በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ደም ማነስ—መንስኤው፣ ምልክቶቹና ሕክምናው

ደም ማነስ—መንስኤው፣ ምልክቶቹና ሕክምናው

ቤት የተባለች አንዲት ሴት እንዲህ ብላለች፦ “ደም ማነስ የያዘኝ በአሥራዎቹ ዕድሜ ሳለሁ ነው። ቶሎ ይደክመኝ፣ አጥንቶቼን ይቆረጥመኝ፣ እንዲሁም ትኩረቴ በቀላሉ ይከፋፈል ነበር። ሐኪሜ የብረት ማዕድን አዘዘልኝ። ኪኒኖቹን መውሰድ ጀመርኩ፤ አመጋገቤንም አስተካከልኩ። ብዙም ሳይቆይ ጤንነቴ ተሻሻለ።”

ቤት የያዛት በሽታ በጣም የተለመደ የጤና እክል ነው። የዓለም የጤና ድርጅት እንደገለጸው ከሆነ ሁለት ቢሊዮን ሕዝብ ማለትም ከዓለም ሕዝብ 30 በመቶ የሚያህለው ደም ማነስ አለበት። በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ውስጥ ከነፍሰ ጡር ሴቶች መካከል 50 በመቶ የሚሆኑት፣ ዕድሜያቸው ለትምህርት ካልደረሰ ሕፃናት መካከል ደግሞ 40 በመቶ የሚሆኑት ደም ማነስ አለባቸው።

ደም ማነስ ከባድ ችግር ሊያስከትል ይችላል። በሽታው ሲባባስ የልብ ሕመም አንዳንድ ጊዜም የልብ ድካም ያስከትላል። የዓለም የጤና ድርጅት እንደተናገረው በአንዳንድ አገሮች ውስጥ “20 በመቶ የሚሆኑት እናቶች የሚሞቱት” በደም ማነስ ነው። በብረት እጥረት ምክንያት የሚመጣ ደም ማነስ (በጣም የተለመደው የደም ማነስ ዓይነት) ያለባቸው እናቶች የሚወልዷቸው ሕፃናት ጊዜያቸው ሳይደርስ ሊወለዱ ወይም ክብደታቸው በጣም አነስተኛ ሊሆን ይችላል። ደም ማነስ ያለባቸው ሕፃናት እድገታቸው ዘገምተኛ ሊሆን ወይም ለኢንፌክሽን ተጋላጭ ሊሆኑ ይችላሉ። ይሁንና አብዛኛውን ጊዜ፣ በብረት እጥረት ምክንያት የሚመጣውን ደም ማነስ መከላከል ወይም ማዳን ይቻላል። *

ደም ማነስ ምንድን ነው?

ደም ማነስ የጤና እክል ነው። በዚህ በሽታ የሚጠቁ ሰዎች በቂ የሆኑ ጤናማ ቀይ የደም ሴሎች የሏቸውም። ይህ የሚሆነው በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ነው። እንዲያውም የሳይንስ ሊቃውንት ከ400 የሚበልጡ የደም ማነስ ዓይነቶች እንዳሉ ይናገራሉ! በሽታው የሚድን ወይም የማይድን እንዲሁም ቀላል ወይም ከባድ ሊሆን ይችላል።

ደም ማነስ መንስኤው ምንድን ነው?

ደም ማነስ የሚከሰተው በሦስት ዋና ዋና ምክንያቶች የተነሳ ነው፤ እነሱም፦

 • ብዙ ደም በመፍሰሱ የተነሳ በሰውነታችን ውስጥ ያሉት ቀይ የደም ሴሎች ሲመናመኑ።

 • ሰውነታችን ጤናማ ቀይ የደም ሴሎችን በበቂ መጠን ማምረት ሲሳነው።

 • ሰውነታችን ቀይ የደም ሴሎችን ማጥፋት ሲጀምር።

በዓለም ላይ በጣም የተስፋፋው የደም ማነስ ዓይነት በብረት እጥረት ምክንያት የሚከሰተው ደም ማነስ ነው። ቀይ የደም ሴሎች ኦክስጅን ማጓጓዝ እንዲችሉ የሚያደርገው ሂሞግሎቢን ነው፤ ሰውነታችን በቂ የብረት ማዕድን ካላገኘ ጤናማ ሂሞግሎቢን በበቂ መጠን መሥራት አይችልም።

በብረት እጥረት ምክንያት የሚከሰተው ደም ማነስ ምልክቶች ምንድን ናቸው?

በደም ማነስ የተያዘ ሰው መጀመሪያ አካባቢ በሽታው እንዳለበት እንኳ ላያስተውል ይችላል። በብረት እጥረት ምክንያት የሚከሰተው ደም ማነስ የተለያዩ ምልክቶች ሊኖሩት ይችላሉ፤ አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው፦

 • ከመጠን ያለፈ ድካም

 • የእጅና የእግር መቀዝቀዝ

 • አቅም ማጣት

 • የቆዳ መገርጣት

 • ራስ ምታትና ማዞር

 • የደረት ሕመም፣ ፈጣን የልብ ምት፣ የትንፋሽ መቆራረጥ

 • የጥፍር መሰነጣጠቅ

 • የምግብ ፍላጎት አለመኖር፣ በተለይ በሕፃናትና በልጆች ላይ

 • በረዶ፣ ስታርች ወይም አፈር የመብላት ፍላጎት

ለበሽታው ተጋላጭ የሆኑት እነማን ናቸው?

