በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ንድፍ አውጪ አለው?

የባሕር ኪያር አስገራሚ ቆዳ

የባሕር ኪያር አስገራሚ ቆዳ

የባሕር ኪያር በባሕር ወለልና በኮራል ሪፎች ላይ የሚኖር እንስሳ ነው። የባሕር ኪያር ቆዳው አባጣ ጎርባጣ ወይም እሾሃማ ሊሆን ይችላል። የባሕር ኪያር እንደ አስፈላጊነቱ አካሉን የመለዋወጥ አስደናቂ ችሎታ አለው፤ በደቂቃዎች ወይም በሴኮንዶች ውስጥ ተለውጦ እንደ ሰም ለስላሳ ወይም እንደ ጣውላ ደረቅ ሊሆን ይችላል። ይህ ችሎታው በጠባብ ቀዳዳዎች ውስጥ ተሽሎክሉኮ እንዲገባ ያስችለዋል፤ ከዚያም ሌሎች የባሕር እንስሳት አውጥተው እንዳይበሉት ደረቅ ይሆናል። የባሕር ኪያር እንዲህ ያለ ችሎታ የኖረው በአስገራሚ ቆዳው የተነሳ ነው።

እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ የባሕር ኪያር ቆዳ ደረቅ፣ መካከለኛ ወይም ለስላሳ ሊሆን ይችላል። የባሕር ኪያር ቆዳውን ከአንዱ ወደ ሌላው የሚቀያይረው በቆዳው ውስጥ ያሉ ጭረቶችን (ፋይበሮች) በማቆላለፍ ወይም በማላቀቅ ነው። ይህን ለማድረግ የሚያደርቁ ወይም የሚያለሰልሱ ፕሮቲኖችን ይጠቀማል።

የሚያደርቁ ፕሮቲኖች በቆዳው ውስጥ ያሉ ጭረቶችን በማያያዝ እንዲቆላለፉ ወይም እንዲተሳሰሩ ያደርጋሉ፤ ይህም ቆዳው ደረቅ እንዲሆን ያደርጋል። የሚያለሰልሱ ፕሮቲኖች ደግሞ እነዚህ ጭረቶች እንዲላቀቁ ያደርጋሉ፤ ይህም ቆዳው ለስላሳ እንዲሆን ያደርጋል። የባሕር ኪያር ቆዳ እየቀለጠ ያለ እስኪመስል ድረስ ሊለሰልስ ይችላል።

ሳይንቲስቶች የባሕር ኪያር ቆዳ ያለውን ራሱን የመለዋወጥ ችሎታ በመኮረጅ የተለያዩ መሣሪያዎችን ለመሥራት እየሞከሩ ነው። ለምሳሌ ለአንጎል ቀዶ ሕክምና የሚውሉ ኤሌክትሮዶችን ለመሥራት ይፈልጋሉ። እነዚህ ኤሌክትሮዶች አንጎል ውስጥ በትክክለኛው ቦታ ላይ እንዲቀመጡ ደረቅ መሆን ያስፈልጋቸዋል፤ ሆኖም ቦታው ላይ ከደረሱ በኋላ ለስላሳ ይሆናሉ። ኤሌክትሮዶቹ ተለዋዋጭ መሆናቸው የታካሚው ሰውነት እንዳይቆጣና ቀዶ ሕክምናው በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን ያስችላል።

ታዲያ ምን ይመስልሃል? የባሕር ኪያር አስገራሚ ቆዳ በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?