“ኢየሱሳዊው ካርዲናል ሆርሃ ማርዮ ቤርጎልዮ የጳጳሳት ጳጳስ ሆነው ተመርጠዋል፤ በመሆኑም ጴጥሮስን የሚተኩ 265ኛው ሰው ናቸው።”—የቫቲካን የመረጃ አገልግሎት (እንግሊዝኛ)፣ ቫቲካን ሲቲ፣ መጋቢት 13, 2013

“የሮም ሊቀ ጳጳስ የዓለም አቀፉ ቤተ ክርስቲያን የበላይ ናቸው፤ ይህም የሆነው የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ በመሆናቸው ነው። ለጴጥሮስ ይህን ልዩ መብት የሰጠው ኢየሱስ ክርስቶስ ነበር።”—ዘ ፕሪማሲ ኦቭ ዘ ቢሾብ ኦቭ ሮም ዲዩሪንግ ዘ ፈርስት ስሪ ሴንቸሪስ፣ 1903፣ በቫንሳን ኤርሞኒ

“በመሆኑም ማንኛውም ሰው ቢሆን . . . የሮም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ይህን የመጨረሻ ከፍተኛ ሥልጣን ሊይዙ የቻሉት የብጹዕ ጴጥሮስ ተተኪ በመሆናቸው እንደሆነ የማይቀበል ከሆነ የተረገመ ይሁን [ይህም ማለት መናፍቅ ተደርጎ ይቆጠር]።”—የመጀመሪያው የቫቲካን ምክር ቤት፣ ሐምሌ 18, 1870

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ካቶሊኮች የመጀመሪያው የቫቲካን ምክር ቤት በ1870 ያወጣውን ድንጋጌ የቤተ ክርስቲያኒቱ ቀኖና ወይም ሊሻር የማይችል ትምህርት አድርገው ይመለከቱታል። ይሁን እንጂ ይህ ትምህርት ቅዱስ ጽሑፋዊ ነው? ብሎ መጠየቁ ተገቢ ነው። ከዚህም ሌላ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በእርግጥ የሐዋርያው ጴጥሮስ ተተኪ ናቸው? ለመሆኑ ጴጥሮስ የመጀመሪያው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ነበር?

“በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ”

የ1870ው የቫቲካኑ ምክር ቤት ድንጋጌ በዋነኝነት የተመሠረተው ምክር ቤቱ ለማቴዎስ 16:16-19 እና ለዮሐንስ 21:15-17 በሰጠው ትንታኔ ላይ ነው። በእነዚህ ጥቅሶች ላይ ሰፍሮ የምናገኘው በኢየሱስና በጴጥሮስ መካከል የተደረገው ውይይትም ሆነ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ሐዋርያው ጴጥሮስ በጥንቱ የክርስትና ታሪክ ወሳኝ ቦታ እንደነበረው ያሳያሉ። እንዲያውም ሁለቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በተገናኙበት ወቅት ጴጥሮስ በሕይወት ዘመኑ እንደ ዓለት ያሉ ባሕርያት እንደሚያንጸባርቅ ኢየሱስ በትንቢት ገልጾ ነበር። (ዮሐንስ 1:42) ይሁንና ክርስቶስ ጴጥሮስን የሁሉም የበላይ አድርጎ ሾሞታል?

ማቴዎስ 16:17, 18 ላይ ኢየሱስ ጴጥሮስን “እኔም እልሃለሁ፣ አንተ ጴጥሮስ [ስሙ “ትንሽ ዓለት” የሚል ትርጉም አለው] ነህ፣ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ” እንዳለው ተገልጿል። * ኢየሱስ ይህን ሲል የእሱ ‘ቤተ ክርስቲያን’ ወይም ጉባኤ ሥጋ ለባሽ በሆነው በጴጥሮስ ላይ እንደሚገነባ እየተናገረ ነበር? ጴጥሮስ የሌሎቹ የኢየሱስ ተከታዮች ራስ ወይም መሪ ይሆናል ማለት ነው? በወቅቱ ሁለቱ ሲነጋገሩ ያዳምጡ የነበሩት ሌሎች ሐዋርያት ኢየሱስ የተናገረውን ሐሳብ የተረዱት እንዴት ነበር? የወንጌል ዘገባዎች እንደሚገልጹት ከዚያ በኋላ፣ በተለያዩ ጊዜያት ታላቅነትን በተመለከተ በመካከላቸው ክርክር ተነስቷል። (ማቴዎስ 20:20-27፤ ማርቆስ 9:33-35፤ ሉቃስ 22:24-26) ኢየሱስ ለጴጥሮስ ከሁሉ የላቀ ቦታ ሰጥቶት ወይም የሁሉም የበላይ እንዲሆን ሾሞት ቢሆን ኖሮ ከሐዋርያቱ መካከል ማን ታላቅ እንደሆነ ጥያቄ ይነሳ ነበር?

