አምላክ ወዳጆቹ እንድንሆን ጋብዞናል።

ሁለት ጓደኛሞች ወዳጅነታቸው እየጠነከረ እንዲሄድ እርስ በርስ መነጋገር አለባቸው። በተመሳሳይም አምላክ እንድናነጋግረው ጋብዞናል፤ በመሆኑም ከእሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንድንመሠርት አጋጣሚውን ከፍቶልናል። እንዲህ ብሏል፦ “እናንተም ትጠሩኛላችሁ፤ ወደ እኔም ቀርባችሁ ትጸልያላችሁ፤ እኔም እሰማችኋለሁ።” (ኤርምያስ 29:12) በመሆኑም አምላክን በጸሎት ስታናግሩት ‘ወደ እሱ ትቀርባላችሁ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል።’ (ያዕቆብ 4:8) መጽሐፍ ቅዱስ “ይሖዋ ለሚጠሩት ሁሉ፣ በእውነት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው” ይላል። (መዝሙር 145:18) ወደ አምላክ በጸለይን መጠን ከእሱ ጋር ያለን ወዳጅነት በዚያው ልክ እያደገ ይሄዳል።

“ይሖዋ ለሚጠሩት ሁሉ፣ በእውነት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው።”—መዝሙር 145:18

አምላክ አንተን ለመርዳት ዝግጁ ነው።

ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ከእናንተ መካከል ልጁ ዳቦ ቢለምነው ድንጋይ የሚሰጠው አለ? ወይስ ዓሣ ቢለምነው እባብ ይሰጠዋል? ታዲያ እናንተ . . . ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ በሰማያት ያለው አባታችሁማ ለሚለምኑት መልካም ነገር እንዴት አብልጦ አይሰጣቸው!” (ማቴዎስ 7:9-11) አዎን፣ አምላክ ወደ እሱ እንድትጸልይ የሚጋብዝህ ‘ስለ አንተ ስለሚያስብና’ አንተን መርዳት ስለሚፈልግ ነው። (1 ጴጥሮስ 5:7) እንዲያውም ችግሮችህን እንድትነግረው ይፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ “ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ፤ ከዚህ ይልቅ ስለ ሁሉም ነገር በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ” ይላል።—ፊልጵስዩስ 4:6

ሰዎች መንፈሳዊ ፍላጎት አላቸው።

ስለ ሰው ባሕርይ የሚያጠኑ ባለሙያዎች በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች መጸለይ አስፈላጊ እንደሆነ እንደሚሰማቸው ተገንዝበዋል። ከእነዚህ መካከል በአምላክ መኖር የማያምኑ ወይም መኖሩን የሚጠራጠሩ ሰዎች ይገኙበታል። * ይህም ሰዎች ከተፈጠሩበት ጊዜ አንስቶ መንፈሳዊ ፍላጎት እንዳላቸው የሚናገረውን ሐቅ ያረጋግጣል። ኢየሱስ “መንፈሳዊ ነገሮችን የተጠሙ ደስተኞች ናቸው” ብሏል። (ማቴዎስ 5:3) ይህን ፍላጎት ማርካት የምንችልበት አንድ መንገድ ዘወትር ከአምላክ ጋር መነጋገር ነው።

አምላክ ወደ እሱ እንድንጸልይ የሰጠንን ማበረታቻ የምንቀበል ከሆነ ምን ጥቅሞች ልናገኝ እንችላለን?

^ አን.8 ፒዩ የምርምር ማዕከል በ2012 ያካሄደው አንድ ጥናት እንዳሳየው ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከሚኖሩ በአምላክ መኖር ከማያምኑ ወይም ከሚጠራጠሩ ሰዎች መካከል 11 በመቶ የሚሆኑት ቢያንስ በወር አንድ ጊዜ ይጸልያሉ።