ድርጅታችን ዓለም አቀፋዊ ነው፤ ይሁንና ከሌሎች ሃይማኖታዊ ቡድኖች ጋር ምንም ዓይነት ኅብረት የለንም። ዋናው መሥሪያ ቤታችን በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኝ ቢሆንም አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች የሚኖሩት በሌሎች አገሮች ውስጥ ነው። እንዲያውም ወደ ስምንት ሚሊዮን ገደማ የምንሆን የይሖዋ ምሥክሮች ከ230 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ እናስተምራለን። ይህን የምናደርገው ደግሞ ኢየሱስ “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል” ሲል የሰጠውን መመሪያ በማክበር ነው።—ማቴዎስ 24:14

የምንኖረው የትም ይሁን የት፣ መንግሥት ያወጣውን ሕግ እናከብራለን። በፖለቲካ ጉዳዮች ግን ፍጹም ገለልተኛ አቋም አለን። እንዲህ የምናደርገው ኢየሱስ ክርስቲያኖችን በተመለከተ ሲናገር “የዓለም ክፍል አይደሉም” በማለት የሰጠውን መመሪያ ስለምናከብር ነው። በመሆኑም በፖለቲካ ጉዳዮችና እንቅስቃሴዎች አንካፈልም ወይም ጦርነትን አንደግፍም። (ዮሐንስ 15:19፤ 17:16) እንዲያውም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች የገለልተኝነት አቋማቸውን ለማላላት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው እስራትና ድብደባ አልፎ ተርፎም የከፋ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ጳጳስ የነበሩ አንድ ጀርመናዊ “ሦስተኛውን ራይክ [የሂትለርን አገዛዝ] እንደተቃወሙ በትክክል መናገር የሚችሉት እነሱ ብቻ ናቸው” ሲሉ ጽፈዋል።

“[የይሖዋ ምሥክሮች] ጠንካራ የሥነ ምግባር አቋም አላቸው። ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ አስተሳሰብ ያላቸውን እነዚህን ሰዎች ለከፍተኛ የፖለቲካ ሥራ ልንጠቀምባቸው እንችል ነበር፤ ይሁንና ፖለቲካ ውስጥ ይገባሉ ብሎ ማሰብ ዘበት ነው። . . . የመንግሥት ባለ ሥልጣናትን የሚታዘዙ ቢሆንም የሰው ልጆች የገጠሟቸውን ችግሮች በሙሉ የሚያስወግደው የአምላክ መንግሥት ብቻ እንደሆነ ያምናሉ።”—ኖቨ ስቮቦደ ጋዜጣ፣ ቼክ ሪፑብሊክ

ያም ሆኖ ከሰዎች ተገልለን አንኖርም። ኢየሱስ ተከታዮቹን አስመልክቶ “የምለምንህ ከዓለም እንድታወጣቸው ሳይሆን ከክፉው እንድትጠብቃቸው ነው” በማለት ወደ አምላክ ጸልዮአል። (ዮሐንስ 17:15) በመሆኑም በመኖሪያ አካባቢያችን በሥራና በገበያ ቦታ እንዲሁም በትምህርት ቤት ልታየን ትችላለህ።