ለመሆኑ ጴጥሮስ ኢየሱስ የተናገረውን ሐሳብ የተረዳው እንዴት ነበር? ጴጥሮስ እስራኤላዊ በመሆኑ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ስለ “ድንጋይ” እና “የማዕዘን ድንጋይ” የሚናገሩትን የተለያዩ ትንቢቶች እንደሚያውቅ ይታመናል። (ኢሳይያስ 8:13, 14፤  28:16፤ ዘካርያስ 3:9) ጴጥሮስ ለእምነት ባልንጀሮቹ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ከትንቢቶቹ አንዱን ጠቅሶ “የማዕዘን ድንጋይ” እንደሆነ በትንቢት የተነገረለት መሲሕ፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ገልጿል። ጴጥሮስ ፔትራ (ኢየሱስ በማቴዎስ 16፡18 በተናገረው ሐሳብ ላይ ይኸው ቃል ይገኛል) የሚለውን ግሪክኛ ቃል የተጠቀመበት ለክርስቶስ ብቻ ነው።—1 ጴጥሮስ 2:4-8

ሌላው ታማኝ የኢየሱስ ተከታይ ሐዋርያው ጳውሎስ ነው። ጳውሎስ፣ ሐዋርያው ጴጥሮስ የሁሉም የበላይ እንዲሆን ኢየሱስ ሾሞታል ብሎ ያምን ነበር? ጳውሎስ፣ “አዕማድ መስለው የሚታዩ” ከተባሉት ውስጥ ጴጥሮስ እንደሚገኝበት መጻፉ በጥንቱ የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ጴጥሮስ ላለው ቦታ እውቅና እንደሰጠ ያሳያል። ይሁንና ጳውሎስ ዓምድ ተደርገው የሚታዩ ሌሎችም መኖራቸውን ያምን ነበር። (ገላትያ 2:9) ከዚህ በተጨማሪ፣ ኢየሱስ የጉባኤው ራስ አድርጎ ጴጥሮስን ሾሞት የነበረ ቢሆን ኖሮ ጴጥሮስ በእምነት ባልንጀሮቹ ዘንድ ዓምድ ተደርጎ የሚታይ በሌላ አባባል የሚገመት ወይም የሚታሰብ እንደሆነ ብቻ ተደርጎ እንዴት ሊገለጽ ይችላል?

ጳውሎስ፣ ሐዋርያው ጴጥሮስ ከሰዎች ጋር በነበረው ግንኙነት ወጥ አቋም ሳይከተል የቀረበትን ጊዜ በተመለከተ ሲጽፍ በአክብሮት ሆኖም በሐቀኝነት “ፊት ለፊት ተቃወምሁት፣ ይፈረድበት ዘንድ ይገባ ነበርና” በማለት ገልጿል። (ገላትያ 2:11-14) ጳውሎስ፣ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያኑን ወይም ጉባኤውን በጴጥሮስ ወይም ፍጽምና በሚጎድለው በሌላ በማንኛውም ሰው ላይ ገንብቷል የሚል አስተሳሰብ አልነበረውም። ከዚህ ይልቅ ጉባኤው የተገነባው መሠረት በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እንደሆነ እምነት ነበረው። በጳውሎስ እምነት ያ “ዓለት ክርስቶስ ነበረ።”—1 ቆሮንቶስ 3:9-11፤ 10:4

“አንተ ጴጥሮስ ነህ . . .”

