በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ንድፍ አውጪ አለው?

ጋኔቶች ወደ ውኃ የሚጠልቁበት መንገድ

ጋኔቶች ወደ ውኃ የሚጠልቁበት መንገድ

 ጋኔቶች ትላልቅ የባሕር ወፎች ሲሆኑ በሰዓት 190 ኪሎ ሜትር በሚደርስ ፍጥነት ወደ ውቅያኖስ መጥለቅ ይችላሉ። ጋኔቶች ወደ ውኃው ሲጠልቁ የሚያርፍባቸው ኃይል ከመሬት ስበት 20 እጥፍ የሚበልጥ ነው። ታዲያ ጋኔቶች ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው በዚህ መልኩ በተደጋጋሚ መጥለቅ የሚችሉት እንዴት ነው?

 እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ ጋኔቶች ወደ ውኃው ከመድረሳቸው በፊት ክንፎቻቸውን ወደ ኋላ በማጠፍ ሰውነታቸው የቀስት ቅርጽ እንዲኖረው ያደርጋሉ። በተጨማሪም ዓይናቸውን ከጉዳት ለመከላከል ሽፋን ያለብሱታል። ከዚህም ሌላ ጋኔቶች በአንገታቸውና በደረታቸው አካባቢ ያሉ የአካል ክፍሎቻቸውን እንደ ፊኛ በመንፋት ወደ ውኃው በሚጠልቁበት ጊዜ በአካላቸው ላይ ጉዳት እንዳይደርስ መከላከል ይችላሉ።

 ጋኔቶች ወደ ውቅያኖሱ ጠልቀው ሲገቡ መንቁራቸው፣ ጭንቅላታቸውና አንገታቸው ሦስት ማዕዘን ቅርጽ ይሠራል። ይህ ቅርጽ የውኃው ግፊት አንድ ጡንቻ ላይ ብቻ ከማረፍ ይልቅ አንገታቸው ላይ ባሉት ሁሉም ጡንቻዎች ላይ እንዲያርፍ ያደርጋል። ከዚያም ወፎቹ ዓይናቸው ውኃ ውስጥ መመልከት እንዲችል እይታቸውን ወዲያውኑ ያስተካክላሉ።

 ጋኔቶች ምን ያህል መጥለቅ ይችላሉ? የሚመጡበት ፍጥነት እስከ 11 ሜትር ድረስ ሊወስዳቸው ቢችልም በግማሽ የታጠፉ ክንፎቻቸውን በማንቀሳቀስና እግሮቻቸውን በማንፈራገጥ ይበልጥ መጥለቅ ይችላሉ። እንዲያውም ውቅያኖሱ ውስጥ ከ25 ሜትር በላይ ጠልቀው መግባት እንደሚችሉ ተስተውሏል። ከዚያም በቀላሉ ወደ ላይ በመንሳፈፍ ከውኃው መውጣትና እንደገና መብረር ይችላሉ።

 ጋኔቶች ሲጠልቁ ተመልከት

 ተመራማሪዎች በነፍስ አድን ሥራ የሚሳተፉ ጋኔት መሳይ ሮቦቶችን ሠርተዋል። እነዚህ ሮቦቶች መብረር፣ ወደ ውኃ መጥለቅ ከዚያም መልሰው መብረር እንዲችሉ ተፈልጎ ነበር። ሆኖም ለሙከራ የተሠራው ሮቦት ውኃውን በከፍተኛ ኃይል ስለመታው ተሰባብሯል። በዚህ የተነሳ ተመራማሪዎቹ ሮቦቱ “የጋኔቶችን ያህል የመጥለቅ ችሎታ እንደሌለው” ደምድመዋል።

 ታዲያ ምን ይመስልሃል? የጋኔቶች የመጥለቅ ችሎታ የተገኘው በዝግመተ ለውጥ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?