ሕዝቡ በጭቆና ቀንበር ሥር ወድቋል። በቀድሞ ዘመን እንደኖሩት አባቶቻቸው ሁሉ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት አይሁዳውያንም በወቅቱ ከነበረው የሮም የጭቆና ቀንበር ነፃ እንዲያወጣቸው በተደጋጋሚ ወደ አምላክ ጸልየው እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ከዚያም ስለ ኢየሱስ ሰሙ። ታዲያ በትንቢት የተነገረለት መሲሕ እሱ ይሆን? በዚህ ጊዜ በሮማውያን ጭቆና ይደርስባቸው የነበሩ በርካታ አይሁዳውያን ኢየሱስ ‘እስራኤልን ነፃ እንደሚያወጣ’ ጠብቀው ነበር። (ሉቃስ 24:21) ሆኖም ከጭቆና ነፃ አልወጡም። ይባስ ብሎም በ70 ዓ.ም. የሮም ሠራዊት መጥቶ ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሷን አወደመ።

ይህ የሆነው ለምንድን ነው? አምላክ ጥንት እንዳደረገው ለአይሁዳውያን ያልተዋጋላቸው ለምንድን ነው? ወይም ደግሞ ከጭቆና ቀንበር ነፃ ለመውጣት እንዲዋጉ ያልፈቀደላቸው ለምንድን ነው? አምላክ ለጦርነት የነበረው አመለካከት ተለውጦ ይሆን? በፍጹም። ይሁን እንጂ ከአይሁዳውያን ጋር በተያያዘ የተደረገ ጉልህ ለውጥ አለ። አይሁዳውያን የአምላክ ልጅ የሆነውን ኢየሱስን መሲሕ አድርገው አልተቀበሉትም። (የሐዋርያት ሥራ 2:36) በመሆኑም በብሔር ደረጃ ከአምላክ ጋር የነበራቸውን ልዩ ዝምድና አጡ።—ማቴዎስ 23:37, 38

የአይሁድ ብሔርና ተስፋይቱ ምድር ከዚህ በኋላ መለኮታዊ ጥበቃ ማግኘታቸው አበቃ። በተጨማሪም አይሁዳውያን ጦርነት ቢያካሂዱ ውጊያው በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዳለው ወይም እሱ ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው መናገር አይችሉም። ኢየሱስ አስቀድሞ እንደተናገረው ሥጋዊ እስራኤላውያን የአምላክን ሞገስ ያገኙ በነበረበት ጊዜ የሚፈስላቸው በረከት ከእነሱ ተወስዶ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘የአምላክ እስራኤል’ ተብሎ ለተጠራው በአዲስ መልክ ለተቋቋመው መንፈሳዊ ብሔር ተሰጠ። (ገላትያ 6:16፤ ማቴዎስ 21:43) በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖችን ያቀፈው ጉባኤ መንፈሳዊ የአምላክ እስራኤል ሆነ። በመሆኑም በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች “አሁን ግን የአምላክ ሕዝብ ናችሁ” ተብለዋል።—1 ጴጥሮስ 2:9, 10

ታዲያ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች “የአምላክ ሕዝብ” ተደርገው ስለተቆጠሩ አምላክ እነሱን ከሮማውያን ጭቆና ነፃ ለማውጣት ተዋግቶላቸዋል? አሊያም በሚጨቁናቸው ብሔር ላይ ጦርነት እንዲያካሂዱ ፈቅዶላቸው ነበር? በጭራሽ። ለምን? በአምላክ ትእዛዝ የሚደረግን ጦርነት በተመለከተ ባለፈው ርዕስ ላይ እንዳየነው፣ እንዲህ ዓይነቱ ውጊያ መቼ መካሄድ እንዳለበት የሚወስነው አምላክ ራሱ ነው። አምላክ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩ ክርስቲያኖች አልተዋጋላቸውም ወይም እንዲዋጉ አልፈቀደላቸውም። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው የመጀመሪያው መቶ ዘመን፣ አምላክ ክፋትንና ጭቆናን በጦርነት ለማስወገድ የመረጠበት ጊዜ አይደለም።

ስለዚህ በጥንት ዘመን እንደነበሩት የአምላክ አገልጋዮች ሁሉ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖችም አምላክ ክፋትንና ጭቆናን ለማስወገድ የወሰነው ጊዜ እስኪደርስ መጠበቅ ነበረባቸው። እስከዚያው ድረስ በጠላቶቻቸው ላይ በራሳቸው ተነሳሽነት ጦርነት እንዲያካሂዱ አልፈቀደላቸውም። ኢየሱስ ክርስቶስ በሰጠው ትምህርት ላይ ይህን ግልጽ አድርጓል። ለምሳሌ ያህል፣ ተከታዮቹ በጦርነት እንዲካፈሉ አላዘዛቸውም፤ ከዚህ ይልቅ “ጠላቶቻችሁን ውደዱ እንዲሁም ስደት ለሚያደርሱባችሁ ጸልዩ” ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 5:44) ኢየሱስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ኢየሩሳሌም በሮም ሠራዊት ጥቃት እንደሚሰነዘርባት ትንቢት ሲናገር ደቀ መዛሙርቱ ከተማዋ ውስጥ ቆይተው እንዲዋጉ ሳይሆን እንዲሸሹ አዟቸዋል፤ እነሱም ይህን ትእዛዝ አክብረዋል።—ሉቃስ 21:20, 21

በተጨማሪም ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት በጻፈው መልእክት ላይ “ራሳችሁ አትበቀሉ፤ ከዚህ ይልቅ ‘በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ’ ይላል ይሖዋ” ብሏል። (ሮም 12:19) እዚህ ላይ ጳውሎስ የጠቀሰው በዘሌዋውያን 19:18 እና በዘዳግም 32:35 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን  አምላክ ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት የተናገረውን ሐሳብ ነው። ባለፈው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው አምላክ በጥንት ዘመን ለሕዝቡ የተበቀለበት አንደኛው መንገድ በጠላቶቻቸው ላይ ጦርነት ሲያካሂዱ እነሱን በመርዳት ነበር። ስለዚህ ጳውሎስ የተናገረው ሐሳብ እንደሚያሳየው አምላክ ለጦርነት ያለው አመለካከት አልተለወጠም። በመጀመሪያው መቶ ዘመንም ቢሆን አምላክ ጦርነትን ለአገልጋዮቹ ሲል ለመበቀል እንዲሁም የተለያዩ የጭቆናና የክፋት ድርጊቶችን ለማስቆም የሚያስችል ትክክለኛ መንገድ አድርጎ ተመልክቶታል። ሆኖም በጥንት ዘመን እንደነበረው ሁሉ በዚህ ጊዜም እንዲህ ዓይነቱ ጦርነት መቼ መካሄድና ማን መዋጋት እንዳለበት የሚወስነው እሱ ራሱ ነበር።

ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው አምላክ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት ክርስቲያኖች እንዲዋጉ አልፈቀደላቸውም። ስለ ዘመናችንስ ምን ማለት ይቻላል? አምላክ በዛሬው ጊዜ እንዲዋጉ የፈቀደላቸው ሕዝቦች አሉ? ወይስ ይህ ወቅት ለአገልጋዮቹ ሲል ጣልቃ ገብቶ የሚዋጋበት ጊዜ ነው? አምላክ በዛሬው ጊዜ ጦርነትን እንዴት ይመለከተዋል? የዚህ ተከታታይ ርዕስ የመጨረሻ ክፍል ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።