በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

Todd Aki/Moment Open via Getty Images

ንድፍ አውጪ አለው?

ማንታ ሬይ የተባለው ዓሣ የማጣሪያ ሥርዓት

ማንታ ሬይ የተባለው ዓሣ የማጣሪያ ሥርዓት

ማንታ ሬይ የተባሉት ዓሣዎች የሚመገቡት፣ በሚዋኙበት ጊዜ የባሕር ውኃንና ባሕር ውስጥ የሚበቅሉ ተክሎችን አፋቸው ውስጥ በማስገባት ነው። በመጀመሪያ ተክሉ ከውኃው ጋር ተቀላቅሎ ወደ ዓሣው የማጣሪያ አካል ይሄዳል፤ በኋላም ወደ ዓሣው ጉሮሮ ይገባና ዓሣው ይመገበዋል። ውኃው ደግሞ በዓሣው ስንጥብ በኩል ወደ ውጭ ይወጣል። የሚገርመው ማንታ ሬይ የተባሉት ዓሣዎች ከማጣሪያ ቀዳዳቸው በጣም ያነሱ የባሕር ተክሎችን እንኳ ከውኃው ለይተው ማስቀረት ይችላሉ። የሳይንስ ዘጋቢ የሆነው ኤድ ዮንግ እንደተናገረው “ይህ ፈጽሞ የማይቻል የሚመስል ነገር ነው።”

እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ የዚህ ዓሣ የማጣሪያ ሥርዓት በሁለት በኩል ጥርስ ያላቸው ማበጠሪዎች የሚመስሉ አምስት ቀዳዳዎች አሉት። ከእነዚህ ጥርሶች መካከል አንዳንዶቹ ወደ ፊት አንዳንዶቹ ደግሞ ወደ ኋላ ያዘነበሉ ናቸው። እነዚህ ጥርሶች የባሕሩን ውኃ በመከፋፈል የተወሰነው ከጥርሶቹ በላይ የተወሰነው ደግሞ በጥርሶቹ መካከል እንዲያልፍ ያደርጋሉ፤ ይህም ትናንሽ የውኃ እሽክርክሪቶችን ይፈጥራል።

የባሕር ተክል ወይም ሌላ ዓይነት ምግብ የጥርሶቹን ጫፍ ሲነካ ወደ ጉሮሮው አቅጣጫ በሚፈሰው ይበልጥ ፍጥነት ያለው ውኃ ተወስዶ ወደ ዓሣው ጉሮሮ ይገባል፤ ከዚያም ዓሣው ምግቡን ይውጠዋል። ትንሽ ከመሆናቸው የተነሳ በጥርሶቹ መካከል የሚገቡ የባሕር ተክሎችም እንኳ ወደ ዓሣው ጉሮሮ ይወሰዳሉ፤ ምክንያቱም እሽክርክሪቱ ተክሎቹ ይበልጥ ፍጥነት እንዲኖራቸው በማድረግ ወደ ጉሮሮው አቅጣጫ ተስፈንጥረው በውኃው እንዲወሰዱ ያደርጋቸዋል። ይህ የማጣሪያ ሥርዓት ዓሣው በማጣሪያ ጥርሶቹ መካከል ሾልከው ወደ ባሕሩ ሊወጡ የሚችሉ ጥቃቅን ምግቦችን እንዲይዝ ያስችለዋል።

በተጨማሪም ማንታ ሬይ የተባለው ዓሣ ማጣሪያዎች፣ ዓሣው የቱንም ያህል በፍጥነት ቢዋኝ ወይም በውኃው ውስጥ ያሉት የባሕር ተክሎች የቱንም ያህል ጥቅጥቅ ያሉ ቢሆኑ የመደፈን ችግር አያጋጥመውም፤ በዚያ ላይ የማጣሪያ ሥርዓቱ ራሱን በራሱ ያጸዳል።

ተመራማሪዎች ይህ ዓሣ የሚያጣራበትን ዘዴ በመኮረጅ ቆሻሻ ውኃን የሚያጸዳና ጎጂ የሆኑ ጥቃቅን ፕላስቲኮችን ለይቶ የሚያወጣ ማጣሪያ የመሥራት ፍላጎት አላቸው።

ታዲያ ምን ይመስልሃል? ማንታ ሬይ የተባለው ዓሣ የማጣሪያ ሥርዓት በዝግመተ ለውጥ የመጣ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?