በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ  |  ቁጥር 3 2017

በዚህ የኪዩኒፎርም ጽላት በአንደኛው ጎን ላይ “ታታኑ” የሚለው ስም ተጽፎ ይገኛል

ተጨማሪ ማስረጃ

ተጨማሪ ማስረጃ

የመጽሐፍ ቅዱስን ዘገባ የሚደግፉ አርኪኦሎጂያዊ ማስረጃዎች አሉ? ቢብሊካል አርኪኦሎጂ ሪቪው የተሰኘ አንድ መጽሔት በ2014 ይዞት የወጣው ርዕስ “በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ከተጠቀሱት ሰዎች መካከል አርኪኦሎጂያዊ ማስረጃ የተገኘላቸው ምን ያህሎቹ ናቸው?” ለሚለው ጥያቄ ማብራሪያ ሰጥቷል። መጽሔቱ “ቢያንስ 50” የሚሆኑት አርኪኦሎጂያዊ ማስረጃ እንደተገኘላቸው ገልጿል! በዚያ ርዕስ ላይ ካልተጠቀሱት ሰዎች መካከል አንዱ ታተናይ ነው። ታተናይ ማን ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ እሱ ምን እንደተባለ እስቲ እንመልከት።

ኢየሩሳሌም በአንድ ወቅት የፋርስ ግዛት ክፍል ነበረች። ከተማዋ የምትገኘው ፋርሳውያን ‘ከወንዙ ባሻገር ያለው ክልል’ ብለው ይጠሩት በነበረው ከኤፍራጥስ በስተ ምዕራብ ባለው አካባቢ ነበር። ፋርሳውያን ባቢሎንን ድል ካደረጉ በኋላ በዚያ የሚገኙትን አይሁዳውያን ምርኮኞች በመልቀቅ በኢየሩሳሌም የይሖዋን ቤተ መቅደስ ዳግመኛ እንዲገነቡ ፈቀዱላቸው። (ዕዝራ 1:1-4) ይሁንና የአይሁዳውያን ጠላቶች የቤተ መቅደሱን ግንባታ ከመቃወማቸውም በላይ አይሁዳውያን ይህን የሚያደርጉት በፋርስ ላይ በማመፅ እንደሆነ የሚገልጽ ክስ ሰነዘሩባቸው። (ዕዝራ 4:4-16) በቀዳማዊ ዳርዮስ የግዛት ዘመን (522-486 ዓ.ዓ.) ታተናይ የተባለ የፋርስ ባለሥልጣን ይህን ለማጣራት ምርመራ አካሄደ። መጽሐፍ ቅዱስ ታተናይን “ከወንዙ ባሻገር ያለው ክልል ገዢ” በማለት ይጠራዋል።—ዕዝራ 5:3-7

ታተናይ የሚለውን ስም የያዙ በርካታ የኪዩኒፎርም ጽላቶች ተገኝተዋል፤ ጽላቶቹ የአንድ ቤተሰብን ታሪካዊ መረጃ የያዙ ሰነዶች ሳይሆኑ አይቀሩም። ከእነዚህ ጽላቶች አንዱ የዚህ ቤተሰብ አባል የሆነን አንድ ሰው ከታተናይ ጋር አያይዞ ይጠቅሳል፤ ጽላቱ በቀዳማዊ ዳርዮስ 20ኛ የግዛት ዘመን ማለትም በ502 ዓ.ዓ. የተጻፈን አንድ የክፍያ ውል የያዘ ነው። የውሉ ምሥክር “ከወንዙ ባሻገር ያለው ክልል ገዢ የሆነው የታታኑ” አገልጋይ እንደሆነ ጽላቱ ላይ ተገልጿል፤ እዚህ ላይ የተጠቀሰው ታታኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባለው የዕዝራ መጽሐፍ ላይ የተጠቀሰው ታተናይ ነው።

ይህ ሰው ያለው ሥልጣን ምን ነበር? ታላቁ ቂሮስ በ535 ዓ.ዓ. ግዛቱን በአውራጃዎች ከፋፍሎ ነበር፤ ከእነዚህ አውራጃዎች አንዱ ባቢሎንና ከወንዙ ባሻገር ያለው ክልል በመባል ይጠራ ነበር። ከጊዜ በኋላ ይህ አውራጃ ለሁለት ተከፈለና አንዱ “ከወንዙ ባሻገር ያለው ክልል” ተብሎ መጠራት ጀመረ። ይህ ክልል ኮይሌ-ሶርያን፣ ፊንቄን፣ ሰማርያንና ይሁዳን ይጨምር ነበር፤ የዚህ ክልል ገዢ በደማስቆ ተቀምጦ ይገዛ የነበረ ይመስላል። ታተናይ ከ520 እስከ 502 ዓ.ዓ. ድረስ ይህን ክልል ገዝቷል።

ታተናይ ‘አይሁዳውያን ዓምፀዋል’ የሚለውን ክስ ለመመርመር ወደ ኢየሩሳሌም ከተጓዘ በኋላ አይሁዳውያኑ ‘የይሖዋን ቤተ መቅደስ መልሶ ለመገንባት ከቂሮስ ፈቃድ አግኝተናል’ እንዳሉ ለዳርዮስ ገለጸለት። ከዚያም በግምጃ ቤቱ ውስጥ የተደረገው ምርመራ አይሁዳውያኑ የተናገሩት ነገር ትክክል እንደሆነ አረጋገጠ። (ዕዝራ 5:6, 7, 11-13፤ 6:1-3) በመሆኑም ታተናይ በግንባታው ላይ ጣልቃ እንዳይገባ ታዘዘ፤ እሱም እንደታዘዘው አደረገ።—ዕዝራ 6:6, 7, 13

እርግጥ ነው፣ “ከወንዙ ባሻገር ያለው ክልል ገዢ የሆነው ታተናይ” በታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሰው አይደለም። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስሙ እንደተጠቀሰና የተሰጠው ማዕረግም ትክክለኛ እንደሆነ ልብ በል። ይህ እውነታ የአርኪኦሎጂ ግኝቶች መጽሐፍ ቅዱስ ከታሪክ አኳያ ትክክል እንደሆነ እንደሚያረጋግጡ የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ ነው።