ሴቶች በወር አበባ ወቅት ደም ስለሚፈሳቸው በብረት እጥረት ምክንያት ለሚከሰት ደም ማነስ ተጋላጭ ናቸው። ነፍሰ ጡር ሴቶችም የቫይታሚን ቢ ዓይነት በሆነው በፎሌት (ፎሊክ አሲድ) የበለጸገ ምግብ ካልተመገቡ ለበሽታው ተጋላጭ ይሆናሉ።

ሕፃናት፦ ከእናት ጡት ወተት ወይም ከፎርሙላ ወተት በቂ የብረት ማዕድን የማያገኙ ጊዜያቸው ሳይደርስ የተወለዱ ወይም ክብደታቸው አነስተኛ የሆነ ሕፃናት።

ልጆች፦ የተመጣጠነ ምግብ የማይመገቡ ልጆች።

አትክልት ብቻ የሚመገቡ ሰዎች በብረት ማዕድን የበለጸጉ ምግቦችን የማይመገቡ ከሆነ ለበሽታው ተጋላጭ ይሆናሉ።

የማይድን በሽታ የያዛቸው ሰዎች፦ ለምሳሌ ከደም ጋር የተያያዙ በሽታዎች፣ ካንሰር፣ የኩላሊት በሽታ፣ ሰውነት ውስጥ ያለ ቁስል ወይም ኢንፌክሽን ያለባቸው ሰዎች።

ደም ማነስን ማከም የሚቻለው እንዴት ነው?

መከላከል ወይም ማዳን የሚቻለው ሁሉንም የደም ማነስ ዓይነቶች አይደለም። ሆኖም በብረት ወይም በቫይታሚን እጥረት ምክንያት የሚከሰት ደም ማነስን አብዛኛውን ጊዜ መከላከል ወይም ማዳን ይቻላል፤ ይህን ማድረግ የሚቻለው በሚከተሉት ንጥረ ነገሮች የበለጸገ አመጋገብ በመከተል ነው፦

ብረት። በሥጋ፣ በባቄላ ዝርያዎች፣ በምስርና እንደ ጎመን ባሉ አትክልቶች ውስጥ ይገኛል። * በተጨማሪም የብረት ድስት ተጠቅሞ ማብሰል በምግብ ውስጥ ያለውን የብረት መጠን ከፍ ሊያደርገው እንደሚችል ጥናቶች ይጠቁማሉ።

ፎሌት። በፍራፍሬ፣ እንደ ጎመን ባሉ አትክልቶች፣ በአተር ዝርያዎች፣ በቦሎቄ፣ በአይብ፣ በእንቁላል፣ በዓሣ፣ በአልሞንድ እና በለውዝ ውስጥ ይገኛል። ቫይታሚን በተጨመረባቸው እንደ ዳቦ፣ ፓስታና ሩዝ ያሉ የእህል ምርቶች ውስጥም ይገኛል። ሰው ሠራሽ የሆነው ፎሌት፣ ፎሊክ አሲድ ይባላል።

ቫይታሚን ቢ-12። በሥጋ፣ በወተት ተዋጽኦዎች እንዲሁም በአኩሪ አተር ምርቶች ውስጥ ይገኛል።

ቫይታሚን ሲ። እንደ ብርቱካንና ሎሚ ባሉ የፍራፍሬ ዝርያዎችና ጭማቂዎች፣ በቃርያ፣ በብሮኮሊ፣ በቲማቲም፣ በሜሎን እና በእንጆሪ ውስጥ ይገኛል። በቫይታሚን ሲ የበለጸጉ ምግቦች ሰውነታችን የብረት ማዕድንን ጥቅም ላይ እንዲያውል ያስችሉታል።

በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ምግቦች ይለያያሉ። ስለዚህ በአካባቢያችሁ ካሉ ምግቦች ውስጥ የሚያስፈልጓችሁን ንጥረ ነገሮች የያዙት የትኞቹ እንደሆኑ ለማወቅ ሞክሩ። ሴቶች በተለይም ነፍሰ ጡር የሆኑ ወይም ልጅ ለመውለድ የሚያስቡ ሴቶች ይህን ማድረጋቸው አስፈላጊ ነው። እናቶች የራሳቸውን ጤንነት መጠበቃቸው የሚወልዷቸው ልጆች በደም ማነስ እንዳይጠቁ እገዛ ያደርጋል። *

^ አን.4 በዚህ ርዕስ ውስጥ የሚገኘው ስለ አመጋገብና ተያያዥ ነገሮች የሚገልጸው መረጃ በዋነኝነት የተውጣጣው ከሜዮ ክሊኒክ እና ዘ ጌል ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ነርሲንግ ኤንድ አላይድ ኸልዝ ነው። ደም ማነስ እንዳለብህ ከጠረጠርክ የሕክምና ባለሙያ አማክር።

^ አን.32 ሐኪም ሳታማክር የብረት ማዕድን የያዙ ኪኒኖችን መውሰድ ወይም ለልጆችህ መስጠት የለብህም። ከመጠን ያለፈ የብረት ማዕድን መውሰድ ጉበትን ሊጎዳ እንዲሁም ሌሎች ጉዳቶችን ሊያስከትል ይችላል።

^ አን.36 አንዳንድ ጊዜ ደም ማነስ የሚታከመው ደም በመውሰድ ነው፤ የይሖዋ ምሥክሮች እንዲህ ያለውን ሕክምና አይቀበሉም።—የሐዋርያት ሥራ 15:28, 29