የይሖዋ ምሥክሮች ‘ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉና ጠቃሚ’ እንደሆኑ ያምናሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) መጽሐፍ ቅዱስ፣ ስለ ፈጣሪ ለመማርና ትርጉም ያለው ሕይወት ለመኖር እንደሚረዳ ስለምናምን የሕይወታችን መመሪያ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ “ስምህ ይሖዋ የሆነው አንተ፣ አዎ፣ አንተ ብቻ በመላው ምድር ላይ ልዑል እንደሆንክ ሰዎች ይወቁ” ይላል። (መዝሙር 83:18) በመሆኑም ይሖዋ አምላክን ብቻ የምናመልክ ሲሆን የእሱ ምሥክሮች በመሆናችን የግል ስሙን ለማሳወቅ ጥረት እናደርጋለን።—ኢሳይያስ 43:10-12

ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ደግሞ “የአምላክ ልጅ” * የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር እንደመጣና መሲሕ ሆኖ እንደተሾመ እናምናለን። (ዮሐንስ 1:34, 41፤ 4:25, 26) ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ወደ ሰማይ ሄዷል። (1 ቆሮንቶስ 15:3, 4) ከጊዜ በኋላ ደግሞ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኗል። (ራእይ 11:15) ይህ መንግሥት ምድርን ዳግመኛ ገነት የሚያደርግ በተጨባጭ ያለ መስተዳድር ነው። (ዳንኤል 2:44) መጽሐፍ ቅዱስ “የዋሆች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በብዙ ሰላምም እጅግ ደስ ይላቸዋል” ይላል።—መዝሙር 37:11, 29

“የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን ሲያነቡ አምላክ እያነጋገራቸው እንዳለ ይሰማቸዋል። በሕይወታቸው ውስጥ ችግር ሲያጋጥማቸው መፍትሔውን ከአምላክ ቃል ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ። . . . ለእነሱ የአምላክ ቃል አሁንም ሕያው ነው።”—የካቶሊክ ቄስ ቤንጃሚን ቼራያዝ፣ ሚዩንስተርላንደሽ ፎልክስጻይቱንግ ጋዜጣ፣ ጀርመን

የይሖዋ ምሥክሮች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች በዛሬው ጊዜ እንኳ ሳይቀር ለሰዎች ጠቃሚ እንደሆኑ ያምናሉ። (ኢሳይያስ 48:17, 18) ስለዚህ እነዚህን መመሪያዎች በጥብቅ እንከተላለን። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ አእምሯችንንና አካላችንን ከሚበክሉ ልማዶች እንድንርቅ ስለሚያስጠነቅቀን ሲጋራ አናጨስም ወይም በአደንዛዥ መድኃኒቶች አላግባብ አንጠቀምም። (2 ቆሮንቶስ 7:1) በተጨማሪም እንደ ስካር፣ ስርቆትና የፆታ ብልግና ካሉ መጽሐፍ ቅዱስ በቀጥታ ከሚያወግዛቸው ልማዶች እንርቃለን።—1 ቆሮንቶስ 6:9-11

^ አን.5 መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን “የአምላክ አንድያ ልጅ” በማለትም ይጠራዋል፤ እንዲህ የተባለው በይሖዋ አምላክ በቀጥታ የተፈጠረው የመጀመሪያው ፍጡር እሱ ብቻ ስለሆነ ነው።—ዮሐንስ 3:18፤ ቆላስይስ 1:13-15