛው ለአስተማሪው ቢናገርስ?

 • በጨዋታ ወይም በቀልድ ጉልበተኛውን ማስቆም ይችል ይሆን?

ጉልበተኞቹ ጥቃት የሚሰነዝሩት ፊት ለፊትም ሆነ በኢንተርኔት አማካኝነት፣ ለሁሉም ሁኔታ የሚሠራ መፍትሔ ማግኘት አይቻልም። ስለዚህ ለልጃችሁ ሁኔታ ተስማሚ የሆነ መፍትሔ አብራችሁ ፈልጉ። ድጋፋችሁ እንደማይለየውም አረጋግጡለት።

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “እውነተኛ ወዳጅ ምንጊዜም አፍቃሪ ነው፤ ደግሞም ለመከራ ቀን የተወለደ ወንድም ነው።”—ምሳሌ 17:17

^ አን.3 ይህ ርዕስ የሚናገረው ስለ ወንድ ልጆች ቢሆንም የተጠቀሱት ምክሮች ለሴት ልጆችም ይሠራሉ።