ታዲያ “አንተ ጴጥሮስ ነህ፣ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ” የሚለውን ሐሳብ መረዳት ያለብን እንዴት ነው? አንድን ተቀንጭቦ የተወሰደ ሐሳብ በትክክል ለመረዳት ዓውዱን ማንበብ ይኖርብናል። ኢየሱስና ጴጥሮስ እየተነጋገሩ የነበሩት ስለምን ጉዳይ ነው? ትንሽ ቀደም ሲል ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ?” በማለት ጠይቋቸው ነበር። ጴጥሮስ ምንም ሳያመነታ “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” የሚል መልስ ሰጠ። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ለጴጥሮስ አድናቆቱን ገለጸለት፤ አክሎም ‘ቤተ ክርስቲያኑን’ ወይም ጉባኤውን ይበልጥ ጠንካራ በሆነ “ዓለት” ላይ እንደሚገነባ ነገረው፤ ይህም  ዓለት ጴጥሮስ እምነት የጣለበት ኢየሱስ ራሱ ነው።—ማቴዎስ 16:15-18

ኢየሱስ “አንተ ጴጥሮስ ነህ፣ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ” ሲል ምን ማለቱ ነበር?

ከዚህ ጋር በሚስማማ መንገድ ብዙ “የቤተ ክርስቲያን አባቶች” ማቴዎስ 16:18 ላይ የተጠቀሰው ዓለት ክርስቶስ እንደሆነ ጽፈዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በአምስተኛው መቶ ዘመን የኖረው ኦገስቲን እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ጌታ እንዲህ ብሏል፦ ‘በዚህች ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እገነባለሁ፤’ እንዲህ ሊል የቻለው ጴጥሮስ ‘አንተ ክርስቶስ የሕያው አምላክ ልጅ ነህ’ ስላለው ነው። ስለዚህ ቤተ ክርስቲያኔን የምገነባው አንተ እምነት በጣልክበት በዚህ ዓለት ላይ ነው።” ኦገስቲን “ዓለቱ (ፔትራ) ክርስቶስ መሆኑን” በተደጋጋሚ ገልጿል።

ኦገስቲንም ሆነ ሌሎች፣ በአሁኑ ጊዜ ተቀባይነት ባለው የካቶሊክ አስተምህሮ መሠረተ ቢዳኙ ኖሮ እንደ መናፍቃን በተቆጠሩ ነበር። እንዲያውም ስዊዘርላንዳዊው የሃይማኖት ምሑር ኡልሪክ ሉስ እንዳሉት ከሆነ በዛሬው ጊዜ ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን በዚህ ጉዳይ ላይ ያላቸው የጋራ አቋም፣ በ1870ው የቫቲካን ምክር ቤት መናፍቅነት ተብሎ በተወገዘ ነበር።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ የጴጥሮስ ተተኪ ናቸው?

ሐዋርያው ጴጥሮስ “ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት” የሚለውን የማዕረግ ስም አያውቀውም። እንደ እውነቱ ከሆነ ሮማውያን ያልሆኑ ብዙ ጳጳሳት እስከ ዘጠነኛው መቶ ዘመን ድረስ ይህን ማዕረግ ለራሳቸው ሲጠቀሙበት ቆይተዋል። ያም ሆኖ እስከ 11ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ድረስ ይህ የማዕረግ ስም ያን ያህል በይፋ አይሠራበትም ነበር። በተጨማሪም ከቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ ለጴጥሮስ ተሰጥቶታል ተብሎ የሚታመነው መብት ለተተኪዎቹ ተላልፏል የሚል አስተሳሰብ አልነበራቸውም። በመሆኑም ጀርመናዊው ምሑር ማርቲን ሄንገል “ከጊዜ በኋላ ተቀባይነት ያገኘውን ጳጳሱ ‘የሁሉም የበላይ ነው’ የሚለውን ሐሳብ እንድንቀበል የሚያስችል ታሪካዊም ሆነ ሃይማኖታዊ ማስረጃ የለም” የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል።

ለማጠቃለል ያህል፦ ጴጥሮስ የመጀመሪያው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ነበር? ተተኪስ ኖሮት ያውቃል? ጳጳሱ የሁሉም የበላይ ናቸው የሚለው የካቶሊክ ቀኖና ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ አለው? የእነዚህ ጥያቄዎች ትክክለኛ መልስ በአጭሩ “በጭራሽ” የሚል ነው። ይሁንና ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያኑን፣ በሌላ አባባል ትክክለኛ ጉባኤውን በራሱ ላይ የመገንባቱ ጉዳይ የማይታበል ሐቅ ነው። (ኤፌሶን 2:20) እንግዲያው በሁላችንም ፊት የሚደቀነው ወሳኝ ጥያቄ ‘እውነተኛውን ጉባኤ ለይቼ አውቄዋለሁ?’ የሚል ነው።

^ አን.8 በዚህ ርዕስ ላይ የተጠቀሱት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ሁሉ የተወሰዱት ከ1954 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ነው።